2012-08-24 11:47:40

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ


ውድ ወንድሞችና እኅቶች፧ ዛሬ እመቤታችን ብፅዕት ድንግል ማርያም “ንግሥት” በሚል ሥያሜ ጥበቃዋ የሚማጠንበት ሥርዓተ አምልኮአዊ ዝክረ በዓል ነው፣ ይህ ዝክረ በዓል መሠረቱና ሥርዓቱ ጥንታዊ ቢሆንም እንደ አንቀጸ ሃይማኖት በውል የታወጀው እ.አ.አ በ1954 ዓም በዝክረ ጥዑም ር.ሊ.ጳ ፕዮስ 12ኛ ነው፣ ቅዱስነታቸው ይህንን ያወጁት የማርያም ዓመት መዝጊያ ላይ ነበር፤ ዕለቱንም 31 ግንቦት እንዲሆን ወስነዋል፣ በዛኛው አጋጣሚ ር.ሊ.ጳጳሳቱ “ማርያም በነፍስዋ ታላቅነትና በተቀበለቻቸው ከፍተኛ መለኮታውያን ሥጦታዎች ከሁሉም ፍጥረት በላይ ንግሥት ናት” ብለው ነበር፣ ከአዋጁ በኋል በሰጡት የመልአከ እግዚብሔር ጉባኤ አስተምህሮም “እርስዋ ለሰው ልጅ ያላት የፍቅርዋ መዝገብና አሳቢነት ከፍ ከማድረግ አትቆጠብምም” ብለው ነበር፣ ከሁለተኛ የቫቲካን ጉባኤ ኅዳሴ በኋላ ግን የዝክረ በዓሉ ዕለት ከፍልሰታ በዓል አንድ ሳምንት በኋላ እንዲሆን ተወስነዋል፣ ይህም የተደረገበት ምክንያት በነፍስዋና በሥጋዋ ወደ ሰማይ በመፍለስ ከልጅዋ ጋር መገናኘትዋንና ንግሥነትዋን ለማያያዝ ነው፣ በሁለተኛው ጉባኤ ሰንዶች ስለቤተ ክርስትያን በሚናገረው ክፍል ውስጥ “እመቤታችን ድንግል ማርያም ለሰማያዊ ክብር ወደ ሰማይ ፈለሰች ከጌታም የመላው ዓለም ንግሥት ሆና ተሰየመች ምክንያቱም ከልጅዋ ጋር ሙሉ በሙሉ ስለተዋሃደች” (ቍ 59) የሚል እናነባለን፣ የዚሁ በዓል መሠረትም እዚህ ላይ ነው፣ እመቤታችን ድንግል ማርያም ንግሥት ናት ምክንያቱም ከልጅዋ ጋር በምድራዊ ሕይወትዋም ይሁን በሰማያዊ ክብርዋ ልዩ በሆነ መንገድ ስለተሳሰረች፣ ታላቁ ሶርያዊ ቅዱስ ኤፍረም የእመቤታችን ንግሥነት ከእናትነትዋ ይመነጫል ምክንያቱም እርስዋ ንጉሠ ነገሥት የሆነ ጌታ እናት ነች፤ በዚህም ሕይወታችን ድህነታችንና ተስፋችን የሆነ ኢየሱስ ጋር ታደርሰናለች” ይላል፣ የእግዚአብሔር አገልጋይ ር.ሊ.ጳ ጳውሎስ 6ኛም ስለ እመቤታችን አክብሮት በጻፉት ሐዋርያዊ ምዕዳን ውስጥ “በእመቤታችን ድንግል ማርያም ሁሉ ከኢየሱስ ጋር የተዛመደ ሁሉ በእርሱ ይጠጋል፤ በእርሱ አማካኝነት እግዚአብሔር አብ ከዘለዓለማዊነት ከእርስዋ በስተቀር ለማንም ባልተሰጠ በቅድስና የተሞላች እናት አድርጎ መረጣት በመንፈስ ቅዱስ ሃብታትም ሸለማት (ቍ 25)” በማለት አስተውሰውታል፣
መለስ ብለን ማርያም ንግሥት ናት ማለት ምን ማለት ነው፧ እንደማንኛው ለሌሎች የሚሰጥ ቅጽል ወይንም የሽልማት ዘውድ ይሆን፧ ምን ማለት ነው፧ ይህ ንግሥነት ምንድር ነው፧ ብለን የጠየቅን እንደሆነ፤ ጌታ እንዳመለከተልን ንግሥነትዋ ከልጅዋ ጋር አንድ መሆን ነው፣ ማለትም ከእግዚአብሔር ጋር አንድ በመሆን በሰማይ መኖርዋን ያመለክታል፣ በተራ አነጋገር ንጉሥ ወይንም ንግሥት ማለት ሥልጣንና ገንዘብ የያዘ ሰው ያመለክት ይሆናል ሆኖም ግን የኢየሱስና የእመቤታችን ማርያም ንግሥነት የዚህ ዓይነት አይደለም፣ ስለ ጌታ ኢየሱስ እናሰላስል፤ ግርማዊነት ከኢየሱስ ማነንት ቢሆንም ቅሉ ከትሕትና ከአገልግሎት እና ከፍቅር ጋር የተሳሰረ ነው፤ በተለይ ደግሞ በማገልገል በመርዳትና በማፍቀር ይገለጣል፣ ኢየሱስ ንጉሥ የተሰየመበት በመስቀል ላይ ተንጠልጥሎ ሳለ ጲላጦስ ንጉሠ አይሁድ ብሎ በጻፈው መሆኑን እናስታውስ፣ ያኔ በመስቀል ላይ ሆኖ ከእኛና ስለእኛ ሲሰቃይ እስከ መጨረሻ በማፍቀር እውነት ፍቅርንና ፍትሕን እየፈጠረ ይገዛል፣ ሌላ ንግሥነቱን የሚገልጠው ደግሞ በመጨረሻው ራት ላይ ተንበርክኮ የወገኑ እግር በማጠብ ይገዛል፣ ስለዚህ የኢየሱስ ንግሥነት ከዚህ ዓለም ኃያላንና ገዢዎች የሚያገናኝ ምንም የለውም፣ አገልጋዮቹን የሚያገለግል ንጉሥ ነው፤ ይህንን ደግሞ በመላው ሕይወቱ አሳየው፣ ለእመቤታችን ድንግል ማርያም ንግሥነትም ልክ እንዲሁ ነው፣ እርስዋ የእግዚአብሔርና የሰው ልጆች አገልግሎት ንግሥት ናት፤ እርስዋ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ድኅነት ባቀደው ዓላማ ለመግባት ሁለመናዋን ለእግዚአብሔር በመሰዋት የምትኖር የፍቅር ንግሥት ናት፣ለመልአኩ “እነሆነኝ የጌታ ባርያ” በማለት የመለሰችና በጸሎትዋ “እግዚብሔር የባርያው ትህትና አይተዋልና” ብላ የዘመረች ሁሌ ትረዳናለች፤ በኑሮአችን ሁሉ እየወደደችንና እየረዳችን የምትኖር ትህትና የተሞላት እኅታችን ንግሥት ናት፣
እንዲህ አድርገን በማሰላሰል እመቤታችን ድንግል ማርያም ይህንን የፍቅር አገልግሎት ንግሥነት እንዴት እተግባር ላይ እንደምታውለው እሚገልጥ ነጥብ ደርሰናል፣ ልናመሰግናት ወይንም እናታዊ ጥበቃውን ለመማጠን፤ ምናልባትም በሥቃይ ጫና ምክንያት ወይንም በዕለታዊ ኑሮአችን በሚገጥሙን ችግሮች ተጨንቀን መንገድ የጠፋን እንደሆነ ሰማያዊ እርዳታዋ ለመጠየቅ በጸሎት ወደ እርስዋ ለምንማጠን ልጆችዋ በመጠበቅ ንግሥነትዋን ትገልጣለች፣ በዚሁ ዓለም ረጅም የሕይወት ጉዞ የሚያስፈልጉንን ጸጋና ምሕረት ከልጅዋ እንድታስገኝልን ተግተን በምንመላለስበትም ይሁን፤ ጨንቆን በኑሮ ጨለማ ስንንከራተት፤ ዘወትር በእርስዋ አማላጅነት ተማምነን እንማጠናታለን፣ ዓለምን በሚገዛውና የዓለምን ሁኔታ ሁሉ በእጁ ለያዘው ጌታ፤ በእመቤታችን አማላጅነት እንዲረዳን በመተማመን እንማጠነዋለን፣ እርሷ ከዘመናት ንግሥተ ሰማያት ተብላ ስትጠራ ኖራለች፣ በጸሎተ መቍጠርያ ሊጣንያ ስምንት ግዜ ንግሥት ተብላ ትለመናለች፧ ንግሥተ መላእክት፤ ንግሥተ አበው፤ ንግሥተ ነብያት፤ ንግሥተ ሐዋርያት፤ ንግሥተ ሰማዕታት፤ ንግሥተ ጻድቃን፤ ንግሥተ ደናግል፤ ንግሥተ ቅዱሳንና ቤተ ሰቦች ተብላ ትጠራለች፣ የእነኚህ ጥንታውያን ሊጣንያዎችና ሰላም ለኪ ኦ ንግሥት የሚል ጸሎት በሰማይ ከልጅዋ ጐን በክብር የምትገኘው እናታችን የሆነችው እመቤታችን ድንግል ማርያም ዕልታዊ ኑሮአችንን በድል እንድናዋጣ እጐናችን ሆና ዘወትር እንደምትሸኘን ለመረዳት ያስችለናል፣ ስለዚህ ንግሥት የሚለው ስያሜ የመተማመን የደስታ እና የፍቅር ስያሜ ነው፣ በዚህች ንግሥት እጅ ያለው የዓለም ዕጣ ፈንታ መልካም መሆኑን እናውቃለን፤ እንዲሁም በችግራችን ጊዜ ታፈቅራናለች ትረዳናለችም፣ውዶቼ፤ እመቤታችንን ማክበር በመፈሳዊ ሕይወት አስፈላጊ ነው፣ ጸሎት ስናሳርግ በመተማመን ወደ እርሷ መማጠንን አንርሳ፣ እመቤታችን ድንግል ማርያምም ስለእኛ ከልጅዋ መማለድ አትረሳም፣ እርሷን አይተን በእምነት ለእግዚአብሔር የድኅነት ፍቅራዊ እቅድ በሙላት መተባበር እና ኢየሱስን በለጋስነት በመቀበል እንመሰላት፣ እመቤታችን ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥትና ከእግዚአብሔር ጋር ናት፤ ሆኖም ግን እያንዳንዳችንን የምታፈቅርና ድምጻችንን የምትሰማ የቅርብ እናትም ናት፣







All the contents on this site are copyrighted ©.