2012-12-14 13:54:26

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ


ውድ ወንድሞችና እኅቶች፧
ባለፈው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ስለ እግዚአብሔር ስለ ገዛ ራሱና ስለ የቸርነቱና የፍቅሩ ዕቅድ ሊነግረን ስላደረገው የእግዚአብሔር ግልጸት ተናግሬ ነበር፣ ይህ የእግዚአብሔር መገለጥ በሰው ልጆች ግዜና ታሪክ ውስጥ ይገባል፣ ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እምነትና አመክንዮ “ፊደስ ኤት ራጽዮ” በሚለው ሐዋርያዊ መልእክታቸው እንደሚገልጡት፤ “ይህ ታሪክ እግዚአብሔር ስለሰው ልጆች በጎ ነገር እየሠራ መሆኑን ማየት የምንችልበት ቦታ ነው፣ ቀለል ባለ መንገድ ልናረጋግጠው በምንችልበት ቤተ ሰባዊ በሆነ አግባብ ይጎበኘናል፣ በዚህም ካለ እርሱ ምንም ልንረዳው እማንችለው የዕለታዊ ኑሮአችን ክፍል ይሆናል፣” (ቍ 12)
ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ አጠር ባለና ጥርት ባለ ሁኔታ የኢየሱስ ስብከት መክፈቻ ግዝያትን “ግዜው ደረሰ፤ የእግዚአብሔር መንግሥትም ቅርብ ነው” (ማር 1፡15) በማለት ይተርካል፣ የዓለምና የሰው ልጅ ታሪክን የሚያበራና ትርጉም የሚሰጠው በቤተ ልሔም ግርግም ማብራት ይጀምራል፣ ከጥቂት ግዝያት በኋላ በበዓለ ልደት የምናስተነትነው በኢየሱስ ክርስቶስ እውን የሚሆን ድኅነት ምሥጢር ነው፣ እግዚአብሔር በናዝራዊው ኢየሱስ ፊቱን ይገልጣል፣ የሰው ልጅንም እንዲያውቀውና እንዲከተለው ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ይጠይቀዋል፣ የእግዚአብሔር በታሪክ መገለጥና ከሰው ልጅ ጋራ የፍቅር ውይይት ግኑኝነት ሲያደርግ ለጠቅላላው የሰው ልጅ ጉዞ አዲስ ትርጉም ይሰጠዋል፣ ታሪክ ሲባል የዘመናት የዓመታት እና የቀናት መከታተል ሳይሆን የህልውና ጊዜ ሆኖ ለህልውናው ራሱ ትርጉም በመስጠት ለጽኑ ተስፋ ክፍት እንዲሆን ያደርገዋል፣
የእግዚአብሔር መገለጥ ም ዕራፎችን የት ልናነበው እንችላለን፧ የዚህ ጉዞ ፍጻሜዎች ለማወቅ ቅዱስ መጽሓፍ ቅድምያና የሚሰጠውና ባለ መብት ነው፣ በዚሁ የእምነት ዓመት ለሁላችሁም እንደገና አደራ ለማለት የምፈልገው ቅዱስ መጽሐፍን ዘወትር በእጃችሁ እንድትይዙት እንድታነቡት እንድታስተነትኑት እንዲሁም በዕለተ ሰንበት ቅዳሴ ለሚነበበው ቃለ እግዚአብሔር ልዩ ትኵረት እንድትሰጡ ደግሜ እማጠናለሁ፣ ይህ ሁሉ ለእምነታቻን ክቡር ቀለብ ነው፣
ብሉይ ኪዳንን በማንበብ እግዚአብሔር ራሱ በመረጠውና ኪዳን ከገባለት ሕዝብ ታሪክ ውስጥ እንዴት እንደገባ ለማየት እንችላለን፣ እነኚህ የጽኑ ኪዳን ግኑኝነቶች እንደማንኛው ፍጻሜ የሚያልፉና የሚረሱ ሳይሆን “ተዝካር” ሆነው የድኅነት ታሪክን ያቆማሉ፣ ሕዝበ እስራኤል ይህንን የድኅነት ታሪክ በሥርዓተ አምኮአቸው የድኅነት ፍጻሜዎቹን ደጋግመው በማክበርና በማስታወስ ዘወትር በኅሊናቸው ሕያው ሆኖ እንድሚኖር አደረጉት፣ በዚህም በኦሪት ዘፀአት እግዚብሔር ለሙሴ ታላቅ ፍጻሜ የተደረገበት ከግብጽ ባርነት ነጻ የወጡትን ጊዜ ማለት የዕብራውያን በዓለ ፋሲካን እንዲያከብር እንዲህ ሲል ያመለክተዋል፣ “ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁናችሁ፥ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ፤ ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ሆኖ ለዘላለም ታደርጉታላችሁ” (12፡14)፣ ለመላው የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር ያደረገላቸውን ማስታወስ ቀጣይ ግዴታ ይሆናል ምክንያቱም የጊዜው ጉዞ ባለፉት ዘመናት በተደረጉ ተአምሮች ተዝካር ሕያው ሆኖ ይኖራል፣ በዚህም በየዕለቱ ዝክር በማድረግ ታሪኩን ሕያው ያደርጉታል፣ በኦሪት ዘዳግም ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ ይለዋል፤ “በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት በኮሬብ በቆምህበት ቀን ዓይኖችህ ያዩትን ነገር እንዳትረሳ፥ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ ከልብህ እንዳይወድቅ ተጠንቀቅ፥ ነፍስህንም በትጋት ጠብቅ፤ ለልጆችህም ለልጅ ልጆችህም አስታውቀው” (4፡9)፣ ለእኛም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ያደረጋቸውን ነገሮች ከልባችሁ እንዳይወድቅ ተጠንቀቁ” ይለናል፣ እምነት ሁሌ ታማኝ የሆነውን እግዚአብሔርን በማግኘትና እርሱን በማስታወስ ትመገባለች፣ ታሪክን የሚመራ ሕይወትህን የምታኖረው እርግጠኛና ጽኑ መሠረት የሚያቆም እርሱ ነው፣ የዚህ የድኅነት ታሪክ ታላቅ ምሳሌ የሚሆነን እመቤታችን ድንግል ማርያም እግዚአብሔርን ከፍ በማድረግ የደረሰችው ጸሎት ተዐብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር የሚለው ጸሎት ነው፣ እመቤታችን በዚሁ ጸሎት የእግዚአብሔር ሥራ ዝክር ታደርጋለች፣ እግዚአብሔር በሕዝቡ ጉዞ ያደረገውን ተጨባጭ የምሕረት ሥራ፤ ለአብርሃምና ለትውልዱ ሁሉ ለሰጠው ተስፋ ታማኝ መሆኑን ታስታውሳለች፣ ይህ ሁሉ ሕያው ዝክርና ከመካከላችን የማይለይ የእግዚአብሔር ከእኛ ጋር መኖርን ያሳስባል (ሉቃ 1፡46-55)፣
ለእስራኤላውያን ከግብጽ መውጣት እግዚአብሔር ታላቅ ችሎታውን የገለጠበት የታሪካቸው አንኳር ነው፣ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነጻ ያወጣቸዋል፣ ይህንን ያደረገበት ምክንያት ደግሞ ወደ ምድረ ተስፋ እንዲመለሱና እርሱ ብቻ ጌታ መሆኑን አውቀው እንዲያመልኩት ነው፣ ሕዝበ እስራኤል ጉዞውን የሚጀመረው እንደሌሎች አሕዛብ የአገራቸው ነጻነት እንዲኖራቸው ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን እግዚአብሔርን በአምልኮና በሕይወታቸው እንዲያከብሩ፤ የሰው ልጅ ለእግዚአብሔር እየታዘዘ የሚኖርበትና በዓለም ውስጥ የእግዚአብሔር ህልውና የእርሱ አምልኮ የሚያርግበት ቦታ ለመፍጠር ነበር፣ ይህም ለሕዝበ እስራኤል ብቻ ሳይሆን በሌሎች አሕዛብ መካከል እንዲመሰክሩለት ነበር፣ ይህ አምልኮም እግዚአብሔር ሁሌ ከእሳቸው ጋር እንዲኖርና ሥራውም እንዳይጓደል ያደርጋል፣ እግዚአብሔር የነጻነት ዕቅዱን በታማኝነት ይይዘዋል የሰው ልጅ እርሱን እስኪያውቅና ጌታውን እያገለገለ ጌታ ለሚያደርግለት በእምነትና በፍቅር መልስ እንዲሰጥ ነው፣
ስለዚህ እግዚአብሔር ራሱን በጥንተ ፍጥረት ብቻ አይደለም የሚገልጠው፤ በታሪካችን ውስጥ ይገባል በአንድ ትንሽ ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ይገባል፤ ሕዝቡም ከሌሎች ይልቅ ብዛትም አልነበረውም ከሌሎች የበለጠ ኃይልም አልነበረውም፣ ይህ የእግዚአብሔር መገለጥ በታሪክ ይቀጥላል በኢየሱስ ክርስቶስም ፍጽማና ያገኛል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ቃለ እግዚአብሔር ነው ይህም ቃል በመጀመርያ የነበረና ሁሉም በእርሱ የተፈጠረ ሲሆን ሥጋ ለብሶ የእግዚአብሔር እውነተኛ ገጽን አሳየን፣ ሁሉ ተስፋ በኢየሱስ ተፈጸመ እግዚአብሔር ከሰው ልጅ ጋር የጀመረው ታሪክም በክርስቶስ ሙላት አገኘ፣ ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ እንደሚተርከው እስከ ኤማሁስ ይጓዙ የነበሩ የሁለቱ ሐዋርያት ታሪክ ስናነብ የኢየሱስ ክርስቶስ አካል ብሉይ ኪዳንን እንድሚያበራ እንረዳለን፣ በዚህም መላው የድኅነት ታሪክን በማብራራት የአዲሱንና የብሉይ ኪዳን ታላቅ ዕቅድ አንድነት በማረጋገጥ የዚሁ አንድነት መንገድን ያሳያል፣ ለዚህም ነው ኢየሱስ ሁሉ ጨልሞባቸው በማንቀባረር ለነበሩት ሁለቱ ሐዋርያ እግዚአብሔር የሰጠው እያንዳንዱ መፈጸሙን የሚገልጥላቸው፣ ቅዱስ ሉቃስም እንዲህ ይላል፤ “ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው” (24፡27)፣ ወንጌላዊው ሁለቱ ሐዋርያት አብሮዋቸው ይጓዝ የነበረው ኢየሱስ መሆኑን ባወቁ ግዜ የተናገሩትን የመገረም ንግግር ሲተርክ “እርስ በርሳቸውም። በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን? ተባባሉ” (ቍ 32) ይላል፣
አዲሱ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ ከቍ 54 – 64 እግዚአብሔር ክጅምሩ ደረጃ በደረጃ ራሱን እንዳሳወቀ ባጭሩ አስፍሮታል፣ ምንም እንኳ የሰው ልጅ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዘኡ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ጓደኝነት ቢያፈርሰውም እግዚአብሔር ግን ብዙ ጊዜ ኪዳኑን ለሰው ልጆች እያሳደሰ በመልአከ ሞት ሥር እንዲውድቁ አልተዋቸውም፣ በዚህም እግዚአብሔር የሰው ልጅን ከመጀመርያ አንስቶ ከእርሱ ጋር የጠበቀ ግኑኝነት እንዲኖረው ጥሪ ያቀርብለታል፣ አዲሱ ትምህርተ ክርስቶስ ከማየ አይኅ በኋላ እግዚአብሔር ከኖኅ ጋር ባደረገው ቃል ኪዳን በሰው ልጆች የሕይወት ጉዞ እንደገባና፤ አብርሃምን የብዙዎች አባት እንዲሆን ከገዛ መሬቱ እንዲወጣ እንደጠራው ይዘረዝራል፣ ከዚህ በመቀጠል እግዚአብሔር ይህን የአብርሃም ዘር ከግብጽ ነጻ በማውጣት በሙሴ አማካኝነት በደብረ ሲና ቃል ኪዳን በመግባትና አንድ አምላክ ለብቻው እርሱ መሆኑን እንዲያቁና እንዲያምለኩት ዓሠርቱ ቃላትን ሰጣቸው፣ በነቢያት ደግሞ ሕዝቡን ለድኅነት ተስፋ ይመራቸዋል፣ ዳግመ ኢሳያስን የተመለከትን እንደሆነ ሁለተኛ ጸአት ማለት እስራኤላውያን ከባቢሎን ስደት ወደ አገራቸው እንደተመለሱና በዚህም ሕዝቡ እንደአዲስ ሲቋቋም ብዙዎች ግን ገና በስደት ተበታትነው እንደቀሩ እንረዳለን፣ ይህም ሃይማኖታቸው እንዲስፋፋና ዓለም አቀፍ እንዲሆን አደረገው፣ በመጨረሻ ሕዝቡ ከዳዊት ዘር ንጉሥ መጠባበቅን ትቶ የመላው ዓለም ሕዝቦች አዳኝ የሆነ የሰው ልጅን መጠባበቅ ጀመሩ፣ የሕዝቡ መበታተን ከባቢሎን ከሲርያ በመጨርሻም ከግሪካውያን ሳይቀር ይገናኛሉ የባህል ልውውጥም ያደርጋሉ፣ እንዲህ ባለ ሁኔታ የእግዚአብሔር ጉዞ እንዴት እንደሰፋና ለዓለም አቀፉ ንጉሥ ለሆነው ክርስቶሳዊ ምሥጢር መንገድ ይከፍታል፣ ጊዜው በደረሰ ጊዜም የቸርነት ዕቅድ የሆነው የእግዚአብሔር መገለጥ በክርስቶስ እንደኛ ሰው በመሆን ፍጻሜ ያስገኘዋል፣
ይህንን ስተርክ እግዚአብሔር በሰው ልጆች ታሪክ ያደረጋቸው ነገሮች ዝክር ለማደርግና የዚሁ ታላቅ የፍቅር ዕቅድ ሂደት በብሉይና በአዲስ ኪዳን እንደተመሰከረው ለጠቅላላው የሰው ዘር የታደቀደ አንድያ የድኅነት ጉዞ መሆኑና በእግዚአብሔር ችሎታ በቀጣይነት የተገለጠና የተከናወነ ነው፣ በዚሁ ዕቅድ እግዚአብሔር ሁሌ የሰው ልጆች በሚሰጡት መልስ መሠረት ይሠራል፤ የሰው ልጆች መስመራቸውን ሲስቱም ሁሌ አዲስ መንገዶች በመፍጠር እንደገና ሥራውን ይጀምራል፣ ይህ ነጥብ ለእምነት ጉዞ አችን መሠረታዊ ነው፣ ለበዓለ ልደት በሚያዘጋጀን ዘመነ ምጽአት ነው ያለነው፣ እንድምናውቀው ምጽአት የሚለው ቃል የጌታ መምጣትንና በመካከላችን መገኘትን ይገልጣል፣ በኦሪት ይህ ቃል የአንድ ንጉሥ ወይንም ግዢ በጠቅላይ ግዛቱ መምጣትን ያመልክት ነበር፣ ለእኛ ክርስትያኖች ይህ ቃል አስደናቂውንና አስፈሪውን ፍጻሜ ያመለክታል፣ እግዚአብሔር ሰማዩን ሰንጥቆ ወደ ሰው ልጅ ተንበረከከ፣ በአንድ ሕዝብ ታሪክ በመግባት ከእርሱ ያለውን ኪዳን አጸና፤ በዚችው ዓለማችን ድኃ የሆነችው ጠቅላይ ግዛት የወረደና ሥጋችን በመልበስ እንደኛ ሰው በመሆን የጐበኘን ንጉሥ እርሱ ነው፣ ዘመነ ምጽ አት የዚህን የእግዚአብሔር በመሃከላችን የመሆን ጉዞ እንደገና እንድንኖረውና እግዚአብሔር ከዓለም ፈጽሞ እንዳልተለየ ያሳስበናል፣ ከእኛ ተለይቶም አያውቅም ፈጽሞም ብቻችን አልተወንም፣ ነገር ግን እንድንለያቸው መማር ባለብን በተለያዩ መንገዶች ሊያገኘን ይመጣል፣ ስለዚህ እኛ በዚሁ ሁሌ ጥልቀት የሌለውና ቀልበ ቢስ በሆነው ዓለማችን በእምነታችን በተስፋችንና በፍቅራችን በየዕለቱ ይህንን የእግዚአብሔር ከእኛ ጋር መመላለስን በማስታወስና በመመስከር በቤተ ልሔም ግርግም የፈነጠቀው ብርሃን በሕይወታችን እንዲያንጸባርቅ እንጠራለን፣








All the contents on this site are copyrighted ©.