2012-11-23 14:22:25

ኮንጎ፦ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ቀውስ


RealAudioMP3 በኪንሻሳ የተሰበሰቡት የ34 የአፍሪቃ አገሮች ብፁዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ሊቀ መናብርት በደሞክራሲያዊት ረፓብሊክ ኮንጎ ተከስቶ ያለው ፖለቲካዊና ወታደራዊ ቀውስ እጅግ አሳሳቢ መሆኑና በአገሪቱ እጅግ ከፍ እያለ በመሄድ ላይ ያለው የትጥቅ አመጽ የሚያሳዝንና የሚያስደነግጥ ከመሆኑም ባሻገር የብዙ ሰው ልጅ ሕይወት ለከፋ አደጋ እያጋለጠ ነው በማለት በአገሪቱ ያለው ውጥረትና ግጭት የብዙ ሕጻናትና የአገሪቱ ዜጋ ሕይወት እየቀጨ ለመፈናቀል አደጋ እያጋለጠ ነው ሲሉ፣ የሕጻናት መንደር የተሰየመው የሕጻናት መርጃ ድርጅት በበኩሉም በአገሪቱ እልባት ያጣው ግጭት ሳቢያ ወላጅ አልባ የሚቀሩት የሕጻናት ቁጥር ብዛት ከፍ እያለ መሆኑና ኮንጎ በሕጻናት ወታደሮች ቁጥር ብዛት በአፍሪቃ የመጀመሪያ ደረጃ ይዛ እንደምትገኝ በመግለጥ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ አስቸኳይ መፍትሔ የሚያሻው መሆኑ ከብፁዓን ጳጳሳቱ ጋር በአንድነት የሰላም ጥሪ ማስተላለፉ ሚስና የዜና አገልግሎት አስታወቀ።
ኤም 32 በመባል የሚተጠራው የአገሪቱን ማእከላዊ መንግሥት ተቃዋሚ ታጣቂው ኃይል ባለፉት ቀናት የጎማን ከተማ መቆጣጠራቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ታጣቂው ኃይል ኡጋንዳ ሩዋንዳና የኮንጎ መንግሥት ከተማይቱን ለቆ እንዲወጣ ላቀረቡት ጥሪ እምቢ በማለት፣ የተዋጊው ኃይል መሪ ዣን ማሪይ ሩኒጋ ከኮንጎ መንግሥት ጋር የሰላም ድርድሩ እስኪጀመር ድረስ ተዋጊው ኃይል ጎማን ለቆ እንደማይወጣ በይፋ አስታውቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ከትላትና በስትያ ኤም 32 ታጣቂው ኃይል ወደ ኪንሻሳ እንደሚያመራ አስታውቆ እንደነበርም የሚታወስ ሲሆን፣ ሆኖም ርእሰ ብሔር ጆሰፍ ካቢላ እንዲጀመር የሚያነቃቁት የሰላም ድርድር ለታጣቂው ኃይል ቀጣይ ውሳኔ መንደርደሪያ ይሆናል እንዳሉ ሚስና የዜና አገልግሎት አስታወቀ።
በእውነቱ ጉዳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና እንዲሁም የአፍሪቃ ህብረት ገላጋይነት የሚያሻው አንገብጋቢ መሆኑና፣ የሕዝቡ ስቃይ ከወዲሁ ለመግታት እንዲቻልና የባሰው እንዳይከሰት የሰላም አስክባሪ ኃይሎች ተልእኮ ወሳኝ መሆኑ ይነገራል።







All the contents on this site are copyrighted ©.