2013-03-27 17:51:30

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍርንቸስኮስ ዛሬ ሮብ ረፋድ ላይ የመንበረ ጴጥሮስ ስልጣን ከጨበጡ ብኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ባቀረቡት ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በላቲኑ ሥርዓተ አምልኮ የተያዝነውን ሶሙነ ሕማምት ትርጕምና መልእክት ካስተማሩ በኋላ ስለመሃከለኛው የአፍሪቃ ሪፓብሊክ ይህንን ጥሪ አስተላልፈዋል፣ °በዚሁ ሰዓታት በመሀከለኛው አፍሪካ ሪፓብሊክ እየተክሄደ ያለውን ሁኔታ በጥንቃቄ እየተከታተልሁት ነኝ፤ ለሚሰቃዩት ሁሉ በተለይ ደግሞ የዚሁ ችግር ሰለባ ለሆኑት ቤተሰቦች የቆሰሉትንና ቤት ንብረታቸውን ትተው ለሕይወታቸው የሸሹትን በጸሎቴ እንደማስባቸው ላረጋገጥላቸው እወዳለሁ፣ በቦታው የሚካሄደው ዓመጽና ዝርፍያ እንዲቆም እንዲሁም ለብዙ ጊዜ የግጭትና ዓመጽ ሰለባ ለሆነው አገሩ ችግር ፖሎቲካዊ መፍትሔ ተግኝቶ ለተወዳጁ የመሀከለኛ አፍሪቃ ሪፓብሊክ ሰላምና ዕርቅ እንዲመለስለት እማጠናለሁ፣”
ቅዱስነታቸው ስለሶሙነ ሕማማት ያስተማሩት ትምህርተ ክርስቶስ እንዲህ ነበር፣
ሰላም ወንድሞችና እኅቶች፤ በዚሁ የመጀመርያ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ ስቀበላችሁ በታላቅ ደስታ ነው፣ ከኔ በፊት ከነበሩ እጅግ ከማፈቅራቸው ልሂቅ ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ እጆች ይህንን ምስክርነት በታላቅ ክብር እቀበላለሁ፣ ከፋሲካ በኋላ የእምነት ዓመት ትምህርተ ክርስቶስ እንደገና እንጀምራለን፣ ዛሬ ስለ ሶሙነ ሕማማት ጥቂት ለማለት እፈልጋለሁ፣ ጌታ ኢየሱስን በሕማማቱ በሞቱና በትንሣኤው የምንሸኝበት የሥርዓተ አምልኮ አንኳር የሆነው ይህን ሳምንት በዕለተ ሆሳዕና ጀምረነዋል፣
ለመሆኑ ሶሙነ ሕማማትን መኖር ለእኛ ምን ማለት ይሆን? ጌታ ኢየሱስን በመስቀል እስከ ሞትና ትንሣኤ መከተል ማለት ምን ማለት ነው? ኢየሱስ በምድራዊ ተልእኮው በቅድስት መሬት ተመላልሰዋል፤ ከእርሱ ጋር እስከ መጨረሻ የተጓዙ የዋሃን የሆኑ 12 ሐዋርያት መረጠ፤ እነኚሁ ሕይወቱን ተሳትፈዋል ተል እኮውን ከእርሱ በኋላ እንዲቀጥሉ ሆነዋል፤ ሴመርጣቸውም እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ ሙሉ እምነት ከነበራቸው ሕዝብ መካከል ነው የመረጣቸው፣ አለምንም መለያየት ለታላላቅና ለትሑታን ለሁላቸው ተናገረ፤ ለሃብታሙ ወጣት እንዲሁም ለድሃዋ መበለት፣ እንዲሁም ለኃያላንና ለዳካሞች፤ ለሁላቸውም የእግዚአብሔር ርኅራኄና ምሕረት አመጣላቸው፣ ሕሙማንን ፈወሰ ያዘኑትን አጽናና ችግረኞችን ረዳ ተስፋ ሰጠ፤ እንደ አንዲት የዋህ እናትና ርኅሩኅ አባት ለልጆቻቸው እንደሚያደርጉት ስለእያንዳንዱ የሴት ልጅና የሰው ልጅ የሚያስብ እግዚአብሔር በመካከላችን አመጣልን፣ እኛ ወደ እርሱ እንድንሄድ አልጠበቀም ነገር ግን አለምንም መተሳሰብና መቆጣጠር እርሱ ራሱ ወደ እኛ መጣ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ነው፣ ወደ እኛ በመምጣት የመጀመርያውን እርምጃ የሚወስደው እርሱ ነው፣ ኢየሱስ በጊዜው የነበሩ ሰዎች ኑሮን በየዕለቱ በመኖር ሕዝቡን ባየ ጊዜ እረኛ እንደሌላቸው መንጋ ሆነው ስላገኛቸው ራራላቸው፣ በአል አዛር ሞት ምክንያት የማርታና የማርያ ስቃይ ባየ ጊዜ አልቀሰ፤ ከመጸበሐውያን አንዱን የእርሱ ተከታይ እንዲሆን ጠራው፣ የጓደኛ ክህደት ሥቃይንም ተቀበለ፣ እግዚአብሔር በኢየሱስ ከእኛ ጋርና በመካከለችን የመኖሩ እርግጠኛነት ሰጠን፣ ስለቀበሮዎች ሲናገርም “ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም” (ማቴ 8፤20) አለ፣ ኢየሱስ ቤት የለውም ቤቱ ሰዎች ናቸው፤ ቤቱ እኛ ነን፣ ተለእኮውም ለሰው ልጆች ህሉ የእግዚአብሔር በርን መክፈት ነው በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅር በመካከላችን መሮሩን አረጋግጥልናል፣
በሶሙነ ሕማማት የዚህ ተልእኮ ጉዞ ማለትም በእግዚአብሔርና በሰው ልጅ መካከል ስላለው ግኑኝነት ያለው የፍቅር እቅድ ታሪክ ከፍተኛ ጠርዝ እናጣጥማለን፤ ኢየሱስ ተልእኮውን የሚያጠቃልልበት የመጨረሻውን ጉዞ ለመፈጸም ለገዛ ራሱ ምንም ሳያስቀር ሕይወቱን ሳይቀር ለመሰዋት ኢየሩሳሌም ይገባል፤ በመጨረሻው እራት ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ሥጋው የሆነ እንጀራን ይካፈላል ደሙ የሆነ ጽዋውን ለእኛ ያቀርበዋል፣ የእግዚአብሔር ልጅ ለእኛ ይሰዋል፣ ለሁል ጊዜ ከእኛ ጋር ለመኖር ደግሞ ስጋውና ደሙን ይሰጠናል፣ በደብረ ዘይት እንዲሁም በጲላጦስ ፍርድ ፊት አለ ምንም ተቋውሞ ራሱን ይሰጣል፣ በትንቢተ ኢሳያስ እንደተመለከተው ራሱን እስከ ለሞት አሳልፎ የሚሰጥ የሚሰቃየው የእግዚአብሔር ባርያ ነው (ኢሳ 53፤12)፣
ኢየሱስ ይህንን እስከ ሞት መሥዋዕት የሚያደርሰው ፍቅር አለምንም ስሜት ወይንም እንደ ዕጣ ፈንታ ዝም ብሎ አይደለም የሚቀበለው፣ ነገር ግን እንደ እውነተኛ ሰው በዚሁ ዓመጸኛ አገዳደል በፊት የተሰማውን መናወጥ ሊድብቅ አልቻለም ሆኖም ግን በሙሉ መተማመን ሁሉን በእግዚብሔር አብ እጅ ይተዋል፣ ኢየሱስ ለእግዚአብሔር አብ ፍቅር መልስ ለመስጠት ወዶ ሞትን ተቀበለ፤ ይህም ከእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ጋር ሙሉ በሙሉ በመጋጠም ነው፣ እንዲህ ያደረገውም ፍቅሩን ሊያሳየን ብሎ ነው፣ ቅ.ጳውሎስ እንደሚለው ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሆኖ አፈቀረኝ ለእኔም ራሱ አሳልፎ ሰጠ (ገላ 2፡20) ይላል፣ እያንዳንዳችን ደግሞ ይህንን ለኔ የሚለውን ቃል በመድገም “አፈቀረኝ ለኔም ራሱን አሳልፎ ሰጠ” ለማለት እንችላለን፣
ይህ ሁሉ ዛሬ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? ይህ ጉዞ መንገዴ መንገደህ የሁላችን መንገድ ነው፣ ሶሙነ ሕማማትን በልባችን በማዘን ብቻ ሳይሆን እርሱን በመከተል ልናሳልፈው አለን፣ ማለትም ከገዛ ራሳችን ወጣ በማለት ሌሎችን ለማግኘት በተለይ ደግሞ ኑሮ ብሶባቸው ከመካከል ወጥተው በየጠረፉ ለሚኖሩ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችንን እጅግ ርቀውና ተረስተው መጽናናት መረዳዳትና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን መርዳት ያስፈልጋል፣
በጾመ አርባ የሕማማት ሳምንት በተለይም ወደ እግዚብሔር ዕቅድና ሃሳብ የምንገባበት ግዜና ሰዓት ነው። ይህም ወደ የመስቀል ትርጉሙ። መስቀል ከሁሉም በላይ ስቃይና ሞት እንዳልሆነ ግን የፍቅር ስጦታ ሆኖ ሕይወት የሚሰጥ ነው። የወንጌልም ትርጉም ይህን ይሰጠናል። ክርስቶስን መከተልና ደቀ መዝሙሩ መሆን ። የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን በመጀመሪያ የሚፈለገው ከእኔነታችን እንድንወጣ ነው። ከእኔነታችን መውጣት ማለት ከዘልማድ ባሕሪያችን፣ የተዳከመ እምነትና የጸሎት ሕይወት፣ ከራሳችን ሐሳብ ውጭ በተለያየ መልኩ በሚደርሱብንና በሚያጋጥሙን ፈተናዎች አቅጣጫችንን በመቀየር ከፈጣሪያችን ጋር ያለንን ግንኙነት እንድናቋርጥ ያደርጋል።
እግዚአብሔር ከእራሱ በመውጣት ከእኛ ጋር እንዲሆን መጥቶልናል፣ ለእኛ ሲል ድንኳኑን ዘርግቶልናል፣ ይህም የእግዚብሔር ምህረት ድንኳን፣ የሚያድንና ተስፋን የሚሰጥ ነው። ስለዚህ እኛም ልንከተለውና አብረነው እንድንሆን ከፈለግን እረኛው ከብቶች በረት ውስጥና ዙርያ ከ 99 በጎቹ ጋር በመቀመጥ አብረነው የጠፋችዋንና ርቃ የኮበለለችውን አንዲት በግ አብረነው ሆነን ለመፈለግ ብቻ እንውጣ!! እዚህ ላይ ላሳስባችሁ የምወደው መውጣት የሚለው ቃል ነው። ከእኔነታችን እንደ እየሱስ በመውጣት ፣ እግዚአብሔር ከራሱ በመውጣት በእየሱስ እንደሆነና፣ እየሱስም ለኛ ሲል ከእራሱ እንደወጣ ነው።
አንዳንዶቻችሁ አባ እኔ ግዜ የለኝም! ብዙ የማደርጋቸው ነገሮች አሉኝ ከባድ ነው እንዳው እኔ በሐይሌ ወይንም በጉልበቴ ምን ማድረግ የምችል ይመስሎታል? አቤት ስንት ነገሮችና ሐጢዓቶችም አሉ? አብዛኛው ግዜ እንዲሁ በአፍ ምስጋና ጸሎትና ከልብ ባልሆነ የዘልማድ የእሁድ ቅዳሴ ጸሎትና አንዳንድ መልካም ነገሮችን በማድረግ ስንኖር ግን እውነተኛውን ክርስቶስን በሕይወታችን ለመኖር በድፍረት ከእኔነታችን ለመውጣት እርምጃ መውሰድ ያቅተናል። እኛም ቅዱስ ጴጥሮስን እንመስለዋለን። እየሱስ ስለ መስቀል ሞትና ትንሣኤው እየሱስ ለእኛና ለሁሉም ስላለው ፍቅር ሲያስተምር ሐዋሪያው ጴጥሮስ ወደ እርሱ በመውሰድ ይገሥጸው ነበር። ምክንያቱም እየሱስ የሚለው ለሐዋሪያው ጴጥሮስ ከሱ ኃሳብ የራቀና ተቀባይነት የሌለው የራሱን ዋስትና በራሱ አመለካከት የነበረውን የሚያፈርስና በተለይም ስለ መሲህ አዳኝ የነበረው አመለካከት የተለየ ስለነበር ነው። እየሱስም ደቀ መዛሙርቱንም አይቶ ጴጥሮስን ገሠጸው ይህ ተግሳፅ በወንጌል ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ ከምናገኘው ከበድ ያለ ቃል አንዱ ሲሆን ይህም ኢየሱስ ጴጥሮስን ወደ ኋላዬ ሂድ አንተ ሰይጣን የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና ይለዋል። ማርቆስ ምዕ 8 ቁ.33 እግዚአብሔር ሁል ግዜ ሲያስብ በምህረት ነው ይሕንን እንዳትረሱ በመደጋገም አደራ የምለው እግዚአብሔር የምህረት አባት ነው። እግዚብሔር የሚያስበው እንደ የልጁን መመለስ የሚጠብቅና የሚጠባበቅ አባትና ልጁን የሚቀበል አባት ነው ልጁን ሲመለስ ከሩቅ ሆኖ ያየዋል የዚህ ትርጉሙ ምንድነው? በየቀኑ ልጁ ወደ ቤቱ እንደተመለሰ ለማየት የሚጠባበቅና የሚከታተል አባት ነው። ይህ ነው የኛ የምህረት አባታችን!! ምልክቱ ከልቡና ከቤቱ በረንዳ ይጠብቀው እንደነበር ነው። እግዚአብሔር የሚያስበው እንደ መልካሙ ሳምራዊ ችግረኛው ጎን ሐዘኑን በመግለፅ የማያልፍና ችግርን እንዳላየ ሳይሆን ግን ምንም ነገር ሳይፈልግና ሳይጠይቅ የሚረዳ የችግረኛውን ማንነት ዘር ሐብት ወይም እምነት ምንም ጥያቄ ሳያደርግ እንዲሁ በነፃ የሚረዳ እግዚአብሔር አባት ነው። እግዚአብሔር የሚያስበው እንደ እረኛ ሕይወቱን በጎቹን ለመከላከልና ለማዳን የሚከላከል አባት ነው። የሕማማት ሳምንት የምሕረት ግዜ እግዚአብሔር የሚሰጠን ስጦታ የልባችንን በሮች እንድንከፍት በሕይወታችን በቤተክርስቲያኖቻችን የሚሰጠን ግዜ ነው። ብዙ ቤተክርስቲያኖች ተዘግተው ማየት እንዴት ያሳዝናል!! በየቁምስናችን የተለያዩ ማኅበሮችና ድርጅቶች በሕብረት በመሆን እንውጣ ከሌሎች ጋር በመገናኘት በኛ ውስጥ ያለውን ደስታና ብርሃን እንዲሁም እምነታችንን ለሌሎች እናካፍል ሁሌ ሁልግዜ መውጣት!! ይህም በእግዚብሔር ፍቅርና ርህራሄ፣ በትህትናና በትዕግስት! ይህም እኛ ሙሉ በሙሉ በአካሄዳችን ልባችን እጆቻችን ተሳታፊዎች መሆናችንን እያወቅን ግን የሚሰራውና የሚመራው እግዚአብሔርና ፍሬውም የሱ መሆኑን እናውቃለን። ለሁላችሁም በነዚህ ቀናት ክርስቶስን በመከተል በድፍረት የፍቅሩን ጮራ ለኛና ለሌሎች እናካፍል!!








All the contents on this site are copyrighted ©.