2013-04-10 08:58:27

እውነተኛ ሰላም የሚሸጥ የሚለወጥ ሳይሆን የእግዚአብሔር ስጦታ ሆኖ ከጌታ ኢየሱስ ጋር በሚደረገው አስገራሚ መነናኘት የሚመነጭ ነው፣


በላቲኑ ሥርዓተ አምልኮ ያለነው ዘመን ዘመነ ትንሣኤ ሆኖ ከሙታትን ተለይቶ የተነሣው ጌታ ደቀ መዛሙርቱን በሚገናኝበት ሁል ጊዜ የሚለው “ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን” የሚል ሐረግ ነው፣ ይህ ሰላም ምን ይሆን? የሚለውን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ትናንትና በቫቲካን በሚገኘው የቅድስት ማርታ እንግዳ መቀበያ ቤተ ጸሎት ከቅድስት መንበር ሠራተኞች ካህናትና ከቫቲካን ማተምያ ቤተ ሠራተኞች ጋር አብረው ባሳረጉት መሥዋዕተ ቅዳሴ የዕለቱን ቃለ ወንጌል ተመርኵዘው ባቀረቡት አጭር ስብከት “እውነተኛ ሰላም የሚሸጥ የሚለወጥ ሳይሆን የእግዚአብሔር ስጦታ ሆኖ ከጌታ ኢየሱስ ጋር በሚደረግ አስገራሚ መነናኘት የሚመነጭ ነው፣” ሲሉ እኛም በዚህ ግርምት መነካት እንዳለብንና ጌታን ይህንን ሰላም እንዲሰጠን መለመን እንዳለብን አሳስበዋል፣
በሕይወት ዘመናችን ችግርና ፈተና ሊያጋጥመን ባህርያዊ ነው፤ ሆኖም ግን ልክ ክርስቶስ እስከ መጨረሻ በአስጨናቂው የመስቀል ሞትም ሳይቀር ሰላምን ሳያጠፋ መኖሩ ይህም ሰላም ውሳጣዊ ኃይል ሆኖ ሁሉን የሚያረጋጋና ከአባታችን ጋር የሚያስተሳስር መሆኑን መዘንጋት እንደሌለብን ገልጠዋል፣ ሕያው ኢየሱስን ስናገኝ የሚሰማን የመገረም ስሜት ነው፣ አንዳንዴ እውነትም ሊመስለን አይችልም፣ ጌታ ግን እውነት መሆኑን ይነገረናል ያስረደናልም፣ ከእኛ የሚፈለገው እግዚአብሔር ይህንን ጸጋ እንዲሰጠን መጠየቅ ብቻ ነው፣ ጸጋ ነው ስንል በነጻ የሚሰጥ ነው ለማለት ነው፣ እውነት ነው በሕይወት ዘመናችን የዚህ ተቀራኒ ፈተና በሰብ አዊ ደካማነታችን ወይንም አንጎላችን ሲታመም ወይም ከዲያብሎስ በሚመጣን ፈተና ልንክደው ብንጥርና የማይጨበጥ ሆኖ ቢታየንና ለማመን ቢያቅተን እግዚአብሔር ግን እውን መሆኑን የረጋግጥልናል፣
የክርስትና መጀመርያ ይህ ነው፤ ጌታን በማግኘታችን በሚሰማን በሚያስገርም የደስታ ስሜት ይጀምራል፣ ሆኖም ግን ሁሌ በዚሁ ግርምት ልንኖር አይቻልም፣ ነገር ግን በር ክፋች መሆኑንም መዘንጋት የለብንም፣ ይህ መገረም በነፋሳችን የማይደመሰስ ማኅተም በመተው መንፈሳዊ መጽናናትን ይሰጠናል፣
ይህ ኢየሱስ ክርስቶስን ማግኘት የሚሰጠን ሰላምና መጽናናት እስከ መጨረሻ ይሸኘናል፣ ማንኛው ክርስትያን ሁሌ በዚህ ሰላምና መጽናናት መሸኘት አለበት፣ በተለይ ደግሞ አስጨናቂ ፈተናዎች እና ብርቱ ሥቃይ በሚገጥምበት ጊዜ ሰላምንና የኢየሱስ ከእርሱ ጋር መኖርን መዘንጋት የለበትም፣ አብዝቶ ለመጸለይ ብርታት ማግኘት አለበት፤ ጌታ ሆይ ይህንን ጸጋ ስጠኝ ያንን አንተን ሳገኝ በነፍሴ ያተምከውን መንፈሳዊ ማኅተም አንቀሳቅስልኝ መንፈሳዊ ጽናትና ሰላም ስጠኝ ብለን እስከ መጨረሻ እንለምን ሲሉ ስብከታቸውን ደምድመዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.