2013-01-03 18:00:10

የር.ሊ.ጳ ሳምታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ!


የጌታችን መድኃኒታችን ልደት አሁንም እንደገና ተስፋና ደስታ ይዞልን በመምጣት በዓለማችንና በልባችን እያንዣበበ ያለውን ጨለማ ለማባረር ብርሃኑ እያንሸባረቀ ነው፣ ይህ ብርሃን ከየት ይመጣል ብለን የጠየቅን እንደሆነ መልሱ በዛው በቤተ ልሔም ግርግም ያ እረኞች “ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ ያገኙበት” ግርግም ነው፣ በዚሁ አጋጣሚ በቅድስት ቤተ ሰብ ዙርያ ሌላ ጠለቅ ያለ ጥያቄ መቅረብ ይቻላል፣ አንድ ትንሽና ደካማ ሕጻን የዓለምን ታሪክ ሊለውጥ የሚችል ሥር ነቀላዊ አዲስ ዜና እንዴት ሊያመጣ ይችላል፣ መሠረቱ ከዛ ግርግም ወዲያ የሆነ ሌላ ምሥጢራዊ ኃይል ይኖር ይሆናልን ብለን ስንጠይቅ፣ ሁሉ ያ ጲላጦስ ጴንጠናዊ በፍርድ ጊዜ ለኢየሱስ ያቀረበው ጥያቄ “ከየት ነህ አንተ” (ዮሐ 19፤29) ለእኛም ሁሌ እንደገና በመመለስ የኢየሱስ መሠረት ምንጭ ለማወቅ እንመራመራለን፣ በዮሐንስ ወንጌል “እኔ ከሰማይ የወረድሁ ኅብስት ነኝ” ባለ ጊዜ አይሁድ “ስለ እርሱ አንጐራጐሩና። አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ። ከሰማይ ወርጃለሁ እንዴት ይላል? አሉ።” (ዮሐ 6፤42) ከዚህ ንግግር በኋላ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የኢየሱስ መሲህነትን በኃይል ሊቋቋሙ ጀምረዋል እርስ በእርሳቸውም “ይህን ከወዴት እንደ ሆነ አውቀናል፤ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም” (ዮሐ 7፤27) በማለትም ተችተዋል፣ ኢየሱስ ገዛ ራሱ የእርሱን ከወዴት መምጣት ማወቅ ብቻው በቂ እንዳለሆነ ሲገልጥ “እኔንም ታውቁኛላችሁ ከወዴትም እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እኔም በራሴ አልመጣሁም ነገር ግን እናንተ የማታውቁት የላከኝ እውነተኛ ነው፤” (ዮሐ 7፤28) ይላል፣ እውነት ኢየሱስ ከናዝሬት ከተማ ነው በቤተልሔምም ተወለደ ነገር ግን ስለ እውነተኛው ምንጩ ምን ይታወቃል፧
ኢየሱስ ከየት ነው ለሚለው ጥያቄ በአራቱ ወንጌላት ጥርት ያለ መልስ ይገኛል፣ እውነተኛ ምንጩ እግዚአብሔር አብ ነው ይላል፣ እርሱ በአጠቃላይ ከእግዚአብሔር አብ ነው የመጣው ነገር ከሌሎች ነቢያትና የእግዚአብሔር መል እክተኞች ልዩ በሆነ መንገድ ነው የመጣው፣ ይህንን የእግዚአብሔር ምሥጢራዊ ምንጭ ማንም አያወቀውም፤ በዚሁ ዘመነ ልደት የምናነባቸው የማቴዎስና የሉቃስ ወንጌሎች ስለኢየሱስ ሕጻንነት በሚተርኩት ይገኛል፣ መል አኩ ገብር ኤል ለእመቤታችን ድንግል ማርያም ሲያበስራት “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” (ሉቃ 1፤35) ይላታል፣ እነኚህን ቃላት እምነታችን ለመግለጥ ጸሎተ ሃይማኖት በምንደግምበት ግዜ “ወተሰብአ ወተሠገወ እመንፈስ ቅዱስ እማርያም እም ቅድስት ድንግል ኮነ ብእሴ” በማለት እንደግማቸዋለን፣ እነኚህን ቃላት ስንደግም ራሳችንን ዝቅ በማድረግ እንሰግዳለን ምክንያቱም እግዚአብሔርን እንዳናይ ከልክሎን የነበረ መጋረጃ ተከፍተዋልና፣ የማይታየውና ሊደረስ የማይቻል እግዚአብሔር ሊጐበኘን መጣ አማኑኤል እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ፣ ቅዳሴ በምንሰማበት ጊዜ እንደ ሞዛርት ያሉ ትላልቅ ሙዚቀኞች በሙዚቃ አድማሳዊ ቋንቋ ይህንን ሲገልጡት ታላቁ የእግዚአብሔር ምሥጢር ሥጋ መልበሱንና ሰው መሆኑን አ እምሮ በማይዘልቀው ዜማ ያዘሙታል፣
“በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ስጋ ለብሶ በእመቤታችን ድንግል ማኅጸን ሰው ሆነ” የሚሉትን ቃላት ጠንቀቅ ብለን ያስተንተንን እንደሆነ አራት ሁኔታዎች ለማስተዋል እንችላለን፣ መንፈስ ቅዱስና እመቤታችን ድንግል ማርያም ይጠቀሳሉ በዚሁ ሓረግ ግን በእመቤታችን ድንግል ማርያም ማኅጸን ሥጋ ለብሶ ሰው የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ እንዳለ ግልጥ ነው፣ በጸሎተ ሃይማኖት ኢየሱስ በተለያዩ የቅጽል ስሞች እንጠረዋለን፣ በኒቅ ያውና በቍስጥንጥንያ በተደረሰው ጸሎተ ሃይማኖት ለምሳሌ “ጌታ … ክርስቶስ … አንድያ የእግዚአብሔር አብ ልጅ … አምላክ ከአምላክ ብርሃን ከብርሃን እውነተኛ አምላክ ከእውነተኛ አምላክ .. ከአባቱ ጋር በመለኮቱ እኩል የሆነ” ብለን እንጠረዋለን፣ በዚህ አግባብ እርሱ ወደ እግዚአብሔር አብ አካል እንደሚያደርሰን እናያለን፣ የዚሁ ሓረግ ባለቤት ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ አምላክ የሆነ እግዚአብሔር አብ ነው፣
ይህ የጸሎተ ሃይማኖት ዓረፍተ ነገር ስለእግዚአብሔር ዘለዓለማዊነት አይደለም የሚናገረው ነገር ግን ስለ የስላሴ አንድ ተግባር ማለት ሶስቱ መለኮታውያን አካላት የሚያደርጉት ሥራ በእመቤታችን ድንግል ማርያም እውን መሆኑን እንታመናለን፣ አለ እመቤታችን ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር በሰው ልጅ ዘር ታሪክ መግባት ግቡን ባልመታ ነበር በዚህም የእምነታችን ምስክርነት አንኳር የሆነው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር አንድ ሆነ የሚለው እውን ባልሆነም ነበር፣ እንዲህ ባለ መንገድ እመቤታችን ድንግል ማርያም በታሪካችን በመግባት በሚሠራ እግዚብሔር የእምነታችን የማይካድ ክፍል ትሆናለች፣ እርሷ ሁለመናዋን ለእግዚአብሔር ትሰጣለች፣ የእግዚአብሔር ማደርያ እንድትሆንም እሺ ትላለች፣ አንዳንዴ በእምነት ጉዞና ኑሮ ድሆች መሆናችን እና ለዓለም ለመስጠት የምንጠየቀው ምስክርነት ባዶ ሆኖ ሊሰማን ይችላል፣ ሆኖም ግን እግዚአብሔር በታላቁ የሮማውያን ግዛት ውስጥ እጅግ ርቃ በምትገኝ አውራጃ እውቅና በሌለው መንደር ትኖር የነበረች ይህችን ዝቅተኛ ሴት መርጠዋል፣ እጅግ አስቸጋሪና ደረቅ በሆነ ሁኔታ ተከበን ብንገኝም ሁሌ በእግዚአብሔር እምነት ሊኖረን ያስፈልጋል፣ ይህንን እምነት በእርሱ ህልውናና በታርካችን ጉዞ እንደ እመቤታችን ድንግል ማርያም ሁሌ ልናሳድሰው ያስፈልጋል፣ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ምንም ነገር የለም፤ ከእርሱ ጋር ከሆንን የኑሮአችን ጉዞ ሁል ግዜ ዋስትና በመላውና ለሚመጣ ጽኑ ተስፋ ክፍት በመሆን ይከናወናል፣
በጸሎተ ሃይማኖት “በመንፈስ ቅዱስ ሥራ በእመቤታችን ድንግል ማኅጸን ሥጋ ለብሶ ሰው ሆነዋል” ብለን ስንመሰክር መንፈስ ቅዱስ እንደ ል ዑል እግዚአብሔር ኃይል ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ በእመቤታችን ድንግል ማርያም እንደሰራና የእግዚአብሔር ልጅ እንደተጸነሰ እናረጋግጣለን፣ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ” (ሉቃ 1፤35) ሲል የሊቀ መላእክቱ ቅዱስ ገብር ኤል ቃላትን ያቀርብልናል፣ በዚሁ ሓረግ ሁለት ነገሮች ይገለጣሉ፣ አንደኛ በፍጥረት ጊዜ የሆነውን ያሳስባል፣ በኦሪት ዘፍጥረት መግቢያ ላይ “የእግዚአብሔር መንፈስም በውኃ ላይ ያንሳፍፍ ነበር” (1፡2) የሚል እናነባለን፤ ይህ መንፈስ ፈጣሪው መንገስ ቅዱስ ሆኖ ለሁሉም ፍጥረት እና ለሰው ልጅ ሕይወት የዘራ ነው፣ በእመቤታችን ድንግል ማርያም የሚፈጸመውም በዚሁ መለኮታዊው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ይሄው ነው ማለት አዲስ ፍጥረት፣ ካለምንም ፍጥረትን የጠራ እግዚአብሔር በምሥጢረ ሥጋዌ አዲስ የሰው ልጅ ዘር ለመጀመር ሕይወት ይሰጣል፣ የቤተ ክርስትያን አበው ክርስቶስን ብዙ ጊዜ አዲስ አዳም በማለት ይጠሩታል፣ ይህም በእግዚአብሔር ልጅ ከእመቤታችን ድንግል ማርያም መወለድ አዲስ ፍጥረት እንደጀመረ ለማስመር ብለው ነው፣ ይህ የሚያሳስበን ለእኛም እምነት እንዴት አድርጎ ህዳሴ በመስጠት ዳግም እንድንወለድ እንደሚያደርገን ነው፣ ክርስትያን ለመሆን በምንጀምርበት ጌዜ ማለትም እንደ እግዚአብሔር ልጆች እንደገና እንድንወለድ የሚያደርገንን ምሥጢረ ጥምቀት በምንቀበልበት ኢየሱስ ከአባቱ ያለውን የልጅነት ግኑኝነት ተሳታፊዎች እንደምንሆን ያደርገናል፣ ለዚህም ነው ምሥጢረ ጥምቀት ሁሌ በተገብሮ አንቀጽ “ተጠመቀ!” በማለት የሚገለጠው ይህ ማለትም ማንኛውም ሰው በገዛ ራሱ ወይንም በማንኛው ሰብ አዊ ኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሊሆን አይችልም ከእግዚአብሔር በነጻ የሚሰጠን ጸጋ ነው፣ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮማውያ በጻፈው መል እክቱ “በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል።” (ሮሜ 8፤14-16) በማለት ባሮች ሳንሆን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን የሚመሰክረው፣ እንደ እመቤታችን ድንግል ለእግዚአብሔር ሥራ ልባችንን በመክፈት እና ሕይወታችን ድገሞ እንደ በሙላት የምንተማመነው ጓደኛ በእግዚአብሔር እጅ በመተው ብቻ ነው ሁሉ ሊለወጥ የሚችለው ሕይውታችን አዲስ ትርጉምና አዲስ ገጽታ ታገኛለች ይህም የሚያፈቅርና ከቶም የማይተው አባት ልጆች ስሜትና ሁኔታ ይፈጥራል፣
ስለሁለት ነገሮች ተናግረናል፤ አንደኛው ፈጣሪው መንፈስ በውኃ ላይ የሚንሳፈፈው ነው፣ በመል አኩ ብሥራት ውስጥ ሌላ ነገርም አለ፣ መል አኩ ለእመቤታችን ማርያም “የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል “ ይላታል፣ ይህ በኦሪት ዘጸአት እስራኤላውያን ከግብጽ ሲወጡ በሲና ተራራ እና ሕዝበ እስራኤል ይዞት ይጓዝ በነበረው የእግዚአብሔርን እዛ መኖር በሚያመልክት ታቦተ ኦሪት በሚገኝበት ድንኳን ያንዣዣበበውን ደመና ያመለክታል (ኦሪ ዘጸ 40፤40፣ 34-38 ተመልከት)፣ ስለዚህ እመቤታችን ድንግል ማርያም አዲሱ ቅዱስ ድንኳን አዲሱ የዕርቅ ታቦተ ኪዳን ናት፣ ሊቀ መል አኩ ለተናገራት እሺ ብላ በመቀበልዋ እግዚአኤብሔር በዚህ ዓለም ማደርያ ያገኛል፣ ዓለም ሊሸከመው ያልተቻለውን የእመቤታችን ድንግል ማርያም ማሕጸን ማደርያ ሆነለት፣
ስለዚህ ትምህርቱን ስንጀምር ወደ ጠየቅነው ጥያቄ እንመለስ፣ ጲላጦስ እንዳለው ኢየሱስ ከየት ነው፣ እላይ ከዘረዘርናቸው አስተንትኖዎች ወንጌላውያን ከመጀመርያው አንስተው የኢየሱስ እውነተኛ ምንጭ ማን መሆኑን ይነግሩናል፣ እርሱ አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፣ እርሱ ከእግዚአብሔር ይመጣል፣ በዚሁ ጊዜ በምናከበረው የልደት ዘመን እንገኛለን፣ እጅግ ታላቅና የሚያስገርም ምስጢር ነው፣ የእግዚአብሔር ልጅ በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ሥጋ ሆኖ በእመቤታችን ድንግል ማርያም ማሕጸን ሰው ሆነ፣ ይህ የምሥራች ዜና በልቦቻችን ተስፋና ደስታ እያመጣ ሁሌ እየታደሰ ይኖራል፣ ምክንያቱም ምንም እንኳ ደካማዎች ድሃዎችና በዓለም በሚገኙ ችግሮችና ጥፋቶች ምንም ማድረግ የማንችል ሆኖ ቢሰማን የእግዚአብሔር ችሎታ ሁሌ እየሠራ ነው፣ በደካማነት አድርጎ አስደናቂ ነገሮችን ያደርጋል፣ የእርሱ ጸጋ ኃይላችን ነው፣ (2ቆሮ 12፤9-10)








All the contents on this site are copyrighted ©.