2013-03-11 11:48:16

ሰንበት ዘወረደ (ዘድራር ጾም) መጋቢት 10/2005 (3/10/13)


መዝሙር፡ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሓት. . . . .
ንባባት፡ ዕብ 13፡7~17፥ ያዕ 4፡6~ፍ፥ ግ.ሓ. 25፡13~ፍ፥ ማቴ 6፡1~19
ምስባክ፡ ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት፥ ወተሓሰዩ ሎቱ በርዓድ፥ አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዐዕ እግዚአብሔር። መዝ. 2፡11።
የፆም የመጀመሪያ ሳምንት
ዛሬ የምንጀምረውን ዓቢይ ፆም መዝሙረኛው ዳዊት «ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ» በማለት ያውጀዋል፡፡ በዛሬው አስተምሕሮ በፈጣሪያችን መልካም ፈቃድና ቸርነት «ፈሪሃ እግዚአብሔር» ምን ማለት እንደሆነ እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔርን መፍራት ማለት ከተራ ፍርሃት የተለየ ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ታሪክ ፍርሃት ወደ ሰው ሕይወት (ወደ ሰው ታሪክ) የገባው አዳም ትእዛዝ አፍርሶ ከአምላኩ ሸሽቶ በተሸሸገ ጊዜ ነው (ዘፍ፡ 3፡10-11)፡፡ ወደ ትክክለኛው ትርጉም ስንመጣ ደግሞ እግዚአብሔርን መፍራት ሁለት ነገሮችን አጣምሮ የያዘ ነው፡ «ፍቅር እና አክብሮት»፤ በሌላ አባባል «ፍቅር የተሞላበት አክብሮት ፤ አክብሮት የተሞላበት ፍቅር» ማለት ነው፡፡ አንድን ሰው ከአክብሮት የተነሳ መፍራት ማለት ያንን ሰው መውደድም ማክበርም ማለት ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ሰውን አለማክበር ማለት አለመውደድ ማለት ነው፣ አክብሮት በሌለበት ፍቅር የለምና፡፡ በጋብቻ ፣ በቤተሰብ ውስጥ ፣ በስራ ቦታ ፣ መከባበር ከሌለ ፍቅር የለም ፡፡ በልባችን ውስጥ ጥላቻና ቂም ካለ ፈሪሃ እግዚአብሔር የለንም ፣ በባልንጀራችን ላይ ነገር የምንሰራበት ከሆነ እግዚአብሔርን አንፈራም ማለት ነው ፣ በጠላትነት የምንነሳሳ ከሆነ ፈሪሃ እግዚአብሔር የለንም ፣ ፍትሕ የምናጓድል ከሆነ ፣ ጉቦ የምንበላ ከሆነ ፣ ወላጅ አልባውን ፣ ድኻ አደጉን ፣ መበለቷን ፣ አቅመ ደካማውን የምንገፋ ከሆነ እግዚአብሔርን አንፈራም ማለት ነው ፤ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ይቅር የማንል ከሆነ እግዚአብሔርን ጨርሶ አንፈራም ማለት ነው ፤ ልባችን ለፍቅር ካልተከፈተ እግዚአብሔርን አንፈራም ሰውንም አናከብርም ማለት ነው ምክንያቱም መዝሙሩ «ንጹም ጾመ ወናፈቅር ቢጸነ ወንትፋቀር በበይናቲነ (ጾምን እንጹም ባልንጀራችንንም እንውደድ)» ብሎታልና ፡፡ እንግዲህ አንድ ሰው እግዚአብሔርን እፈራለሁ ሲል እሱን ለመታዘዝና ደስ ለማሰኘት መርጧል ማለት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ምርጫ በየዕለቱ እያደገ የሚሄድና ልብን ጥልቅ በሆነው በእግዚአብሔር ፍቅር የሚሞላ ነው ፡፡ እግዚአብሔርን የመፍራት ጉዳይ ከተራ መንቀጥቀጥ ጋር ካመሳሰልነው ግን ባዶ ፍቅር እንዲሁም ፍቅር አልባ ክብር ይሆናል፡፡ ሁለቱ ሲዋሃዱ ግን ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲያድርብን ያደርጋሉ፡፡ እግዚአብሔርም በእንዲህ ዓይነት የሚፈሩትን አብዝቶ ይባርካቸዋል ቸርነቱም ይበዛላቸዋል (መዝ. 146(147)፡11፤ 114(115)፡13 ምሳሌ 14፡26)፡፡ አንዳንዴ በሌሎች ሰዎች ስኬት፣ በተለይ በእኛ ፍርድ መሰረት እግዚአብሔርን የማያውቁም ሆነ የማይፈሩ ኑሮ የተስተካከለላቸው መስሎ ሲታየን እንቀናለን፤ እንዴት እኔ በየቀኑ እያስቀደስኩ ፣ እየጸለይኩ ሳይሆንልኝ እነሱ ግን… ወደ ማለቱ ጥርጣሬ እንገባለን፡፡ ቃለ እግዚአብሔር ለዚህም መልስ አለው «ልብህ በኃጢአተኞች አይቅና፤ ነገር ግን ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር፣ በእውነት ፍጻሜ አለህ፣ ተስፋህም አይጠፋምና» (ምሳሌ 23፡17-18)፡፡ እንግዲህ ፈሪሃ እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ የምንጠበቅበት ኃይላችን እንደሆነ እንወቅ አንረዳም፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ እንዳለው የእግዚአብሔር መልካምነትም አይለየንም (ኤር. 32፡40-41)፡፡
ሠላም ወሰናይ
አባ ዳዊት ወረቁ
ዘማኅበረ ካፑቺን
RealAudioMP3







All the contents on this site are copyrighted ©.