2012-09-29 13:32:42

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ ኣጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ


ውድ ወንድሞችና እኅቶች፧ ባለፉት ወራት ጸሎትን በሚገባ ለመማር፤ በብሉይ ኪዳን በሚገኙ ታላላቅ የጸሎት ምሳሌዎች በመመልከት እንዲሁም መዝሙረ ዳዊት፤ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክቶችና የዮሐንስ ራእይ በመቃኘት፤ ከሁሉ በላይ ግን ኢየሱስ ከሰማያዊ አባቱ ጋር የነበረው ግኑኝነት መሠረታዊና አንድያ የጸሎት ምሳሌ ላይ በማትኰር በእግዚአብሔር ቃል ብርሃን ተጕዘናል፣ እንደእውነቱ ከሆነ በልጅነት መንፈስ ከሚያፈቅረው አባቱ ከእግዚአብሔር ጋር ጥልቅና የጦፈ አንድነት ሊፈጥር የቻለው ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ የሆነው ክርስቶስ ብቻ ነው፣ ፍቅር በሞላው ስሜት “አባ! አባታችን” ብለን ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የምንችለው በእርሱ ብቻ ነው፣ እንደ ሐዋርያት እኛም ለኢየሱስ “ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን” (ሉቃ 11፤1) በማለት ደጋግመን እንደጠየቅነው አሁንም እንጠይቀው፣
ከዚህ ሌላም ከእግዚአብሔር እግዚአብሔር ግላዊ ግኑኝነት ለመረዳትና ይህንን በጦፈ መንገድ ለመኖር፤ ከሙታን ተለይቶ የተነሣ ክርስቶስ አንደኛ ስጦታ የሆነውን መንፈስ ቅዱስ መለመን እንዳለብን ተምረናል፤ ምክንያቱም “መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል”(ሮሜ 8፡26)፣
እዚህ ላይ፤ በቅዱስ መጽሐፍ ተመርኵዘን ስለጸሎት ብዙ የትምህርተ ክርስቶስ ክፍለ ግዜዎች ካየን በኋላ “በመንፈስ ቅዱስ ለመታነጽ ከእግዚአብሔር ጋር እና በእግዚአብሔር አስተሳሰብ ገብቼ ለመጸለይ እንዴት እችላለሁ፧ እንዴት መጸለይ እንዳለብኝ የሚያስተምረኝና ድካሜን በማገዝ እግዚአብሔርን በሚገባ መጸለይ እንዴት ይረዳኛል፧ ብለን መጠየቅ እንችላለን፣ ባለፉት ሳምንታት እንደተመለከትነው መጀመርያው የጸሎት ትምህርት ቃለ እግዚአብሔር ማለትም ቅዱስ መጽሐፍ ነው፣ ቅዱስ መጽሐፍ በእግዚአብሔር በሰው ልጅ መሃከል የሚደረገው ቀጣይ ውይይት ነው፣ በዚሁ ውይይት እግዚአብሔር ቅርብ ሆኖ ይታያል፣ በዚህም ሁሌ ገጽታውን ድምጹንና ማንነቱን ለማወቅ እንችላለን፣ የሰው ልጅም እግዚአብሔርን ማወቅንና ከእርሱ ጋር መንጋገርን ይቀበላል፣ ስለዚህ ባለፉት ሳምንታት ቅዱስ መጽሐፍን በማንበብ ከዚሁ ቀጣይ ውይይት እንዴት አድርገን ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት እንድምንችል በቅዱስ መጽሐፍ ፈልገን ነበር፣
ከዚህ የተሻለ ሌላ ክቡር ነገር አለ፤ በጸሎት የሚያሳድግ ከላየኛው ጋር ጠበቅ ያለ ግኑኝነት ያለው የሕይወት ውኃ ምንጭ የሆነ እጅግ የከበረ ምንጭ አለ፣ ሥርዓተ አምልኮ ወይንም ሊጡርግያን ለማመልከት ነው፣ የሥርዓተ አምልኮ ምሥጢር እግዚአብሔር በሁሉም ግዜና በሁሉም ቦታ ከመ ቅጽበት ወዲያውኑ ለእያንዳንዳችን የሚናገርበት እና ከእኛ መልስ የሚጠብቅበት ታላቅ ፍጻሜ ነው፣
ሥርዓተ አምልኮ ምንድር ነው፧ ሁሌ ታላቅ መዝገብና ምንጭ የሆነው አዲሱን የካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ ማንበብ እንችላለን “በመሠረቱ ቀደም ሲል ሥር ዓተ አምልኮ የሚለው ቃል ትጉሙ ሕዝባዊ ተግባር ወይም በሕዝብ የሚደረግ አገልግሎት ማለት ነው” (ቍ 1069) የሚል እናነባለን፣ ትምህርተ ንባበ መልኮት ይህንን ቃል ከግሪክ ቢወስደውም በመስቀላ ላይ እጁን ዘርግቶ በአንዱ እግዚአብሔር ሰላም ለሰበሰበውና ክርስቶስ በወለደው አዲስይ የእግዚአብሔር ሕዝብን እግምት ውስጥ በማስገባት ይህንን ትርጉም ሰጠው፣ “በሕዝብ ስም የሚደረግ አገልግሎት” ሲል በገዛ ራሱ የሚቆም ሳይሆን ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢረ ፋሲካ ምስጋና ይግባውና በዚህ የቆመ ሕዝብ ነው፣ እንደእ እውነቱም ከሆነ የእግዚአብሔር ሕዝብ በደም ትሥሥር በመሬትና ባገር ድንበር የቆመ አይደለም ነገር ግን በእግዚአብሄር ልጅ ተግባርና በእርሱ በሚከናወነው የእግዚአብሔር አብ ኅብረት ይወለዳል፣
በአዲሱ የቤተ ክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ በክርስቲያን ባሕል ሥርኣተ ኣምልኮ የሚለው ቃል “ሕዝበ እግዚአብሔር “በእግዚብሔር ሥራ” አንደሚሳተፍ የሚገልፅ መሆኑን ያመለክታል። ምክንያቱም ሕዝበ እግዚኣብሔር እንዳለ የሚኖረው በእግዚኣብሔር ስራ ስለሆነ ነው። ይህንን ጉዳይ የዛሬ 50 ዓመት የተካሄደው የቫቲካን ጉባኤም ጉባኤ መክፈቻውን በስርዓተ ዓምልኮ ጥናት ማድረጉና ታህሳስ 4 1963 ዓ.ም. ጉባኤው ለመጀመሪያ ያፀደቀው ሰነድ የስርዓተ አምልኮ ሰነድ ነበር። ይህ የሆነበት ማለትም የጉባኤው የመጀመርያ ሰነድ የስርዓተ አምልኮ መሆኑ ለብዙዎች የዕድል ጉዳይ መስሎ ይታይ ነበር። በጉባኤው ከፀደቁ ሰነዶች የሥርዓተ ኣምልኮው ሰነድ ብዙ የማያከራክር ቢመስልም የጉባኤውን የአሠራር ጥበብ እንዲያሳድግ አድርጎታል። ሆኖም ግን ያጋጣሚ ነገር ቢመስልም ያለ ምንም ጥርጥር ትክክለኛው ምርጫ መሆኑን ያረጋግጣል፣ ምክንያቱም ቤተ ክርስትያንን ከሚመለከቱ ጉዳዮች በቅደም ተከተልና በይዘት የመጀመሪያ ደረጃውን የያዘ የሥርዓተ አምልኮ ርዕስ ነው፣ ጉባኤው ስለ ሥርዓተ ኣምልኮ ለማጥናት ሲጀምር ጥርት ባለ መልኩ የመጀመሪያውን ቦታ የሠጠው ለፈጣሪው ነው። ከሁሉምና ከምንም በላይ እግዚአብሔር ነውና፡ የጉባኤው ምርጫ እራሱ ስርዓተ አምልኮን መሆኑን ይገለፅልናል። በእግዚአብሔርን ላይ ማተኮር ቅድምያ ካልተሰጠው ሁሉም ነገር አቅጣጫውን ያጠፋል። የስርዓተ አምልኮ ዋና መመዘኛው በእግዚአብሔር ማትኮር ነው እንዲህ በማድረጉም በእግዚኣብሔር ሥራ ይሳተፋል፣ ሆኖም ግን እኛ ልሳተፍበት የተጠራነው በየትኛው የእግዚብሔር ስራ ውስጥ ነው ብለን እራሳችንን መጠየቅ እንችላለን? ለዚህ መልሱ የጉባኤው የስርዓተ ኣምልኮ ሰነድ ሁለት መልሶችን ይሰጠናል። በቁጥር 5 ሲገልፅልን የእግዚአብሔር ሥራ በደህንነት ታሪካችን የፈፀማችው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ያገኘነው ደህንነት ነው። ሆኖም ግን ሰነዱ በቁጥር 7 ላይ ስርዓተ አምልኮ ስንፈፅም የስርዓቱ ማሳረግ ሥራ ራሱ “የክርስቶስ ተግባር ነው” ይለናል። በእርግጥም ሁለቱ ትርጉሞች የተሳሰሩ ናቸው። ዓለምና ሰውን የሚያድነው ማን ነው ብለን የጠየቅን እንደሆነ ያለን ብቸኛ መልስ፡ በመስቀል ላይ የሞተውና ከሙታን ተለይቶ የተነሣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህን ደህንነት ያመጣ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ምሥጢር፣ ዛሬ ለእኛ ለኔ እንዴት እውን ይሆናል። መልሱ በክርስቶስ ሥራ በቤተክርስቲያን ኣማካኝነት ይህም በስርዓተ ዓምልኮ፡ በተለይም የእግዚኣብሔር ልጅ መሥዋዕት የሆነበት የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሕያው በሚያደርግ በምሥጢረ ቅዱስ ቁርባን እውን ይሆናል። እንዲሁም ከሐጢዓት ሞት ወደ አዲስ ሕይወት የምንለወጥበት ምሥጢረ ንስሓና ወደ ቅድስና በሚያደርሱን ሌሎችም ሚስጥራት እውን ይሆና። እንዲህ ባለ መንገድ የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የያዘ ሚስጥረ ፋሲካ የጉባኤው ሥርዓተ ኣምልኮኣዊ ትምህርተ መለኮት ማእከል መሆኑን ያሳያል።

ወደፊት አንድ እርምጃ እንራመድና፤ ይህ የክርስቶስ ምሥጢረ ፋሲካ እውን እንዲሆን የሚያደርገው ምን ይሆን፧ ብለን እንጠይቅ፣ ር.ሊ.ጳ ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቅዱስ ጉባኤ የሚለው የሁለተኛ ቫቲካን ሰነድ ከታወጀ በ25ኛው ዓመት ዝክር የሚከተለውን ጽፈዋል፣ “ክርስቶስ ምሥጢረ ፋሲካውብ እውን ለማድረግ ሁሌ በቤተ ክርስትያኑ ሕያው ነው፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ በሥርዓተ አምልኮ ተግባር፣ ስለዚህም ሥርዓተ አምልኮ ክርስትያኖች ከእግዚብሔርና እሱ ከላከው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚገናኙበት ልዩና የተከበረ ቦታ ነው (ዮሐ 17.3 )፣” በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስም የሚከተለውን እናነባለን፣ “እያንዳንዱ የሥርዓተ አምልኮ ፍጻሜ የእግዚብሔር ልጆች ከአባቻቸው ጋር በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ቅዱስ የሚገናኙበት መንገድ ነው። ይኽም ግንኙነት በቃላትና በድርጊት አማካይነት የሚገለጽና የውይይት መልክ ያለው ነው።” (ቍ.1153) ይሁን እንጂ በመጀመሪያ ስርዓተ አምልኮን ለማክበር የሚያስፈልገው በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገርና በተለይም ድምፁን በማዳመጥ መልስ መስጠት ነው፣ አቡነ ብሩክ በሕገ ገዳሙ መዝሙረ ዳዊትን ስለመድገም ለመነኩሴዎች ሲያስተምር “ሃሳባችን ከድምፃችን ጋር መስማማት” እንዳለበት ነው፣ ቅዱሱ በጸሎተ መዝሙረ ዳዊት ቃላቶች አሳባችንን መቅደም እንዳለባቸው ያስተምራሉ፣ ሁል ግዜ ግን በዘልማድ እንዲህ አይደለም፣ መጀመሪያ ማሰብ አለብን ከዛ በኋላ ያሰብነውን በቃላት እንናገራልን፣ በሥርዓተ አምልኮ ግን የተገላቢጦሽ ሆኖ ይቀየራል። የሚቀድመው ቃሉ ነው፣ እግዚብሔር ቃልን ቅዱስ ሥርዓተ አምልኮ ደግሞ ቃላትን ያበረክቱልናል፣ እኛም በቃላቱና በትርጉማቸው ውስጥ በመግባትና በመቀበል ከሱ ቃል ጋር በመስማማት የእግዚአብሔር ልጆችና እሱንም መምሰል እንችላለን፣ የቅዱስ ጉባኤ ሰነድ እንደሚያስታውሰን “ሥርዓተ አምልኮውን ውጤት እንዲኖረው፤ምእመናን በቅኑ መንፈስ ተዘጋጅተው ሐሳባቸው ከአፋቸው ከሚወጣው ቃል ጋር በማስማማት መለኮታዊውን ጸጋ ለከንቱ እንዳይቀበሉ ከእርሱ ጋር በመተባበር መሥራት አለባቸው” (ቍ.11)፣ በሥር ዓተ አምልኮ ከእግዚአብሔር ጋር በምናከናውነው ውይይት መሠረታዊና ተቀዳሚ ነገር ከአፋችን ከሚወጡ ቃላትና በልባቸው ከምናስበው መካከል ሙሉ ስምምነት መኖር አለበት፣ በታላቁ የጸሎት ታሪክ ቃላት ውስጥ በመግባት ገዛ ራሳችን በእነዚህ ቃላት መንፈስ እናስማማለን በዚህም ከእግዚአብሔር ጋር መናገር እንችላለን፣
ከዚሁ መስመር ሳልወጣ በሥርዓተ አምልኮ ጊዜ ከሚፈጸሙ ነገሮች ስለአንድ ጉዳይ መጥቀስ እፈልጋለሁ፣ ሥር ዓተ አምልኮው ራሱ ከምንሰማው ቃለ እግዚአብሔር በምንናገረውና በምንፈጽመው ስምምነት እንዲኖረን ይጠራናል ይረዳናልም፣ የምናገረው ሠራዒ ካህን ጸሎተ አኰቴተ ቍርባንን ሲጀምር አል ዕሉ አልባቢክሙ ልባችሁን አንሡ የሚለውን ነው፤ ይህም ማለት ከሚያስጨንቁንና ከሚያሳስቡን ፍላጎቶቻችን ጭንቀቶቻችንና ሓሳባችን ከሚሰርቁ ነገሮች ልባችንን ከፍ እናድርግ ይላል፣ ከሁሉም ነገር እጅግ ቅርባችን የሆነው ልባችን በትሕትና ለቃለ እግዚአብሔር ዝግጁ በመሆን ከሚሰማቸውና ከሚደግማቸው ቃላት ትኵረቱን ወደ እግዚብሔር እንዲያደርግ በቤተ ክርስትያን ጸሎት መሳተፍ አለበት፣ የልባችን ትኵረት ሁሌ በመሃከላችን በሚገኝ በእግዚአብሔር ማነጣጠር መሠረታዊ ዝግጅት ነው፣
እንዲህ ባለ ጥልቅ ስሜት ሥርዓተ አምልኮን የፈጸመን እንደሆነ ልባችን ወደ ታች ከሚስበው ስበት ከፍ ብሎ በኅሊና እውነትና ፍቅር ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ወደ ላይ ይወጣል፣ የቤተ ክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ በቍ 2655 “በሚጸልይ ልብ ውስጥ የሚቀጥለውን የድኅነት ምሥጢር የክርስቶስና የመንፈስ ቅዱስ ተል እኮ የሚያውጀው፤ የሚያቀርበውና የሚያስተላልፈው በቤተ ክርስትያን ምሥጢራታዊ ሥርዓተ አምልኮ አማካኝነት ነው፣ መንፈሳውያ ጸሐፍት አንዳንድ ጊዜ ልብን ከመሠዊያ ጋር ያነጻጽሩታል” እንዳለው ሁሉ የእግዚአብሔር መንበረ ታቦት ልባችን ነው፣
ውዶቼ ሥርዓተ አምልኮን በሚገባ የምናሳርገውና የምንኖረው በጸሎት መንፈስ ስናደርገው ነው፤ እንድንታይ ወይንም ሌላ ነገር ለማድረግ ካልፈለግን ነገር ግን የልባችን ትኵረት ወደ እግዚአብሔር በማድረግ ከክርስቶስ ምሥጢር ጋር እና ከአባቱ ጋር ባለው የልጅነቱ ውይይት በመተባበር መንፈሳችን በጸሎት ስንቆጣጠረው ብቻ ነው፣ ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚያረጋግጥልን እግዚአብሔር ጸሎት እንዴት እንደምናደርግ ያስተምረናል፣ (ሮሜ 8፡26) ወደ እርሱ እንድናተኵር እርሱ ራሱ ቃላትን ይሰጠናል፣ እነኚህን ቃላት በመዝሙረ ዳዊት እና በሌሎች ትላልቅ የሥርዓተ አምልኮ ጸሎቶች እንዲሁም በመሥዋዕተ ቅዳሴ ሥር ዓት እናገኛቸዋለን፣ ከመንፈስ ቅዱስና ከእኛ የሚፈልቀው የሥርዓተ አምልኮ ጸሎት፤ ሰው በሆነው ልጁ አማካይነት ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር አብ ያቀና እና የእግዚአብሔርና የሰው ልጅ ተግባር መሆኑን መረዳት እንድንችል ዘንድ እግዚአብሔርን እንለምነው፣








All the contents on this site are copyrighted ©.