2012-08-24 14:27:40

ብፁዕ አቡነ ቶማሲ፦ ጸረ ክርስትያን ዓመጽ መስፋፋት
33ኛው ዓለም አቀፍ“Comunione e liberazione-ሱታፌና አርነት” የጥናት ጉባኤ



ባለፈው እሁድ እ.ኤ.አ. ነሐሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢጣሊሊያ ሮማ አቅራቢያ በምተገኘው ሪሚኒ ከተማ “Comunione e liberazione-ሱታፌና አርነት” የተየሰየመው ካቶሊካዊ ማኅበርሰብ በየዓመቱ የሚያዘጋጀው ዓለም አቀፋዊ ዓወደ ጥናት በመቀጠል “የሰው ልጅ ዓይነተኛው ባህርይ ከወሰን አልቦ ጋር ተገናኝነት” በተሰየመው RealAudioMP3 ጠቅላይ ርእስ ሥር የማኅበርሰቡ መሥራች ስመ ጥር ነፍሰ ኄር ክቡር አባ ልዊጂ ጁሳኒ “ሃይማኖታዊ ስሜትና ትርጉም” በሚል ርእስ ሥር የደረሱት አቢይ ቲዮሎጊያዊና ፍልስፍናዊ ጥናታዊ ሰነድ ላይ በማተኮር የዘንድሮ 33ኛው ዓለም አቀፍ ዓውደ ጥናት በይፋ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፣ በዓወደ ጥናቱ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት በጀነቭ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ብፁዕ አቡነ ሲልቫኖ ማሪያ ቶማሲ ትላትና ለተጋባእያኑ የሃይማኖት ነጻነት ዙሪያ ባሰሙት ንግግር፣ በዓለም ጸረ ክርስያን አመጽ እየተስፋፋ ነው በማለት እንዳሰመሩበት ሲታወቅ ብፁዕነታቸው ከቫቲካን ረዲዮ ጋዜጠኛ ደቦራ ዶኒኒ ለቀረበላቸው ቃለ መጠይቅ ሲመልሱ፣ በዓለማችን ጸረ ሃይማኖት መንፈስ እየተስፋፋ መሆኑ ገልጠው፣ አንዳንድ መንግሥታት የምእመናን የሃይማኖት መብትና ነጻነት በመገደብም በሌላው ረገድም ኅብረተሰብ በውስጡ የሚጠቃለሉትን የውሁዳን ሃይማኖት ነጻነት በመርገጥ በሕግና እንዲሁም በፖለቲካዊ ሂደት በአማኞች ማኅበረሰብ ላይ የሚታየው የተጽእኖና የማሳደዱ ተግባር መሠረት በማድረግ ካብራሩ በኋላ፣ ይኽንን የሰጡት የሃይማኖት ነጻነት ጉዳይ ትንተና በቅርቡ የተለያዩ የሥነ ማሕበረሰብ ጥናቶች ዋቢ ያደረገ ሆኖ፣ አክለውም ጸረ ክርስትያን ዓመጽ መስፋፋትና ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ሲነጻጸር ማኅበረ ክርስትያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ለስደትና መከራ ተጋልጦ እንደሚገኝም የሕብረተሰብ ክፍል መሆኑ ከተሰጠው የሥነ ማኅበረሰብ ጥናት መሠረት በማድረግ ገልጠዋል።
በናይጀሪያ ያለው ወቅታዊው ሁኔታ ማኅበረ ክርስትያን እምነቱን እንዳይኖር ተገሎ እንዲኖር ለማድረግ አልሞ ከአክራርያን ሙስሊሞች ኃይሎች የሚጣልበት ጥቃት፣ እንዲሁም በሌሎች ክልሎች ክርስትያን የማኅበርሰብ ክፍል እንዳይኖር ለማድረግ ያለመ ምእመናን ለስደት የሚዳርጉ ጸረ ክርስትያን አመጽ እንደሚታይ የኢራቅ ወቅታዊው ሁኔታ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በሲሪያ እየተከሰተ ያለው ሁኔታ ጠቅሰው በማብራራትም፣ ክርስትያን ማኅበርሰብ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ትሥሥር ያለው ነው በሚል አገላለጥ በገዛ አገር የውጭ ዜጋ በማድረግ የሚነጥል ለስደት የሚዳርግ አመለካከትና ይኸንን አመለካከት በመከተል ክርስትያን ማኅበረሰብ ለስደት እንዲል የሚገፋፉ አመጾች ሲፈጸሙ ይታያል ብለዋል።
በምዕራቡ ዓለም ሃይማኖት ለግል ነጻነት መሰናክል ነው የሚል አስተሳሰብ የሚያዛምቱ ፖለቲካዊ ፍልስፍናዊ አመለካከቶች እንዳሉ ገልጠው፣ ይኽ ደግሞ ሃይማኖት ማሕበራዊ ገጽታውን ለመሰረዝ ሆን ተብሎ የሚሰነዘር ስውር ጥቃት መሆኑ አብራርተው፣ የማኅበረ ክርስትያን መብት የሚገታ ስውር ባህላዊ ደባ እየተስፋፋ መሆኑ የሚያረጋግጥ ነው ካሉ በኋላ የሌላው መብትና ክብር እንዲገታ የሚያደርገው የአንድ ሃይማኖት ተከታይ ማኅበረሰብ ሳይሆን፣ ሕዝባዊ ወይንም መንግሥታዊ ውሳኔዎች ናቸው የአማኞች መብትና ክብር እንዲገታ የሚያደርጉት። ሃይማኖት የማንም መብትና ክብር የሚቀናቀን ሳይሆን እውነተኛው ሰብአዊ መብትና ክብር እንዲከበር የሚል ነው በማለት የሰጡትን ቃለ ምልልስ አጠቃለዋል።







All the contents on this site are copyrighted ©.