2012-07-31 18:45:14

የ.ር.ሊ.ጳ የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ትናንትና እኩለ ቀን ለበጋ ዕረፍት በሚገኙበት ብካስተል ጋንደልፎ ሐዋርያዊ አደራሽ ከአከባቢው ምእመናንና ነጋድያን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት የዕለቱ ቃለ ወንጌል ተመርኵዘው “ትናንሽ የፍቅር ምግባሮችን” ማወቅ እንዳለብን አሳስበው በሲርያ እየተካሄደ ያለው ዕልቂትና ጭፍጨፋ እንዲቆም እንዲሁም በኢራቅ በየጊዜው የሚፈጸመው የዓመጽና የውድመት ተግባር እንዲገታ ጥሪ አቅርበዋል፣ ሶሙንን በኢጣልያ ሃገር በታራንቶ ከተማ በኢልቫ ሠራተኞች ላይ በደረሰው አደጋ ለተጐዱትና ለቤተሰቦቻቸው በመንፈስ ቅርበታቸውን ገልጠዋል፣
የሲርያ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ የተሰማቸውን ስጋት ሲገልጹ መፍትሔው ግን በዓመጽ ሳይሆን ፍትሕ የሚነግሠው በፍቅር ነው፣ እንዲህ እንዲሆንም ጸሎት አሳርገዋል፣ በመጨረሻም ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀንን በ2013 በሪዮ ዲ ጃነሮ ብራዚል በተሳካ ሁኔታ እንዲደረግ በዝግጅት ላይ እየሰሩ ያሉትን የሪዮ ዲ ጃነሮ ወጣቶችን አመስግነዋል፣ ከ50 ሺ በላይ የሚሆኑ የብራዚል ወጣቶች በሪዮ ዲ ጃነሮ ላለፉት ሶስት ቀናት ተሰብስበው ለዝግጅቱ የሚሠሩ 5 ሺ የሚሆኑ በነጻ በውዴታ የሚያገልግሉ ወጣቶች መርጠዋል፣ በስብሰባው የቤተ ክርስትያን ባለሥልጣናትም ተገኝተዋል ወጣቶቹም በኑንስዮ አመካኝነት ለር.ሊ.ጳ ምስጋናቸው የሚገልጥና በመሃከላቸው እንዲገኙ ደስተኞች መሆናቸውን በመግለጥ መምጣታቸውን በጉጉት እንደሚጠባበቁት የሚገልጽ መል እክት ልከዋል፣ ለዚህና ለሚያደርጉት ዝግጅትም ነው ቅዱስነታቸው ያመሰገኑት፣
በሲርያ ውስጥ ዘግናኝ ውግያ እየቀጠለ ነው፣ ቅዱስነታቸውም ይህንን እየተከታተሉት መሆናቸውና በየዕለቱ እየባሰ የሚሄደው አሳዛኝ የዓመጽ ሁኔታ ሰላማውያን ሰዎች ሳይቀሩ ብዙ ሞትና ወድመት እያስከተለ እንዲሁም ብዙ ሰዎች እየተፈናቀሉና ቤት ንብረታቸው ትተው አለምንም መከላከያ በጐረቤት አገሮች ለስደት እየጐረፉ ናቸው፣
ለዚህም አስፈላጊው ሰብ አዊ እርዳታ እንዲደረግላቸው ሁላቸው እንዲተባበርዋቸው ጥሪ አቅርበዋል፣ እሳቸውም ከዚሁ ከሚሰቃየው ሕዝብ በመንፈስ ቅርብ መሆናቸውና በጸሎታቸው እንደሚያስብዋቸው ገልጠዋል፣
“ማንኛው ዓመጽና ደም መፋሰስ ወዲያው እንዲቆም እንደገና አስቸኳይ ጥሪ አቀርባለሁ፣ ሁላቸው በተለይ ደግሞ ታላቅ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች ሰላማዊ መፈትሔ የሚገኝበት መንገድ ሳይታክቱ እንዲፈልጉ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ማኅበረ ሰብ በውይይትና በዕርቅ ለግጭቱ ተገቢ ፖሎቲካዊ መፍትሔ እንዲያገኙ፣ እግዚአብሔር የልብ ጥበብ እንዲሰጥ እለምነዋለሁ፣” በማለት ስለሲርያ ጥሪ ካቀረቡ በኋላ በዚሁ ቀናት የብዙ ሰዎች ሕይወት የቀዘፉና ያቆሰሉ እጅግ ብዙና ከባድ የዓመጽ ተግባሮች በማስታወስም እንዲህ ብለዋል፣ “ይህች ታላቅ አገር የመረጋጋት የዕርቅና የሰላም መንገድ እንድታገኝ ይሁን፣”
ቅዱስነታቸው በሌላ በኩል ያስታወሱት ደግሞ በኢልቫ ሠራተኞች በታራንቶ ከተማ የተከሰተውን ችግር ነው፣ “በጸሎቴ እንደማስባቸው እና የቤተ ክርስትያን ድጋፍ እንደማይለያቸው በማረጋገጥ ሁላቸው የኃላፊነት ስሜት እንዲያሳድሩ እንዲሁም ሃገራዊና የቦታው ተቅዋሞች በተለይ ደግሞ በዚሁ የምጣኔ ሃብት ቀውስ ባለበት ጊዜ ለጥያቄው ትክክለኛ መፍትሔ እንዲያገኙ የጤናና የሥራ መብት እንዲያስጠብቁ አበራታታለሁ” ብለዋል፣
በመጨረሻም ለሚመጣው ዓመት በሪዮ ዲ ጃነሮ ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በማዘጋጀት ያሉትን ለዚሁ አስፈላጊ የቤተ ክርስትያን መገናኘት ለሚያደርጉት አበርክቶ እንዲህ ሲሉ አመስግነዋል፣ “ለብዙ ወጣቶች የቤተ ክርስትያን አባላት የመሆን እና በእምነት የመኖር ደስታንና መልካምነት የሚያጣጥሙበት ወርቃማ አጋጣሚ ነው” ብለውታል፣
ቅዱስነታቸው በትምህርታቸው በላቲኑ ሥርዓተ አምልኮ ለትናንትና እሁድ የቀረበውን የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 6 ኢየሱስ አምስት ሺ ሰዎች በተአምር የመገበበት ክፍል የቅዱስ ቍርባን ምሳሌ መሆኑን አመልክተው ቅዱስ ቍርባን እግዚአብሔርና የሰው ልጅ ዘወትር የሚገናኙበት ጌታ ደግሞ ወደ እርሱ እንዲለውጠን ራሱን በመስጠት መግባችን የሚሆንበት ምሥጢር መሆኑን ገልጠዋል፣ ብዙ ሰዎች ተርበው ባየ ጊዜ የነበርውን አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘውን ልጅ በማስታወስም፣
“ተአምር አለምንም መንሻ አይደረግም ሆኖም ግን አንድ ልጅ ይዞ በነበረው ትንሽ ነገር ይፈጸማል፣ ኢየሱስ የሌለን ነገር አይጠይቀንም ነገር ግን እያንዳንዳችን ያለንን ትንሽ ነገር ያቀረብን እንደሆነ እንደገና አዲስ ተአምር ሊያደርግ እንደሚችል ያስተምረናል፣ እግዚአብሔር እያንዳንዱን ትንሽ የፍቅር እንቅስቃሴአችን ሊያበረክተውና የስጦታው ተካፋዮች ሊያደርገን የሚችል አምላክ ነው፣ ሰዎቹም ኢየሱስ ያደረገውን ተአምር ባዩ ጊዜ በእርግጥ ይህ ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው በማለት ሊያነግሱት ፈልገዋል፣ ኢየሱስም ይህን ባወቀ ጊዜ ራቅ ብሎ ብቻውን እንደገና ወደ ኮረብታ ሄደ፣ ኢየሱስ ግዛቱን የሚያሳይ ምድራዊ ንጉሥ አይደለም ነገር ግን የሚያገለግል ንጉሥ ነው፣ ምድራዊ ረሃቡን ሊቆጭ ብቻ ሳይሆን ጥልቅ የሆነው ረሃቡ የመአዝንህ የማወቅ ረሃብ የሕይወት ትርጉም የማወቅ ረሃብ የእውነት ረሃብ የእግዚአብሔር ረሃብን ለማርካት ራሱን ወደ ሰው ልጆች ዝቅ የሚደርግ ንጉሥ ነው፣”
ር.ሊ.ጳ በመጨረሻ “የሰው ልጆች በዳቦ ብቻ ሳይሆን በእውነት በፍቅር በክርስቶስ በክርስቶስ ሰውነት እንዲመገቡና በታማኝነት በታላቅ እውቀት በቅዱስ ቍርባን እንዲሳተፉ ዘወትር ከጌታ ጋር የጠለቀ ግኑኝነት እንዲኖራቸው እንድሚጸልዩም” ገልጠዋል፣
ከዚህ ጋር በማያያዝም “ለማንኛውም ሰው ለተገቢ ሕይወት አስፈላጊ የሆነው የዕለት እንጀራ እንዳይጐድልና በዓለማችን ያለው አለእኩልነት በዓመጽ መሳርያ ሳይሆነ በመከፋፈልና በፍቅር እንዲሸኘፉ፡መጸለይ፡አለብን” ብለዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.