2013-02-18 15:18:15

የዓቢይ ጾም ሱባኤ


RealAudioMP3 ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ ከመላ የቅርብ ተባባሪዎቻቸው የቅድስት መንበር የበላይ ብፁዓን ካርዲናላትና ብፁዓን ጳጳሳት በጋራ በመሆን የሚሳተፉበት የባህል ጉዳይ ተንከባካቢ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር ብፁዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ በሰባኪነት የሚመሩት እ.ኤ.አ. እፊታችን የካቲት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. የሚጠቃለለው ሱባኤ ትላትና በሮማ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ ስድስት ሰዓት በይፋ መጀመሩ ሲገለጥ፣ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ትላንትና እኩለ ቀን በአጸደ ቅዱስ ጴጥሮስ ጸሎት መልአከ እግዚአብሔር ከመምራታቸው ቀደም በማድረግ ባሰሙት ስብከት እንዳስታወሱትም ይኽ በሐዋርያዊ መንበር በሚገኘው እመ መድኅኔ ዓለም ቤተ ጸሎት የሚካሄደው ሱባኤ ቅዱስነታቸው በቅዱስ ጴጥሮስ ተከታይነት ሥልጣናቸው የሚሳተፉበት የመጨረሻ ሱባኤ መሆኑ እንደገለጡ ለማወቅ ተችለዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ ከቫቲካን ረዲዮ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ እንዳመለከቱት የዚህ የሚመሩት የዓቢይ ጾም ሱባኤ ርእስ፦ “Ars orandi, ars credendi. Il volto di Dio e il volto dell’uomo nella preghiera salmica-የጸሎት ሥነ ጥበብና የእምነት ሥነ ጥበብ፣ በመዝሙረ ዳዊት ዘንድ የእግዚአብሔርና የሰው ልጅ ምስል” በማለት እንደሰየሙት ገልጠው፣ የሱባኤው ርእስና ይዞታ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በእድሜ መግፋት ምክንያት ቅዱስ ጴጥሮሳዊ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ ከወሰዱት ውሳኔ በፊት ያዘጋጁት ቢሆንም ቅሉ ብዙ ለውጥ እንደማይኖረው ነው ካሉ በኋላ፣ በሱባኤው መግቢያ ልዩ የሰላምታ ቃል እንዳከሉበትና የቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16 ምስል በቤተ ክርስቲያን መጻኢ የጸላይ የአስተንታኝ አድማስ እንደሚሆን የሚያስተጋባ ነው ብለዋል።
ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በቅዱስ ጴጥሮሳዊ መሪነታቸው ሥር ከኢአማንያንና ከአማንያን ምሁራንና ሊቃውንት ጋር እምነት በማስደገፍ ውይይት እንዲካሄድ በማሳሰብ ያስጀመሩት “Cortile dei Gentili -የአሕዛብ ቅጥር ግቢ” በሚል ርእስ ሥር የባህል ጉዳይ በሚከታተለው ጳጳሳዊ ምክር ቤት አማካኝነት እንዲመራ ያነቃቁት ዓውደ ጥናት በማስታወስ በእውነቱ ይኽ አንዱ በባህል ጉዳይ በልዩ የሚታወሱበት መርሃ ግብር ነው። በአሁኑ ወቅት እሴቶች ደብዝዘውና ለወቅታዊው ዓለም የሚሉት እንደሌላቸው ተደርገው ማመን አለ ማመን ያው ነው በሚለው ተዛማጅ ባህል ሥር እየተገለጡ ባለበት ወቅት፣ እምነትና አእምሮ ወይንም ባህል በማወያየት መሠረታዊ ኅልውናቸው ለማስተጋባት እንዲሁም በእምነትና በሥነ ጥበብ መካከል ያለው ተወያይነት ለማረጋገጥ ያለመ መርሃ ግብር ነው። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ከውእነት ጋር ብቻ ሳይሆን በውበትና በእምነት መካከል ያለው ተወያይነት ዳግም ለማስተጋባት ያነቃቃት ውሳኔ መሆኑ አብራርተው፣ ባህል በቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ጴጥሮሳዊ መሪነት ያለው አቢይ ሥፍራ የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
ከባህል ከሥነ ምርምር እንዲሁም ከወጣት ትውልድ ጋር የሚደረገው ውይይት በዚህ ዓለም በተለይ በሥነ አኃዝ በተራቀቀው የመገናኛ ብዙሃን ባህል በተስፋፋበትና በሚከተሉበት በአሁኑ ወቅት ከዚህ የወጣት አዲስ ባህል ጋር በመቀራረብ ቋንቋውን ጠንቅቆ በማወቅ፣ ከእርሱ ጋር ለመወያየት ቅዱስ አባታችን ያነቃቁት መርሃ ግብር በልዩ የሚታወሱበት አጋጣሚ ነው። እምነትና ሃይማኖት በትክክል በማስረዳት በሐዋርያዊ ግብረ ኖልዎ ሥር ኵላዊት ቤተ ክርስቲያን ለወጣት ትውልድ በማስተማር ከባህሎች ጋር ከሥነ ምርምር ጋር የምታከናውነው ውይይት የኵላዊት ቤተ ክርስቲያን አንዱ የሐዋርያዊ ግብረ ኖልዎ እቅድ እንዲሆን አድርገዋል በማለት የሰጡትን ቃለ ምልልስ አጠቃለዋል።







All the contents on this site are copyrighted ©.