2012-11-14 13:52:01

ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ በአገረ ቫቲካን፦ አቢያተ ህክምና የአስፍሆተ ወንጌል፣ የሰብአዊና የመንፈሳዊ ተልእኮ ሥፍራ


“አቢያተ ህክምና የአስፍሆተ ወንጌል የሰብአዊና የመንፈሳዊ ተልእኮ” ሥፍራ በሚል ርእሰ ጉዳይ የተመራ የሥነ ህክምና ባለ ሙያዎችና የአቢያተ ህክምና ጉዳይ ሐዋርያዊ ተንከባካቢ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ያዘጋጀው 27ኛ ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ በአገረ ቫቲካን እ.ኤ.አ. ከህዳር 15 ቀን እስከ ህዳር 17 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚካሄድ RealAudioMP3 ከትላትና በስትያ የዚህ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር ብፁዕ አቡነ ዝይግሙንት ዞሞውስኪ በቅድስት መንበር የዜናና ማኅተም ክፍል ሕንፃ በሚገኘው የጉባኤ አዳራሽ ተገኝተው ከሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ለመረዳት ተችለዋል።
ይኸንን ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ በቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ ስም ለተጋባእያኑ የእንኳን ደህና መጣችሁና መልእክት በማሰማት መሥዋዕተ ቅዳሴ በማቅረብ የሚያስጀምሩ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ታርቸዚዮ በርቶነ መሆናቸውም ብፁዕ አቡነ ዚሞውስኪ አስታውቀዋል።
ይኽ ከተለያዩ አገሮች የተወጣጡ የሥነ ህክምና ባለ ሙያዎች ሊቃውንትና የሥነ ምርምር ሊቃውንት እንዲሁም በአቢያተ ህክምና ቆሞሶችና የቤተ ጸሎት ሐላፊዎች ካህናትና የበጎ ፈቃድ የግብረ ሠናይ ማኅበር አባላት የኵላዊት ቤተ ክርስትያን አበይት አካላ ጭምር በማሳተፍ ለሦስት ቀናት የሚካሄደው ጉባኤ፣ ስለ አቢያተ ሕክምና ተጨባጭ ሰብአዊ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሁኔታ በመዳሰስ፣ በአቢያተ ህክምና የመተባበርና የፍቅር ሥራ ለማነቃቃት አልሞ አቢያተ ህክምና ለተልእኮ ወንጌል የተገባ ሥፍራ መሆኑ በተለያየ መልኩ የሚያበክር ጉባኤ እንደሚሆን ብፁዕ አቡነ ዝሞውስኪ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በማብራራት፦ “ቤተ ክርስትያን በአቢያተ ህክምና የምትሰጠው አገልግሎት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኵላዊት ቤተ ክርስትያን ‘ቃለ እግዚአብሔር ማበሰርና ድኾችና የታመሙትን መንከባከብ’ በማለት ከሰጠው የተልእኮ ኃላፊነት የመነጨ ነው” ብለዋል።
በበለጸጉ አገሮች ለአቢያተ ህክምና ሥራና አገልግሎት ማስፈጸሚያ የሚመደበው የውጪ እቅድ ብፁዕ አቡነ ዚሞውስኪ በመጥቀስ በየዓመቱ እየጎደለ በመሄድ ላይ መሆኑ በማስታወስ በተለይ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ተከስቶ ያለው ዓለም አቀፋዊ የኤኮኖሚ ቀውስ በአገልግሎት መስጫ ማአከሎች ዘንድ አቢይ ችግር እያስከተለ ነው ካሉ በኋላ፦ “የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን የህክምና መስጫ ማእከሎችና አቢያተ ህክምናዎች መለያቸውና ሚናቸውንም ጭምር የሕይወት ባህል መንከባከብና ማስፋፋት በሚለው መርህ መሠረት በማቀብ የሞትን ባህል የሚቃወሙ ናቸው፣ በሕክምና እጦትና በመድሃኒት ዋጋ መናር ሳቢያ ለሞት አደጋ የሚጋለጡ ዜጎች ብዛት በቀላሉ የሚታይ አይደለም” ብለዋል።
የካቶሊክ አቢያተ ክርስትያን አቢያተ ህክምና ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ መሆናቸው ብፁዕነታቸው በማስታወስ፦ “እነዚህ የቅድስት ቤተ ክርስትያን አቢያተ ህክምናዎችና የጤና ጥበቃ ጣቢያዎች በተለያዩ የመንግሥትና ሌሎች የተለያዩ የዓለም አቀፍ የህክምና መስጫ ማእከሎች በማይገኙባቸው በገጠሩ ክልል የሚገኙ መሆናቸውና አለ ምንም የእምነት የሃይማኖት ልዩነት ለሁሉም ሰብአዊ ፍጡር አገልግሎት የሚሰጥበት ነው” በማለት የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ አጠቃለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በዚህ ከአምስቱ ክፍለ ዓለም የተወጣጡ በጠቅላላ 600 ተጋባእያን “ታሪክና ተልእኮ፣ ሥነ ምግባርና ሰብአዊነት እንዲሰርጽ፣ የሚሠዋ ፍርቅር መንፈሳዊነትና አገልግሎት’ በተሰኙት አበይት ርእሶች ሥር አስተምህሮ በማዳመጥ የሚሳተፉበት ሲሆን፣ የኢጣሊያ የጤና ጥበቃ ሚኒስተር ሬናቶ ባልዱዚ የሚሳተፉ መሆናቸውም ሲገለጥ፣ ቅዳሜ በጉባኤው ማጠቃለያ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ ለተጋባእያኑ በዚህ የእምነት ዓመት የሕክምና አገልግሎትና የሥነ ህክምና ባለ ሙያዎች ጸሎትና መንፈሳዊነት ላይ ያተኮረ አስተምህሮ እንደሚለግሱ ለማወቅ ሲቻል የኤውሮጳ የካቶሊክ ምእመናን የሥነ ጤና ጥበቃ ባለ ሙያዎች ማኅበር እንደሚሳተፍም ተገልጠዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.