2013-03-25 13:41:52

ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ቅዱስ አባታችንን ር.ሊ.ጳ. በጉጉት እየተጠባበቀ ነው


RealAudioMP3 28ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በብራዚል ሪዮ ደ ጃኒየሮ ከተማ ሐመሌ ወር 2013 ዓ.ም. እንደሚካሄድ ቀደም ተብሎ መገለጡ የሚታወስ ሲሆን፣ የብራዚል ወጣቶችና የመላ ዓለም ወጣቶች ቅዱስነታቸውን በጉጉት እየተጠባበቁ መሆናቸው በሐዋርያዊ ተልእኮ ጉብኝት እዚህ ሮማ የሚገኙት የሪዮ ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ኦራኒ ዥዋው ተምፐስታ ከቫቲካን ረዲዮ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ ገልጠዋል።
ወደ ሮማ ስመጣ የሪዮ ወጣቶች ቅዱስ አባታችንን ር.ሊ.ጳ. ሰላም እንድልላቸውና በጉጉት መንፈስ እየተጠበቁዋቸው መሆናቸውም ንገርልን ብለውኛል። በርግጥ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. የመረጡት ስም የቅዱስ ፍራንቸስኮ ዘአሲዚ ስም በመሆኑ ሁሉም ወጣቶች ለዚህ ቅዱስ ካላቸው አድናቆትና ፍቅር በቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ላይ ያኖርት እምነትና ፍቅር ጥልቅና አቢይ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወት ማእከል የማድረጉ ጥሪ የሚያጎሉ ናቸው። የቅዱስ አግናዚዮ ዘሎዮላ ልጅ እንደመሆናቸውም መጠን የቅዱስ እግናዚዮ ዘሎዮላ ጥልቅ መንፈሳዊ ትምህርት ያነገቡም ናቸው። ቅዱስ ፍራንቸስኮ ዘአሲዚና ቅዱስ ኢግናዚዮ ዘሎዮላ አጣምረው የሚኖሩ የቅዱስ ጴጥሮስ ተከታይ እንደመሆናቸውም መጠን ቤተ ክርስቲያንና ወጣት ትውልድ ሊኖረው የሚገባውን መንፈሳዊነት በቃልና በሕይወት የሚያስተምሩ ናቸው ካሉ በኋላ ሪዮ ደጃነይሮ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ለማስተናገድ በቅዱስነታቸው ልኂቅ ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ ከተመረጠችበት ዕለት ጀምሮ ቅድመ ዝግጅቱ በተዋጣለት ሁኔታ እያከናወነች መሆንዋንም ገልጠው፣ ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቆ ቅዱስ አባታችንና ወጣቶችን ለማስተናገድ በመጠባበቅ ላይ ነን፣ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ለመጀመሪያ ጊዜ በመምራትና መሪ ቃል በመለገስ እንዲሁም በእምነት ወንድሞችን በማጽናት የሚሳተፉበት ነው። ለቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮስ እንደ የቅዱስ ጴጥሮስ ተከታይ ይህ በብራዚል የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን የመጀመሪያቸው ነው። ስለዚህ 28ኛ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ለቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ቀዳሜ ተመክሮ ነው። በመሆኑም ታሪካዊነቱ ከወዲሁ ለመገመቱ አያዳግትም ካሉ በኋላ ሪዮ ከተማ ጥልቅ መንፈሳዊነት የሚኖርባት የተለያዩ ማኅበራዊና ሰብአዊ ችግሮች የሚፈራረቁባት ከተማ ብትሆንም የወጣቶች ኃሴት የሚታይባት ከተማ ነች፣ በከተማይቱ እጅግ ከፍ ብሎ የተሰቀለው እጆቹን የዘረጋው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሐወልት የከተማይቱ መንፈሳዊና ባህላዊ ገጽታ የሚያብራራ ነው በማለት የሰጡትን ቃለ ምልልስ አጠቃለዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.