2012-11-12 16:22:02

ምንም ነገር መስጠት ከማይችል የባሰ ድኃ የለም፣


RealAudioMP3 ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ትናንትና እኩለ ቀን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የመልአከ እግዚአብሔር ከማሳረጋቸው በፊት ዘወትር በዚህ አጋጣሚ እንደሚያደርጉት በዕለቱ ቃለ ወንጌልና በዕለቱ በሚዘከሩ ልዩ ፍጻሜዎች በመመርኰዝ አስተምህሮ አቅርበዋል፣ በላቲኑ ሥርዓተ አምልኮ የትናንትና እሁድ ወንጌል፤ ድኃዋ መበለት ያቀረበችው የሳንቲም መባእ የሚተርክ ነበር እንዲሁም በጣልያን አገር የምሥጋና ቀንም በመኖሩ በእምነት የተመሠረተ የኑሮ ዘዴ መከተል እንዳለብን በማመልከት “ምንም ነገር መስጠት ከማይችል የባሰ ድኃ የለም” ሲሉ በ1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 17፡10 ላይ ለገዛ ራስዋ ለልጅዋ ብቻ አንዴ ሊመግብ የሚችል ትንሽ ዱቄትና ጥቂት ዘይት ብቻ የነበራት አንዲት ባልቴት፤ ኤልያስ እንጨት ስትለቅም አግኝተዋት ልትመግበው በጠየቃት ጊዜ ያላትን ሁሉ ለእርሱ በመስጠትዋ ዱቄቱ ከማድጋ ሳይጨረስ፥ ዘይቱም ከማሰሮው ሳይጎድል ዝናም እስኪመጣ ለረዥም ቀናት እንደቆየ የሚነግረው ታሪክንና በወንጌለ ማርቆስ 12፡38 የተጻፈውን ያላትን ሁሉ መባ ያቀረበት መበለት ሴት ታሪክ “እጅግ ታላቅ የእምነት ትምህርት” ሲሉ ገልጠውታል፣ ሁለቱም መበለት ሴቶች የእምነት ሞዴሎች ወይም ምሳሌዎች መሆናቸውን እንዲህ ሲሉ አብራርተዋል፣
“ይህ ዓይነት እምነት ሕይወቱን በእግዚአብሔር ላይ የመሠረተ ጥልቅ የሆነ መተማመንን ያመለክታል፤ በአጠቅላይ በእግዚአብሔር ቃል እና በእግዚአብሔር ይተማመናል፣ እግዚአብሔር ከእኛ የሚጠይቀው ነጻ ሆነን ማመንን ነው፤ ይህም ለእርሱ እና ለጓደኞቻችን ባለን ፍቅር ይገለጣል፣ ምንም ነገር መስጠት ከማይችል የባሰ ድኃ የለም፣ ዛሬም ሳይቀር በጎ የፍቅር ሥራ በማድረግ እምነትን የሚያሳዩን በመካከላችን ያሉ መበለቶች ናቸው፣” ሲሉ በእምነትና በምሕረት ሥራ ያለውን ጽኑ መተሳሰርን እውን በማድረግ በእግዚአብሔርና በጓደኛ ፍቅር ያለው መተሳሰርን እንደሚመስከሩ ገልጠዋል፣ ከትናትና ወዲያ ዝክረ በዓሉ የተከበረውን ቅዱስ ልዮን ታላቁን በመጥቀስ ደግሞ “በመለኮታዊው የፍትሕ ሚዛን የሚመዘነው የስጦታ ብዛት ሳይሆን የልቦቻችን ክብደት ነው፣ በእግዚአብሔር ፊት ማንኛው የርኅራኄ ተግባርና የምሕረት ሥራ አለ ፍሬ አይቀርም” ካሉ በኋላ ወደ እመቤታችን የሚከተለውን ልመና አቅርበዋል፣
በዚሁ የእምነት ዓመት እመቤታችን ድንግል ማርያም እያንዳንዳችንን በእግዚአብሔርና በቃሉ ያለን እምነት እንድታበራታታልን እንለምናት ብለው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አሳርገዋል፣
ከመል አከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ ከትናንትና ወዲያ በእስፖለቶ ከተማ ብፅዕናዋ የታወጀ ብፅዕት ማርያ ልዊዛ ፕሮስፐሪ አስታውሰዋል፣ ብፅ ዕት ማርያ ልዊዛ ፕሮስፐሪ የትረቪ የአቡነ ብሩክ ደናግሎች ማኅበር እመምኔት የነበረች መነኵሴ ሆና ከክርስቶስ ሥቃይ ጋር ልዩ ትሥስር የነበራት መሆንዋንም ገልጠዋል፣ በመጨረሻም የምሥጋና ዕለትን በማስታወስ “በዚሁ የእምነት ዓመት በጌታ ተማመን መልካም ነገርን አድርግ ዓለማችን በሕይወት የተመሠረት ኑሮ እንድሚያስፈልጋት ትገልጠሃለች፣ በምስጋና መንፈስም ልጆችህን የሚመግበው ፈጣሪና አሳቢ የሆነው የእግዚአብሔር እጅን በእምነት ልታውቀው ነው” ሲሉ በተለይ ለእርሻ አምራቾች ልዩ ሰላምታና ምስጋና አቅርበዋል፣







All the contents on this site are copyrighted ©.