2013-02-06 16:29:28

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ


ውድ ወንድሞችና እኅቶች፧ እግዚአብሔርን ሁሉን የሚችል ብሎ የሚገልጠው ጸሎተ ሃይማኖትን ባለፈው ሳምንት አስተንትነናል፣ ከዛ በመቀጠል “ሰማይና ምድርን የፈጠረ” በማለት ቅዱስ መጽሐፍ በመጀመርያ የተጠቀመውን ቃል እንደገና ይደግማል፣ በቅዱስ መጽሓፍ መጀመርያ ላይ የመጀመርያው ኍልቍ “እግዚአብሔር በመጀመርያ ሰማይና ምድርን ፈጠረ” (ዘፍ 1፤1) ይላል፣ እግዚአብሔር የሁሉ ምንጭ ነው፤ በፍጥረቱ መልካምነትም የአፍቃሪ አባት ከሃሌ ኵሉነት ይገለጣል፣
እግዚአብሔር በፍጥረት እንደ አባት ይገለጣል፣ በፍጥረት የሕይወት ምንጭ በመሆኑም ከሃሌ ኵሉነቱን ይገልጣል፣ ይህንን ለመግለጥ ቅዱስ መጽሓፍ የሚጠቀማቸው ምሳሌዎች ብዙ ናቸው፤ (ኢሳ 40፤12፣ 45፤18፣ 48፤13፣ መዝ 104፤2.5፣ 135፤7፣ ምሳ 8፤27-29፣ ኢዮ 38-39 መመልከት ይቻላል)፣ እግዚአብሔር እንደ መልካምና ሁሉ ቻይ አባት የፈጠረውን ሁሉ በፍቅርና በማይጐድል ታማኝነት ይንከባከባል (መዝ 57፤11፣ 108፤5፣ 36፤6)፣ መዝሙረ ዳዊት እየደጋገመ ይህንን ይነግረናል፣ በዚህም ፍጥረት የእግዚአብሔርን ከሃሌ ኵሉነትና መልካምነትን ደጋግመን የምናውቅበት ቦታ ይሆናል፤ እንዲሁም የእኛ የአማኞች ኅሊናን እየቀሰቀሰ እግዚአብሔር ፈጣሪ ነው ብለን እንድናውጅ ያደርገናል፣ የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ “ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን” (11፤3) ብሎ ጽፈዋል፣ ስለዚህ እምነት የሚታየው ዓለም በመመልከት የማይታየውን እግዚአብሔር ለማወቅ ያስችለናል፣ አማኙ ታላቁን የተፈጥሮ መጽሐፍ ለማንበብና ቋንቋውን ሊረዳ ይችላል (መዝ 19፤2-5)፣ ሆኖም ግን ይህ ብቻ አይበቃም እምነት የሚሰጠው ገላጩ ቃለ እግዚአብሔር ያስፈልገናል፣ የሰው ልጅ በዚሁ ቃል እግዚአብሔር እንደ ፈጣሪና አባት የፈጠራቸውን ነገሮች እውነተኛና ሙሉ እውቀት ሊያገኝ ይችላል፣ በቅዱስ መጽሐፍ የሰው ልጅ አእምሮ በእምነት ብርሃን ተረድቶ የተፈጠረ ዓለም ምሥጢር ለመረዳት ይችላል፣ በተለይ የኦሪት ዘፍጥረት አንደኛ ምዕራፍ የእግዚአብሔር መለኮታዊና ፈጣሪ ኃይል በሰባት ቀኖች ሲገለጽ ልዩ ቦታ አለው፣ እግዚአብሔር በስድስት ቀን ፍጥረት ሁሉን ፈጸመ በሰባተኛው ቀን በሰንበት ከሁሉም ሥራው ዓረፈ፣ ይህ ዕለት ለሁላችን የነጻነት ዕለት ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የምንሆንበት ዕለት በዚህም በኦሪት ዘፍጥረት ምሳሌ የመጀመርያው አሳባችን ለእግዚአብሔር የፍቅር ሥራ በማሰብ በፍቅር እንድንመልሰው ይሁን፣ ሁለተኛ አሳብ ደግሞ ከእግዚአብሔር የፍቅር ፍጥረት ጋር የሚዋሃድ ዓለም መፍጠር ላይ ነው፤ ይህም ፍጥረት ለእግዚአብሔር በፍቅር ይመልሳል፣ ይህ ፍጥረት ምንኛ ያህል መልካም እንደነበረ ለማመልከት በኦርት ዘፍጥረት ስድስት ጊዜ “እግዚአብሔር ሁሉ መልካም እንደሆነ አየ” የሚል ሓረግ ተደጋግሞ እናገኛለን (4፤10.12.18.21.25)፣ ይህንን ለማገባደድ ደግሞ በሰባተኛው ቀን ከሰው ልጅ ፍጥረት በኋላ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ ተመለከተ እነሆም ሁሉ እጅግ መልካም ነበር” (31) ይላል፣ እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ ቆንጆና መልካም ሆኖ በጥበብና በፍቅር የሞላ ነው፣ የእግዚአብሔር ፈጣሪ ተግባር ሥርዓት ያመጣል ውህደት ይሰጣል ቍንጅናም ይሰጣል፣ በኦሪት ዘፍጥረት ሌላ ጎልቶ የሚታየው ደግሞ እግዚአብሔር ሁሉን በቃሉ ይፈጥራል ለአሥር ጊዜ ያህል “እግዚአብሔር ይሁን አለ”( 3.6.9.11.14.20.24.26.28.29)፣ ቃሉም የእግዚአብሔር ቃል ሆኖ የዓለምና የሁሉ ነገር መሠረት ነው፤ እግዚአብሔር ተናገረ እንደቃሉም ሁሉ ተፈጠሩ፣ ይህም የእግዚአብሔር መለኮታዊ ቃል ችሎታን ያመለክታል፣ ዳዊትም “እግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ፤ … እርሱ ተናግሮአልና፥ ሆኑም፤ እርሱ አዘዘ፥ ጸኑም።”(መዝ 33፤6.9) ብሎ ይዘምራል፣ ሕይወት ብቅ አለች ዓለምም እንድትኖር ሆነ ይህም የሆነበት ምክንያት ሁሉም ለመለኮታዊው ቃል ስለታዘዙ ነው፣
ሆኖም ግን ዛሬ በሳይንስና በተክኖሎጂ ዘመናችን ስለፍጥረት መናገር ትርጉም ይኖረዋልን፧ የኦሪት ዘፍጥረት ትረካን እንዴት ልንረዳው እንችላለን፧ የሚል ጥያቄ አለ፣ ቅዱስ መጽሐፍ የባህርያዊ ሳይንስ መጽሓፍ ሊሆን አይችልም ሆኖም ግን የነገሮች ሁሉ እውነተኛውና ጥልቁን ሓቅ ሊያስረዳን ስለፈለገ ነው፣ ኦሪት ዘፍጥረት የሚያቀርበልን መሠረታዊ ሓቅ ዓለምና በእርስዋ ውስጥ የሚገኙ ነገሮች እርስ በእርስ የሚቃረኑ ኃይሎች ያከማቹት ሳይሆን መሠረቱንና ጽናቱን ከዘለዓለማዊ የእግዚአብሔር መሪነት ከእርሱ ቃል ያገኛል፣ ገናም መላው ፍጥረትን መታደጉን ይቀጥላል፣ ከዚሁ ከእግዚአብሔር አሳብ ከፈጣሪው መንፈስ የሚወለድ ለዓለም አንድ ዕቅድ አለ፣ በእያንዳንዱ ፍጡር መሠረት ይህ እንዳለ ማመን የኑሮ ትርጉምን ለመረዳት ኅልናችን ያበራል ሕይወትን በመተማመንና በተስፋ ለመምራትም ብርታት ይሰጣል፣ ስለዚህ ቅዱስ መጽሐፍ የዓለማችን ኅልውና እና የገዛ ራሳችን ምንጭ የዕድል ጉዳይ ወይንም የአጋጣሚ ጉዳይ ሳይሆን ዓላማ ፍቅርና ነጻነት እንዳለው ይነግረናል፣ በዕድል ወይንም በገዛ ራሱ ለሚለው አስተሳሰብ የእኛ መልስ ይህ ነው፤ እኛም በዚሁ እናምናለን፤ (ይቀጥላል)








All the contents on this site are copyrighted ©.