2012-11-26 16:14:28

የኢየሱስ ሥልጣን የእውነትና የፍቅር ሆኖ ለዘለዓለም የሚኖር ነው፣


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ትናንትና የኢየሱስ ንጉሥ በዓል ለማክበር በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ባሳረጉት መሥዋዕተ ቅዳሴ “የኢየሱስ ሥልጣን የእውነትና የፍቅር ሆኖ ለዘለዓለም የሚኖር ነው፣” ሲሉ ክብረ በዓሉን የሚመለከት ስብከት አቅርበዋል፣ በመሥዋዕተ ቅዳሴው ከተሳተፉት መካከል ቅዳሜ ዕለት የተሾሙ ስድስቱ አዲስ ካርድናሎች ነበሩ፣
የኢየሱስ ንጉሥ ክብረ በዓል ከሚያሳስቡን ነገሮች አንዱ እውነት ኢየሱስን የሕይወታችን ንጉሥ አድርገን የምንቀብልና በፍቅሩ የምንማረክ መሆናችን ወይንም በዚሁ ዓለም ሥልጣን ጥም የተገዛን መሆናችንን የሚያስረዳ ነው፣ ቅዱስነታቸውም ልባችንን ዘለዓለማዊና ወሳኝ በሆነው በክርስቶስ መንግሥት በቆመው ዋና ዓላማችን ማትኰር እንዳለብን ይህም የጌታ ግርማዊነት ሕያዋንና ሙታንን ለመፍረድ በሚመጣበት ጊዜ እንደሚገለጥ አሳስበዋል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በኖርበት ጊዜ የትሕትና መንገድንና መስቀልን መርጠዋል፣ ሕዝብ ግን ሌላ መሲህ ይጠባበቅ ነበር፣ ኢፍትሓዊነትን በኃይል የሚዋጋና መፍትሔ የሚያስገኝ መስሎዋቸው ስለነበር የኢየሱስ የትሕትናና የመስቀል ምርጫ አልዋጥ ብሎዋቸው ነበር፣ ተከታዮቹ የነበሩት ሐዋርያትም ሳይቀር ከእርሱ ጋር የኖሩና ቃሉን ያዳመጡ በፖሎቲካዊ መንግሥትና ሥልጣን የሚያስተዳድርና በዓመጽም ሳይቀር ፍትሕ የሚያመጣ መስሎአቸው ነበር፣
“በጌተሰማኒ ቅዱስ ጴጥሮስ ሰይፉን መዞ መዋጋት ጀመር ኢየሱስ ግን አቆመው፣ (ዮሐ 18፤10-11) ኢየሱስ በጦር መሣርያ ሊከላከሉለት አልፈለገም፤ ሆኖም ግን የአባቱን ፍቃድ እስከ መጨረሻ ለመታዘዝና መንግሥቱን በጦር መሣርያና በዓመጽ ሳይሆን ድካም በሚመስለው ሕይወቱን እስከ መስጠት ባደረገው የፍቅር ሥራ ነበር፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ከዚህ ዓለም መንግሥታት በፍጹም የተለየ ነው”፤ ጲላጦስ ሳይቀር እፊቱ ቆሞ ግዛትናን ኃይልን እግምት ውስጥ ስለ ማያገባ ሥልጣን ሲናገር በሰማ ጊዜ ይገርመዋል፣
“የእውነተኛው መሲህ ሥልጣን ፍጹም የማያልፍና -ፍጹም የማይደመሰስ ሥልጣን ነው፣ እንደምድራዊ ሥልጣናት የሚቆሙና የሚወድቁ ሳይሆን የእውነትና የፍቅር ሥልጣን ነው፣ በዚህም የኢየሱስ ንግሥነት በሮማዊው አስተዳዳሪ ፊት በምሳሌና ግልጥ በሆነ መንገድ በኢየሱስ እንደተገለጠው ለሁሉም ነገሮች ብርሃናቸውና ታላቅነታቸውን የሚሰጥ ብቸኛ የእውነት መንግሥት ነው፣” ክርስቶስን በመስቀል መንገድ የሚከተል በመንግሥቱ ይካፈላል፣
“ኢየሱስ በመሥዋዕቱ ከእግዚአብሔር ጋር ጥልቅ የሆነ ግኑኝነት ለመፍጠር መንገድ ከፈተልን፣ በኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል፤ ስለዚህም በዚህ ዓለም የእርሱ መንግሥት ተካፋዮች ሆነናል፣ የኢየሱስ ተከታይ መሆን ስለዚህ በዚሁ ዓለም የሥልጣን አስተሳሰብ እንዳንማረክ ሆኖም ግን በዓለም የእግዚአብሔር እውነትና ፍቅር ብርሃን ማምጣት አለብን፣”
የክርስቶስ ንጉሥ ክብረ በዓል ስለዚህ እያንዳንዳችን በሕይወታችን እንደገና በአዲስ መንፈስ የእግዚአብሔር ግርማዊነት ወደ ሆነውና እውነተኛው የእግዚአብሔር መንግሥት እንድንመለስ ጥሪ ያቀርብልናል፤
“በየዕለቱ በምናሳርገው በሰማይ የምትኖር አባትችን ሆይ ጸሎት “መንግሥትህ ይምጣ” በሚሉ ቃላት እንለምነዋለን፣ ይህ ማለትም ኢየሱስን ጌታ ሆይ ያንተው አድርገን፤ ከእኛ ጋር ኑር፤ በየቦታው ተበታትኖ በሥቃይ የሚገኘውን የሰው ልጆችን ሰብሳበቸው በአንተ አድርገውም በመሐሪውና ፍቅር በሆነው እግዚአብሔር አብ ሥር እንዲሆኑ አድርግ፤ ብለን እንለምነዋለን፣
በስብከታቸው መጨረሻም ቅዱስነታቸው አዲስ ካርዲናሎችን በማስታውስ “ለእግዚአብሔር መንግሥት ለእውነት ምስክርነት መስጠት አለባችሁ፣ ይህም ማለት ሁሌ የዚሁ ዓለም ጥቅምንና ሥልጣኖችን ትታችሁ ለእግዚአብሔር ለእርሱ ፈቃድ ቅድምያ እንድትሰጡ ይሁን፣ ይህም እስከ መጨረሻ ማፍቀር ለምታፈቅራቸው ሕይወትህን እስከ መስጠት የሚጠይቅ ግዳጅ ነው” ሲሉ ስብከታቸውን ደምድመዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.