2013-03-22 18:44:54

ሰንበት ዘምኵራብ 15/3/ 2005 ዓ.ም. (3/24/ 2013)


መዝሙር: ቦአ ኢየሱስ ምኵራበ አይሁድ ወመሃረ ቃለ ሃይማኖት. . . . .
ንባባት: ፍሊጲ 3፡17~4፦1፥ ያዕ 4፡1~12፥ ግ.ሓ 5፡17~3፥ ሉቃ 9፡28~36
ስብከት: እስመ ቅንአተ ቤተከ በልዓኒ፥ ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ፤ ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ መዝ. 69፡9 የዐቢይ ፆም ሦስተኛ ሳምንት

«ኢትግብሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ ፤… ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ትሰመይ» (ዮሐ 2፡16፤ ኢሳ 56፡7)
RealAudioMP3
በዛሬው ሰንበት የሚነበብልን ወንጌል ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሄደና በዚያም ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚገበያዩትን ሁሉ እንዳስወጣ የሚናገር ነው፡፡ ክርሰቶስ ለአባቱ ቤት ያለውን ቀናተኛነት፣ ለመቅደሱ ያለውን ፍቅር የጸሎት ቤቱን በማጽዳት፣ ከነጋዴዎች በመከላከል ገለጸ፤ በዚህም ሁኔታ በመዝሙር «ቅንዓተ ቤትከ በልዓኒ (የቤትህ ቅናት በልታኛለች)» የተባለው ተፈጸመ (መዝ 68፡9)፡፡
በዚህ የጸጋ ወቅት ለምንገኝ ይህ የወንጌል ክፍል ምንድን ነው የሚያስተምረን?
ሐዋርያው ቅ. ጳውሎስ የሰውን አካል ክቡርነት «ለመሆኑ ሰውነታችሁ (ሥጋችሁ) በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቁምን?» በማለት ይገልጸዋል (1ቆሮ 6፡19)፡፡ ይህ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ እንዲሆን የተመረጠ ሥፍራ ምንኛ ንጹህ ቅዱስ እና የተመቸ ሊሆን በተገባ፡፡ ለዚህ ደግሞ ራስን ማወቅ ወደ ውስጣችን መመልከት፣ ስንት ነገር በልባችን ላይ እንደተቆለለ ማየት፤ ይህን በይበልጥ ላመረዳት ደግሞ ውስጣችንን በሥጋዊ ሳይሆን በኅሊና ዓይን ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ያኔ መጠኑ ይብዛም ይነስ የምናገኘው ነገር አለ ፤ ኃጢአት በደል ክፋት ምቀኝነት ወገንተኝነት ተራ መታበይ ንፍገት ስስት አፍቅሮተ ንዋይ በእግዚአብሔር መልክና አምሳል የተፈጠረውን ሰው እንደ ሰው አለመቁጠር…፡፡ ዛሬ ግን በዚህ በበረከት ወቅት እና በጸጋ ጊዜ ከአምላካችን ጋር በጸሎት እየተነጋገርን የማጽዳቱን ሥራ የዕለት ተዕለት ተግባራቸህን ሊሆን ይገባል፡፡
ያኔ መቅደሱን ከነጋዴዎች ያጸዳው ክርስቶስ ዛሬ እያንዳንዳችንን «ልብህን ያ እኔና አንተ ከምናውቀው ኃጢአት አንጻው ምክንያቱም በጸሎት ወደኔ በምትቀርብበት ሰዓት፣ እኔም በምስጢራት ወዳንተ ስመጣ ማረፊያዬ ነህና» ይላል፡፡ በብዙ ግሳንግስ የተሞላ ልብ ግን ልክ እንደሚቆረቁር መኝታ ወይም እንደ ድንጋይ መቀመጫ ነው፡፡ ይህ ዓይነት ልብ ክርስቶስን ያኔ ጨካኞቹ በመስቀል ሲቸነክሩት በራሱ ላይ ከደፉበት የእሾህ አክሊል የበለጠ እየወጋጋ ያሳምመዋል፡፡ ታዲያ ዛሬ ክርስቶስ «መቅደስ» እንዲሆን በመረጠው ልብ ውስጥ ስንት ንግድ ይካሄድ ይሆን? ስንት የክፋት መደብሮችና የግፍ ሱቆች፣ ስንት ነገር የሚሰራባቸው ፋብሪካዎችና የተንኮል ማከፋፈያዎች ይኖራሉ? ዛሬም ሁኔታችንን፣ የአምልኳችንንና የእምነታችንን ደካማነት ልማዳዊነትና ለታይታ የምናደርገውን ሁሉ ሲመለከት ይህ ጌታ ያዝናል፣ «እኔ የሕይወት ዋጋ የከፈልኩላትን ነፍስ፣ እንደ መቅደስ የቆጠርኳትን አካል እንዴት የነዚህ ሁሉ ማስተናገጃ አደረጋችኋት» እንደሚልም አይጠረጠርም፡፡ እንግዲህ መንጻት የሚሻ ካለ እንደ መዝሙረኛው ዳዊት ወደርሱ ቀርቦ «ትነዝሐኒ በአዛብ ወእነጽህ ተሐጽበኒ ወእምበረድ እጸዐዱ (በሂሶጵ እርጨኝ እነፃማለሁ፣ እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ)» በማለት ምልጃውን ያቅርብ (መዝ. 50፡7)፡፡

ሰላም ወሠናይ
አባ ዳዊት ወርቁ
ዘማኅበረ ካፑቺን








All the contents on this site are copyrighted ©.