2012-09-15 08:05:56

ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ ለመካከለኛው ምስራቅ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋያርዊ ምዕዳን ለገሱ


ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ እ.ኤ.አ. እስከ ፊታችን መስከረም 16 ቀን 2012 ዓ.ም. የሚዘልቀው 24ኛው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ዛሬ ሊባኖስ በመግባት እንደጀመሩ ሲታወቅ፣ የዚህ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋነኛው ዓላማው ወንድሞችን በእምነት ማጽናት የሚል መሆኑ ቢታወቅም ይኸንን ጴጥሮሳዊ RealAudioMP3 ተግባር እ.ኤ.አ. ከጥቅምት 10 ቀን እስከ ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በአገረ ቫቲካን በመካከለኛው ምስራቅ ለምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ብፁዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ‘”ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን በመካከለኛው ምስራቅ፦ ሱታፌና ምስክርነት” በሚል ርእሰ ጉዳይ ሥር ያካሄደው ውይይትና ያረቀቀው የሲኖዶሱ የፍጻሜው ሰነድ በጥልቀት በመመርመር መሪ ቃል ያኖሩበት የደረሱት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምዕዳን ፍሪማቸውን በማኖር፣ በመካከለኛው ምስራቅ ለምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን በመለገስ የሚገልጡት ነው። ቅዱስነታቸው ዛሬ በሮማ ሰዓት አቆጣጠር ከቀትር በኋላ ልክ አምስት ሰዓት ላይ ሃሪሳ በሚገኘው ቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ተገኝተው የደረሱት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምዕዳን ፊርማቸውን የማኖር ሥነ ሥርዓት በመፈጸም ንግግር ማሰማታቸው ለማወቅ ተችለዋል።
ቅዱስ አባታችን በሥነ ሥርዓቱ ለተገኙት የረፓብሊካዊት ሊባኖስ ክቡር ርእሰ ብሔር ሚሸል ሱለይማንን፣ ለክቡርነታቸው ፓትሪያርክ ብፁዕ አቡነ ጆርጆ ላሐም፣ ለመካከለኛው ምስራቅ ብፁዓን ጳጳሳት፣ የሲኖዶስ አባላት ብፁዓን ጳጳሳትና ክቡራን ፓትሪያርኮችን በጠቅላላ በሢመተ ጵጵስና ከሳቸው ጋር ወንድማዊነት ኅብረትና ውህደት ላላቸው አክለውም የተለያዩ ሃይማኖቶች መሪዎች የባህልና የመንግሥት ልኡካን፣ በክርስቶስ ወንድሞቼና እኅቶቼና ውድ ጓደኞቼ በሚል መጠሪያ ሥር በባዚሊካው ለተገኙት ሁሉ ጥልቅ ሰላምታን ካቀረቡ በኋላ፦ ፓትሪያርክ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሳት ጆርጆ ላሐም ላደረጉላቸው አቀባበልና እያቀረቡላቸው ለላአው መስተንግዶ አምስግነው በባዚሊካው እሳቸውን ለማስተዋወቅ ንግግር ላሰሙት ለብፁዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ኒኮላ ኤተሮቪች እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ ለምትገኘው የላቲን ሥርዓትና የምሥራቅ ሥርዓት ለምትከተለው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ብፁዓን ጳጳሳትና ፓትሪያርኮች፣ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያንና የምስልምና ሃይማኖት መሪዎች በሥፍራው ለተቀበላቸው የግሪክ መለካዊት ሥርዓት ለምትከተለው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ምእመናን አመስግነው፣ የሁሉም በዚያኑ ሥፍራ መገኘት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምዕዳን ፊርማ የማኖሩ ሥነ ሥርዓት ከብሮ እንዲደምቅ ማድረጉና ሐውርያዊው ምዕዳን ለኵላዊት ቤተ ክርስያንን የሚመለከት ቢሆንም ቅሉ ለየት ባለ መልኵ በመካከለኛው ምስራቅ ለምተገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ለየት ባለ መልኩ ያተኰረ ነው” ብለዋል።
ፊርማ የማኖሩ ሥነ ሥርዓት የተከናወነበት ዕለት እ.ኤ.አ. በ 335 ዓ.ም. በንጉስ ቆስጣንጢኖስ አቢይ በቤተ ክርስትያን ቅዱስ የተባለው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ የመቃብር ሥፍራ በጎልጎታ የትንሣኤ ሥፍራ ባሲሊካ ግንባታ ማግሥት በምሥራቅ አቢያተ ክርስትያን የተወለደው ዓመታዊ በዓለ መስቀል የሚከበርበት ቀን በመሆኑ ለየት እንዳደረገው ገልጠው፣ “ድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምዕዳን በዚህ የቅዱስ መስቀል በዓል ማስረከቡ የመስቀል ብርሃን እንዲታይ በተለይ ደግሞ በክርስቶስ ብርሃን ሥር መጤን እንዳለበት የሚያሳስብ ዕለት ነው”። በመስቀልና በትንሣኤ መነጣጠል ፈጽሞ የለም፣ የክርስትያን ሱታፌና ምስክርነት በሚሥጢረ ፋሲካ ላይ የጸና ነው። መስቀል የምሉእና የፍጹም ፍቅር መግለጫና ምስክር ነው። ምስቀልን ማክበር ለክስትያናዊ ምስክርነት ምንጭ የሆነው የወንድማማችነትና የቤተ ክርስትያናዊነት ትሥሥር ነጋሪዎች መሆን እንዳለብን ያስገነዝበናል። ተስፋን የሚተገብር ተጨባጭ ሁነት ነው። ብለዋል።
“በመካከለኛው ምስራቅ የምትገኘው ቤተ ክርስትያን የምትኖረው ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከትን እንደሆን ብፁዓን የሲኖዶስ አበው ቀደምት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የተፈራረቀባቸው ኃሴትና ስቃይን፣ ፍርሃትና ተስፋ ዙሪያ በማስተንተን፣ የሚሰቃዩት በውጥረትና በፍርሃት በጭንቀት ተውጠው የሕልውና ትርጉም የሆነውን ክርስቶስ ለመከተል የመረጡትና ብዙውን ጊዜ እንዳይከተሉት መሰናክል የሚጋረጥባቸውን የሚኖሩትን አስቸጋሪው ዕለታዊ ገጠመኝ ቤተ ክርስትያን የራስዋ በማረግ የምትኖረው እንደሆነም መስክረዋል። ከዚሁ ጋር በማያያዝ ቅዱስነታቸው አንደኛ ተሰሎንቄ ምዕ. 1 ቍ. 2 “ሁሉ ጊዜ በጸሎታችን እያስታወስናችሁ በእናንተ ምክንያት ዘወትር እግዚአብሔርን እናመሰግናለን” በማለት ይኽ ቅዱስ ጳውሎስ ያቀረበው ምስጋና ዛሬ ለመካከለኛው ምስራቅ ማኅበረ ክርስትያን ገጠመኝ መሠረት መሆኑ በድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምዕዳን በመጀመሪያው ክፍል የተተኮረበት ነጥብ መሆኑ ገልጠው ቤተ ክርስትያን የምታስተጋባው ቃልም ነው እንዳሉም ተገልጠዋል።
“ቤተ ክርስትያን በመካከለኛው ምስራቅ፣ እይታዋ በክርስቶስ ላይ በማኖርና የክርስቶስ እይታ የገዛ እራሷ በማድረግ፣ ዛሬ መጻኢን ግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሆን ትመራለች፣ ቤተ ክርስትያን በወንጌል መሠረት በሐዋርያዊ ግብረ ኖልዎ በሊጡርጊያ በጥሪዎቿ በመንፈሳዊና ቤተ ክርስትያናዊ ምዕዳኖቿ በምታቀርበው የውይይት ጥሪ በምትሰጠው ትምህረተ ክርስቶስ ወሳኝኛ መሠረታዊ የሆነውን እርሱም ክርስቶስና የክርስቶስ መንገድ ብቻ መሆኑ እንደምትመሰክር በማብራራትም፣ “ወቅቱ ጥላቻ በፍቅር ቂም በቀል በምኅረትና በይቅር ባይነት፣ ትዕቢት በትህትና ሞት በትንሳኤ የመሸነፉ እርግጠኛነት የሚኖርበት የሚመሰከርበት ወቅት ነው፣ በበዓለ መስቀልና እንዲሁም በሐዋርያዊው ምዕዳን ትግባሬ መሠረትም ሁሉም ከፍርሃት ነጻ እንዲሆን በእውነት ላይ እንዲጸናና የእምነት ንጽህና እዲኰተኩትም በማሳሰብም፣ ይኽ ደግሞ የመስቀል ክብር ማለት ነው” ብለዋል። ስለዚህ “መስቀል የሚያጋጥመን ስቃይ ስለ ወዳጆቻችን ወደ እግዚአብሔር የሚጮኽ ፍቅርና ምህረት ሆኖ እንዲለወጥ ይመራናል። በማለት ይኸንን ሃሳብ ከሁለተኛው ቆሮንጦስ ምዕ. 4፣ 7-18 ባለው የቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስ መልእክት ሥር በማብራራትም፣ ክርስቶስን የሚያንጸባርቁ ቃላት መሆናችቸም ገልጠው፣ ስለዚህ ሁሉም የተለያዩ አቢያተ ክርስትያን የአማኞች ማኅበረሰብ መሆን ያለው ውበት (ግብረ ሐዋርያት ምዕ. 2፣ 41-47) እንዲያስተነትኑ የሚደግፍ መሆኑም በማብራራት፣ ይኽ ሃሳብ ለለገሱት የድኅረ ሲኖዶስ ሐውርያዊ ምዕዳን የሁለተኛው ክፍል ማእከል መሆኑ ገልጠዋል።
“በመካከለኛው ምስራቅ የምትገኘው ቤተ ክርስትያን እያንዳንዱ የክርስቶስ ተከታይ ጥረቱና ፍላጎቱን እንዲቀድስ ለቅድስና ጥሪው እንዲተጋ፣ ለአንድ ያልተዛባ ተጨባጭ ግምገማ እውንነት የሚበጅ ለግልና ለማኅበራዊ ሕሊና ምርመራ የሚያነቃቃ ድጋፍ ታቀርባለች። በአንድና ፈጣሬ ኵሉ በሆነው እግዚአብሔር ላይ በሚኖረው እምነት የተመሠረተ፣ በተለያዩ ኃይማኖቶች መካከል ቅንና እውነተኛ የሆነ የጋራ ውይይት እንዲረጋገጥ ምዕዳን ታቀርባለች፣ በወንጌል ማቴዎስ ምዕራፍ 28፣ 19-20 ‘ወደ ዓለም ሕዝብ ሁሉ ሂዱ በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁኋቸው የእኔ ደቀ መዛሙርት አድርጉአቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲፈጽሙ አስተምህሩአቸው፣ እነሆ እኔ እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ ሁሉጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።’ ተብሎ በሰጠው መርህ ቃል መሠረትም በወንጌላዊ ፍቅርና እውነት የተመራ መንፈሳዊ ሰብአዊና የነቃ ችሎታ ያለው በሁሉም አቢያተ ክርስትያን መካከል ለውህደት ያቀና ውይይት ታነቃቃለች። ብለዋል።
የደረሱት ሐዋያዊ ምዕዳን በሁሎም ክፍሉ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ በሙላት እንዲኖርና በምሥጢረ ጥምቀት አማካኝነት የብርሃን ልጅ መሆኑና በእግዚአብሔር ብርሃን ቦግ ያለ መሆኑ፣ ጨለማን ሰንጥቆ ብርሃኑን የሚያፈነድቅ በአስጨናቂው የጭለማው መንፈስ ውስጥም አዲስ ኩራዝ የሆነውን እውነተኛው ብርሃን (ዮሕ, 1፣ 4-5 ና 2ቆር. 4፣ 1-6 ተመልከተ) እንዲያስተላልፍ ለሁሉም እንዲመሰክረውም የሚደግፍ መሆኑ ቅዱስነታቸው ገልጠው፣ “እምነትን የክርስቶስን ደማቁን ግርማ ከሚጋርድ ክፍ ነገሮችና ሁኔታዎች ሁሉ የሚያላቅቅ ነው። ስለዚህ ሱታፌ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይነትን የሚያመለክት ሲሆን፣ ምስክርነት ለመስቀል ክብር ትርጉም የሚሰጥ የፋሲካ ሚሥጢር ጮራ የሚያፈነጥቅ ማለት ነው። እኛ “የእግዚአብሔር ኃይል የእግዚአብእሔር ጥበብ የሆነው … ክርስቶስ ስለ እኛ መሰቀሉን … መስቀሉን እንመሰክራለን … (1ቆሮ. 1፣ 23-24)፣ የተሰኘው ቃለ ወንጌል የሐዋርያዊው ምዕዳን ማእከል መሆኑ ገልጠዋል።
“እናንተ አነስተኛ መንጋ የሆናችሁ ወገኖቼ አትፍሩ….” (ሉቃ. 12፣ 32) ኢየሱስ ክርስቶስ ለንጉስ ቆስጣንጢኖስ አቢይ “በመስቀል ምልክት ታሸንፋለህ” ሲል የገባው ቃል ቅዱስ አባታችን ሁሉም ልብ እንዲለው አደራ ካሉ በኋላ በመካከለኛው ምሥራቅ ለምትገኘው ቤተ ክርስትያን “አትፍሪ ምክንያቱም ጌታችን እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከአንቺ ጋር ነው፣ አትፍሪ ምክንያቱም ኵላዊት ቤተ ክርስትያን በሰብአዊና በመንፈሳዊ ረገድ ቅርብ በመሆን በጉዞሽ አብራ በመጓዝ ተሸኛኝሻለችና። በማለት በዚህ ስሜትና የማበረታታቻ መንፈስ የመካከለኛው ምስራቅ ቤተ ክርስትያንና ምእመናን በሱታፌና በምስክርነት አማካኝነት የክልሉ ዕለታዊ ሕይወት ንቁ ተሳታፊያን እንዲሆኑ ተማጥነው፣ ይኸንን የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምዕዳን እ.ኤ.አ. እሁድ መስከረም 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ወንድሞቼ በማለት ለሰየሙዋቸው ለብፁዓን ፓትሪያርኮች ሊቀ ጳጳሳት፣ ጳጳሳትና ካህናት ዲያቆናትና ገዳማውያን የዘርአ ክህነት ተማሪዎችና ምእመናን በይፋ እንደሚለግሱ በማስታወስ፣ “…ነገር ግን አይዞአችሁ፣ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁና” (ዮሐ. 16፣33) የሚለውን የኢየሱስ ቃል በመጥቀስም ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም ጥበቃ ለክልሉ ህዝብ ሰላምና ወድማማችነት የሃይማኖት ነጻነት እንዲረጋገጥልነት ታማልድልን ካሉ በኋላ እግዚአብሔር ሁሉንም ይባርክ በማለት ያሰሙትን ንግግር አጠናቀዋል።







All the contents on this site are copyrighted ©.