2013-03-07 08:49:24

የኩላዊት ቤተ ክርስቲያን የትምህርተ ክርስቶስ መዝገብ


RealAudioMP3 የካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን የትምህርተ ክርስቶስ መዝገበ ሃይማኖት ዝክረ 20ኛው ዓመት ምክንያት የቫቲካን ረዲዮ በተከታታይ በኢየሱሳውያን ማኅበር አባል የሥነ አቢያተ ክርስትያን ጉባኤና የቲዮሎጊያ ሊቅ አባ ዳርዩስ ኮዋልዝይክ አማካኝነት ሳምንታዊ ዕለተ ማክሰኞ የሚያቀረብው አስተምህሮ በመቀጠል ትላትና አባ ኮዋልዝይክ፦ በአንድ እግዚአብሔር ‘አብ’ አምናለሁ” በሚል ርእስ ሥር 17ኛው ክፍለ አስተምህሮ ሲያቀርቡ እንዳመለከቱት፦ ‘በእግዚአብሔር አብ አምናለሁ’ በማለት ተአምኖተ ሃይማኖት ስንደግም የእዚአብሔር አባትነቱን እንናዘዛለን። ለምን እግዚአብሔር አብ ብለን እንጠራዋለን? በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር አብ ተብሎ እንደሚጠራ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የትምህርተ ክርስቶስ መዝገብ ይገልጥልናል፣ አብ የሚል መጠሪያም ፈጣሪነቱን እርሱም ፈጣሬ ኵሉ መሆኑና እንዲሁም የአባትነቱ ቅዋሜ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያጸናው ቃል ኪዳን ነው። መሎኮታዊ አብነት የሁሉም አናሥርና ወደር የለሽነቱ በሌላው ረገድም ለሰው ልጅ ፍቅር የሚያሳስብ የሚያነቃቃ ነው። (የትምህርተ ክርስቶስ መዝገብ ቍ. 238-239 ተመልከት)”።
ከሁሉም በፊት እኛ እግዚአብሔርን አባታችን ሆይ ብለን እንጠራዋለን፦ “ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አባትነቱን ‘…ሁሉም ከአባቴ ዘንድ ተሰጠኝ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቀው የለም፣ አብንም ከወልድ በቀር፣ ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር የሚያውቀው የለም’ (ማቴ. 11.27)፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ዘለአለማዊ አብነት ገልጦልናል፣ ገዛ እራሱንም ከአብ በዘለዓለማዊነት የተወለደ መሆኑ በመግለጥ እኛ የዚህ መለኮታዊ ባህርይ ተካፋዮች አድርጎናል፣ ‘የመለኰታዊ ባህርይ ተካፋዮች አድርጎናል’ (2ጴጥ. 1 ቍ.4)። እግዚአብሔር ዘለአለማዊ አባት መሆኑ ኢየሱስ ገዛ እራሱ በዘለዓለማዊነት የተፈጠረ የነበረ ቀጥሎም በአብና በወልድ መካከል ያለው ዘለዓለማዊ ፍቅር የሆነውን መንፈስ ቅዱስን ገልጦልናል።”
“በሌላው ረገድም ኢየሱስ ለሰው ልጅ የገለጠውን ዘለዓለማዊ መለኰታዊ አባትነት በዘፍጥረት ላይ ብቻ እንዳልሆነና ይኽ በቅድሚያ የመለኰታዊ ባህርይ ተካፋዮች እንድንሆን መፈጠራችን ባለው እቅድ ላይ የሚገለጥ ነው (2ጴጥ. 1.4)። ምድራዊው አባት ለልጁ ሰብአዊ ባህርይ ይሰጣል፣ ዘለዓለማዊው አባት የመለኰታዊ ባህርይ ተካፋዮች ያደርጋል። ይኽ ለእኛ የምሥራች ወይንም አዲስ ዜና ነው። ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚያረጋግጠውም፦ ‘እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆን ወራሾቹ ነን፣ የእግዚአብሔር ወራሾች ከሆንም የክርስቶስ ወራሾቹ ነን’ (ሮሜ. 8 ቍ.17)፣ የክብሩ ተካፋዮች ለመሆን የተጠራን ነን” ብለዋል።
“የእግዚአብሔር አባትነት ወይንም አብ-ነት ከተባዕት ፆታ ጋር ምንም የሚያዛምደው ነገር የለም፣ እግዚአብሔር አብ ለመሆኑ የተባዕት ፆታ መመዘኛው አይደለም ወይንም አመክንዮ ሊሆነውም አይችልም። የአባትነቱ ባህርይ ተባዕት ፆታ ላይ የጸና አይደለም። በአባትነቱ እናትነቱንም ጭምር ተጠቃሎ ይገኛል። ር.ሊ.ጳ. ብፁዕ ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፦ በወንጌል የሚገለጠው ጠፍቶ የተገኘው ልጅ ምሳሌ መሠረት በማድረግ ሲተነትኑ ‘በዚህ ምሳሌ የሚገለጠው የእግዚአብሔር መሃሪነት እውነተኛውና የማያማታው በሰብአዊ ፍጥረት ዘንድ ያለው አባትነትና እናትነትን ልቆ የሚሄድ ነው” ያሉትን በመጥቀስ ያቀረቡትን አስተምህሮ አጠቃለዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.