2012-12-19 14:39:12

የኵላዊት ቤተ ክርስትያን የትምህርተ ክርስቶስ መዝገብ


RealAudioMP3 ዝክረ 20ኛው ዓመት እየተከበረ ያለው የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የትምህርተ ክርስቶስ መዝገብ ርእስ ሥር የቫቲካን ረዲዮ በኢየሱሳውያን ማኅበር አባል የሥነ አቢያተ ክርስቲያን ጉባኤዎችና የቲዮሎጊያ ሊቅ አባ ዳሪዩስዝ ኮዋልዝይክ የተመራ የሚያቀርበው ተከታታይ የሥርጭት መርሃ ግብር በመቀጠል ትላትና፦ “ኢየሱስ ቅዱስ መጽሐፍ የሚተነትን ቁልፍ ነው” በሚል መሪ ሃሳብ አስደግፈው፣ “የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ግንዛቤ የግል ጥረት የሚያስግኘው ውጤት ሳይሆን፣ ከቤተ ክርስቲያን ሥልጣናዊ ትምህርት ጋር የሚዛመድና የሚመሰካከር መሆን አለበት፣ ካለ ሥልጣናዊ ትምህርተ ቤተ ክርስቲያን ግንዛቤው ሙላት አይኖረውም” በማለት ይኸንን አገላለጥ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የትምህርተ ክርስቶስ መዝገብ ሥር በማቅረብ በግልጸትና ግልጸት በማስተላለፉ ተግባር መካከል ያለው ግኑኝነት ቁ. 80 ዋቢ በማድረግ፦ “በትውፊትና በመጽሐፍ ቅዱስ መካከል ያለው ትስስር” መለኮታዊ ግልጸት የማስተላለፉ ተግባር በሁለት መንገድ ይረጋገጣል፣ እርሱን በትውፊትና በቅዱስ መጽሐፍ” መሆኑ አብራርተው፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መዝገበ ሃይማኖት እንደሚያስተምረውም፦”ቅዱስ ትውፊትና መጽሐፍ ቅዱስ በጥብቅ የተሳሰሩ በመሆናቸው አንዱ ከሌላኛው ጋር ይናበባሉ። ሁለቱም ከአንድ መለኮታዊ ምንጭ የሚፈሱ በመሆናቸውም አንድን ነገር ለማሳየት በሆነ ቅርጽ በኅብረት ብቅ ብለው ወደ አንድ ግብ በአንድነት ይመራሉ” የሚለው በመጥቀስ አረጋግጠዋል።
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ መጽሐፍ ለእምነት የበላይ መመሪያ እንደሆነ ታምንበታለች ታስተምራለችም፣ ስለዚህ “ጥልቅ የሃይማኖት መጽሐፍ ብቻ አይደለም፣ ይኽም በእግዚአብሔር አነሳሽነት በመንፈስ ቅዱስ አስተንፍሶ የተጻፈ ነው። ስለዚህ ስለ ድኅነታችን በተመለከተ የሚናገረው ሁሉ ከማንኛውም ስኅተት ቁጡብና የታቀበም ነው። አንዳንድ ታሪካዊና መልክአ ምድራዊ ትክክለኛነት የማያረጋግጡ አብነት ሊገኝበት ይችል ይሆናል፣ ይኽም ከደራስያን ሰብአዊ ውስንነት ምክንያት የሚያጋጥም ነው። እግዚአብሔር ድኅነታችን ፍጻሜ በተመለከተ ካለ ምንም ስኅተት ግልጽ አድርጎልናል” ብለዋል።
በመጽሐፍ ቅዱስ በሰው ልጅ ቋንቋ የተጻፈው እውነተኛው የእግዚአብሔር ቃል ሰፍሮበታል። ይኽም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የትምህርተ ክርስቶስ መዝገብ ቁ. 108፦ “የክርስትናው እምነት ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ሃይማኖት’ አይደለም፣ ክርስትና በእግዚአብሔር ‘ቃል’ ላይ የተመሠረተ ሃይማኖት እንደ መሆኑ፣ ‘ሥጋ የለበሰ ኅያው’ የሆነ እንጂ በጽሑፍ የተቀመጠ የማይናገር ቃል አይደለም”። ካሉ በኋላ “አዲስ ኪዳን ከሰማይ የተወረወረ መጽሐፍ ሳይሆን የቀደምት ማኅበረ ክርስትያን ስብከት ውጤት ነው። በመሆኑም በኅያው ቤተ ክርስቲያን ባህል ሥር መነበብና መፈታት አለበት” ይህ እውነት ቅዱስ መጽሐፍ በግል እናነበውም ዘንድ አያግደንምን፣ እንዳውም በግል የማንበቡ ልምድ ያነቃቃል ያበረታታልም። ግላዊ ግንዛቤአችን ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር መጋጠም ይኖርበታል። የመጽሐፍ ቅዱስ ማእከል ኢየሱስ ነው። ሞቱና ትንሣኤው የቅዱስ ምጽሐፍ ንባብና ትርጉም ቁልፍ ናቸው” ብለዋል።
በመጨረሻ፦ መጽሐፍ ቅዱስ በግልና ከቤተ ክርስቲያን ጋር እናነበዋለን፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መዝገበ ሃይማኖት፦ ቁ. 133 ላይ “መጽሐፍ ቅዱስን አለማወቅ ክርስቶስን አለ ማወቅ ነው” በሚል የቅዱስ ሄሮኒሞስ ቃል ዋቢ በማድረግ ያረጋግጥልናል በማለት ያቀረቡትን አስተምህሮ አጠናቀዋል።







All the contents on this site are copyrighted ©.