2012-06-13 15:21:35

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ (13.06.12)


ውድ ወንድሞችና እኅቶች፧ ከጌታ ጋር የምናደርገው ዕለታዊ ግኑኘትና ዘወትር ምሥጢራትን መሳተፍ አእምሮአችንና ልባችንን ለጌታ ህልውና ለቃላቱ እና ለተግባሩ ክፍት ያደርገዋል፣ ጸሎት የነፍስ እስትንፋስ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን አንድ ምሳሌ ለመጠቅም ያህል፤ መንፈሳዊ ሕይወታችን የሚመግብና ኑሮ አችን ከሚቀይር ውኃ መቅዳት የምንችልበት የሰላም ምድረ ገነት ነው፣ ዘወትር አጠገቡ እንድንሆን በጉዞ አችን ብርሃንና መጽናናት እየሰጠን ወደ እርሱ የሚስበን፤ በቅድስና ተራራ ላይ እንድንወጣ የሚያደርገን፤ እግዚአብሔር ነው፣ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንጦስ ሰዎች በጻፈው ሁለተኛ መል እክቱ በም ዕራፍ 12 ይህንን ግላዊ ተመኵሮ የሚገልጸው ይህንን ነው፣ ዛሬ ለማስተማር የምፈልገውም ይህ ነው፣ የሐዋርያዊ አገልግሎቱ ሕጋውነት ከሚቃወሙት ፊት ቆሞ እርሱ የመሠረተውን ማኅበረ ክርስትያን ብዛት ወይንም የተጓዛቸው ኪሎ ሜትሮች ብዛት አይዘረዘርም ወይንም ወንጌል ሲሰብክ ያገጠመው ችግርና ተቋውሞን በመተረክ አይወሰንም፤ ነገር ግን ከጌታ ጋር ያለውን ግኑኝነት ያመለክታል፤ ይህ ግኑኝነት እጅግ የጦፈ ሆኖ እስከ በሰቂለ ኅሊና የሚገለጽ የራእይና የመገለጥ ግዜ እንደሆነ ይገልጣል (2ቆሮ 12፡1 ተመልከት)፣ ስለዚህ እርሲ በፈጸማቸው ጉድዮች ስለ ችሎታው ስለ ታታሪነቱ ወይንም ድል ስለ ማድረጉ አይመካም፤ ነገር ግን ይህንን ሁሉ በእርሱ አማካኝነት እንዲፈጸም ባደረገው በውስጡ ባለው በእግዚአብሔር ይመካል፣ በታላቅ ትሕትናም ወደ እግዚአብሔር እስከ ሰማይ ሲመነጥቅ የተሰማውን ልዩ ተመክሮ ይተርካል፣ “እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ” (ኍ 2)፣ ይህንን ሊተረክ የማይቻል ፍጻሜ ለመተረክ ቅዱስ ጳውሎስ የሚጠቀመው ዘይቤና ሰዋስው ለየት ይላል፣ ስለገዛ ራሱ ሲናገር በሶስተኛ አካል እንዲህ ሲል ይተርካል፣ አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር ገነት፤ መንግሥተ ሰማያት ተነጠቀ ይላል፣ አስተንትኖው እጅግ ጥልቅና የጦፈ በመኖሩ ሐዋርያው የግልጸቱ ይዘት አያስታውስም፤ ነገር ግን ጌታ እንዴት ባለ አግባብ ከነጭራሹ እንደተቆጣጠረውና ልክ ወደ ክርስትና ሲገባ በደማስቆስ መንገድ እንዳደረገው እንዴት ወደ እርሱ እንደሳበው የሚያመለክቱ ሁኔታዎችና ነገሮች ዘወትር አልረሳቸውም (ፊል 3፤12 ተመልከት)፣
ቅዱስ ጳውሎስ በተቀበላቸው ግልጸቶች ታላቅነት እንዳይታበይ በገዛ ሰውነቱ የሥጋ መውጊያ ተሸክመዋል፤ ከዚሁ ከሰይጣን መል እክተኛ የተሰጠው አሰቃቂ የሥጋ መውጊያ ስቃይ ነጻ እንዲሆን ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ኃይል እንዲሰጠው ይለምናል፣(2ቆሮ 12፡7)፣ እርሱ እንደሚያመለክተው ጌታ ይህንን ፈተና እንዲያርቅለት ለሶስት ጊዜ ያህል ደጋግሞ ለመነ፣ በዚህ ሁኔታ ጥልቅ በሆነ መንገድ ስለ እግዚአብሔር ሲያተነትን ሳለ “ሰው ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ” (ኁ 4)፤ ለልመናውም መልስ አገኘ፣ ከሙታን ተለይቶ የተነሣውም ጥርት ያለና እርግጠኛ ቃል ይሰጠዋል፤ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኃይሌ የሚገለጠው በአንተ ደካማነት ነው” (ኍ 9) ይለዋል፣
ቅዱስ ጳውሎስ በእነዚህ ቃላት የሚያደርገው ሐተታ ሊያስደንቀን ይችላል፤ ነገር ግን እውነተኛ የወንጌል ሐዋርያ መሆን ማለት ምን ማለት መሆኑ እንደተረዳ ይገልጣል፣ ስለሆነም እንዲህ ይላል፣ “እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትርም በጭንቀትም ደስ ይለኛሌ፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና።” (ኍ.9-10)፣ ይህ ማለት በተግባሮቹ ሳይሆን በድካሙ በሚሠራው የኢየሱስ ክርስቶስ ተግባር ይመካል፣ ይህ በእግዚአብሔር ግልጸት ፊት የሚታየው ጥልቅ ትሕትናና እምነት ለእኛም በጸሎታችንና በኑሮአችን ጊዜ ከእግዚአብሔር እና ከድካሞቻችን ጋር ላለን ግኑኝነት መሠረታውያን ስለሆኑ ስለእነዚሁ ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቶስን ሊያበስር ወደ ምዕራባዊው ክፍለ ዓለም ከመጓዙ በፊት በጽሞናና በአስተንትኖ ያሳለፋቸው ዓመታት አንዴ እንመልከት፣
ለመሆኑ ሐዋርያው ስለ የትኛው ደካማነት ይናገራል፧ ይህ ሥጋን እንደ እሾህ የሚወጋ ምን ይሆን፧ አናውቀውም እሱም አይነግረንም፤ ነገር ግን የሐዋርያው ባህርይ ክርስቶስን በመከተልና ወንጌሉን በመስበክ የሚያጋጥመን እያንዳንዱ ውጣ ውረድ ጌታ ባንተ እንዲሰራ ክፍት በመሆን ሊሸነፍ እንደሚችል ያስረዳል፣ ቅዱስ ጳውሎስ ታላላቅ ነገሮችን ያደረገ ጌታ እንጂ እርሱ ስላልሆነ “የማይጠቅም አገልጋይ” (ሉቃ 17፡10) መሆኑን እና እግዚአብሔር የጸጋው ሃብቱን እና ኃይልን የሚያኖርበት “የሸክላ ዕቃ” (2ቆሮ 4፡7) መሆኑን ጥሩ አድርጎ ያውቃል፣ ቅዱስ ጳውሎስ በዚሁ የጦፈ የአስተንትኖ ጸሎት ጊዜ ማንኛውንም ክንዋኔ በተለይ ደግሞ የገዛ ራሱ ደካማነት እና ብቻችን የማይተወን ነገር ግን መጠጊያና ኃይል የሚሆነው የእግዚአብሔር ኃይል በሚገለጥበት ስቃይ ውጣ ውረድ እና ስደትን እንዴት አድርጎ መጋፈጥና መኖር እንዳለበት ጥርት ባለ ሁኔታ ይረዳል፣ እርግጥ ነው ቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ ስቃይ የሆነ የስጋ እሾህ ሊላቀቅ በፈለገ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አይሆንም፤ ለአንተ አስፈላጊ ነው፤ ልትቋመውና መደረግ ያለበትን ለማድረግ በቂ ጸጋ ይኖረሃል ይላል፣ ይህ ለእኛ ይሆናል፣ እግዚአብሔር ከፈትና ነጻ አያደርገንም ነገር ግን በሥቃይ በውጣ ውረድና በስደት እንድንበስል ይረዳናል፣ እምነታችን እንደሚያስተምረን ከእግዚአብሔር ጋር የቆመን እንደሆነ “ብዙ ውጣ ውረዶች ስላሉ የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ ውስጣዊ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል፤ በፈተና ይበስላል፤” (2ቆሮ 4:16)፣ ሐዋርያው ለቆሮንጦስ ማኅበረ ክርስትያን ለእኛም ሳይቀር “”ቀላልና ጊዝያዊ መከራችን ወደር የሌለውን እጅግ ታላቅ የሆነ ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል” (ኁ 17) ይለናል፣ እንደ እውነቱ በሰው ልጅ አነጋገር የውጣ ውረዱ ክብደት ቀላል አልነበረም አስቸጋሪ ነበር፣ ሆኖም ግን ከእግዚአብሔር ፍቅር፤ በእግዚአብሔር የተፈቀረ ከመሆን ታላቅነትእና የምታገኘው ዘላለማዊ ክብር ብዛት ወደር የሌለው መሆኑ ማወቅ ጋር ሲነጻጸር ቀላል ሆኖ ይታያል፣ ስለዚህ ከጌታ ያለን አንድነት ባደገው ቍጥርና ጸሎታችን የጦፈ በሆነበት መጠን እኛም ወደ መሠረታዊው ጉዳይ ገብተን የእግዚአብሔር መንግሥትን እውን የሚያደርጉ የዕሴቶታችን መሣርያነት ኃይል ወይም ችሎታችን ሳይሆን በደካማነታችን ወይንም ለኃላፊነቱ ብቁ ባለመሆናችን አስደናቂ ነገሮች የሚያደርገው እግዚአብሔር መሆኑን እንረዳለን፣ ስለዚህ በቀላሉ በገዛ ራሳችን ተማምነን እንዳንሰራ የሚገታን ትሕትና ሊኖረን ያስፈልጋል፣ ነገር ግን እንደ የሚሰበር የመሬት ዕቃ በጌታ በመተማመን በወይን አትክልት በእርሱ እርዳታ እንድንሰራ ይሁን፣
ቅዱስ ጳውሎስ ሕይወቱን ስር ነቀላዊ በሆነ መንገድ ስለለወጡ ሁለት ልዩ ግልጸቶች ይናገራል፣ እንደምናወቀው አንደኛው በደማስቆስ መንገድ ያጋጠመው በጭባጭ ጥያቄ፤ “ሳውል! ሳውል! ለምን ታሳደናልህ፧”(ሐሥ 9፤4) የሚለው ጥያቄ ሕያውና ህልው ለሆነው ክርስቶስ እንዲያገኛ ያደረገውና የወንጌል ሐዋርያ እንዲሆን የቀረበለትን ጥሪ የሰማበት ሁኔታ ነበር፣ ሁለተኛው ደግሞ ይህ ዛሬ የምናስተነትነው በጸሎት ተመስጦ ሳለ ጌታ የተናገረው ““ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኃይሌ የሚገለጠው በአንተ ደካማነት ነው” የሚሉ ቃላት ናቸው፣ ለከንቱ እንዳንሠራ ዋስትና የሚሰጠን በማይተወን የእግዚብሔር በጎነት ሥራ በመተማመን የሚጸና እምነት ብቻ ነው፣ እንዲህ ባለ መንገድ ቅዱስ ጳውሎስ የጌታ ወንጌልን ለመስፋፋት የሸኘው ኃይል የጌታ ጸጋ ነው፤ ለእኛ ሲል የሞተውንና ከሙታን ተለይቶ የተነሳው ክርስቶስ ዜናን ለማብሰር እንዲችልም ልቡ በኢየሱስ ልብ ውስጥ ገባ፣
እኛም ጸሎት ስናሳርግ እግዚአብሔር በደካማነታችን አድሮ ወደ ስብከተ ወንጌል ኃይል ለውጦት እስዲሠራ መንፈሳችን ለእርሱ እንከፍታለን፣ ይህንን የጌታ በተንኮታኮተ ሰውነቱ ማደር ለመግለጽ ቅዱስ ጳውሎስ የሚጠቀመው የግሪክ አንቀጽ “ኤፒስከኑ” የሚል ነው፤ ትርጉሙም “ደንኳንህን መዘርጋት” ነው፣ ጌታ ድንኳኑ በእኛ ላይ በመካከላችን ማኖር እየቀጠለ ነው፤ ይህም ምሥጢረ ሥጋዌ ነው፣ ሥጋ ሆኖ በሰብአውነታችን ለማደር የመጣው መለኮታዊ ቃል ሊያበራልን እና ሕይወታችንና መላው ዓለምን ለመለወጥ ድንኳኑን በመዘርጋት በእኛ ውስጥ ለመኖር ይፈልጋል፣
በጦፈ መንገድ ስለ እግዚአብሔር በማሰላሰል ቅዱስ ጳውሎስ ያጣጠመው ሁኔታ፤ በደብረ ታቦር ሐዋርያት በብርሃን የሚብለጨልጭና የተለወጠ ጌታን ባዩ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ “መምህር ሆይ! በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው።” ቅዱስ ማርቆስም “እጅግ ስለ ፈሩ የሚለውን አያውቅም ነበር።” ይላል (ማር 9፡5-6) ስለ ጌታ ማስተንተን አስደናቂ ነው፣ የሚያስፈራም ነው፣ አስደናቂ የሚሆንበት ምክንያት እርሱ ወደ እርሱ ስለሚያቀርበንና የፍቅሩ ሰላምንና መልካምነትን ለማጣጣም ወደ ሰማይ ስለሚያመጥቀን፣ አስፈሪ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ ሰብአዊ ድክመታችንና ብቁ አለመሆናችንን ራቁቱን ስለሚያወጣው እንዲሁም ሕይወታችንን በመፈተን በሥጋችን በምትገኘው ተዋጊ እሾህ የተመለከተች ክፋትን ለማሸነፍ የምናሳየው ስንፍና ግልጥ ስለሚሆን ነው፣ ጸሎት በምናሳግበት ጊዜ እና በየዕለቱ ስለጌታ በምናስተነትንበት ጊዜ የእግዚአብሔር ፍቅር ኃይል እናገኛለን፤ በዚህም ቅዱስ ጳውሎስ በሮም ወደ ሚገኙ ክርስትያን “ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።” (ሮሜ 8፡38-39) ብሎ የጻፈው እውነት መሆኑን እንረዳለን፣
በቅልጥፍናችንና በችሎታችን ብቻ የመተማመን አደጋ በሰፈነበት በዚሁ ዓለማችን የእግዚአብሔር ችሎታን ለማግነትና እርሱን ለመስከር የተጠራን ነን፣ እግዚአብሔር ይህን ችሎታው ሕይወታችንን ከክርስቶስ ሕይወት ጋር በማስማማት የምናድግበት በየዕለቱ በምናሳርገው ጸሎት ያስተላልፍልናል፣ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን “በድካም ተሰቅሎአልና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኃይል በሕይወት ይኖራል። እኛ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንደክማለንና፥ ነገር ግን ስለ እናንተ በሆነ በእግዚአብሔር ኃይል ከእርሱ ጋር በሕይወት እንኖራለን።” (2ቆሮ 13፡4) በማለት ያረጋግጥልናል፣
ውዶቼ፧ ባለፈው ዘመን አልበርት ሽቫይጸር የሚባል የፕሮተስታንት የትምህርተ ንባበ መለኮት ሊቅና የሰላም ሽልማት ተሸላሚ “ጳውሎስ ባሕታዊ ነው፣ ከባሕታዊ ሌላ ምንም አይደለም” ይላል፣ ይህ ማለት ክርስቶስን ያፈቀረ በዚህ ፍቅር ከእርሱ ጋር በጽኑ ስለሚተሳሰር “እኔ ሳይሆን ክርስቶስ ነው በእኔ የሚኖረው” እስከማለት ይደርሳል፣ የቅዱስ ጳውሎስ ባሕታዊ ብቃት እርሱ በኖራቸው ልዩ ሁኔታዎች ብቻ አይመሰረትም፤ ነገር ግን ዘወትር በጸጋው ከሚደገፈው እግዚአብሔር በሚያደርገው ዕለታዊና የጦፈ ግኑኝነትም ነው፣ ሰቂለ ኅልናዊ ባሕታውነት ከዓለም አላራቀውም፤ ይበልጥ በየቀኑ ለኽርስቶስ እንዲኖርና ያኔ የነበረችውን ቤተ ክርስትያን እስከ አጽናፈ ዓለም ለማነጽ ኃይል ሰጠው፣ ከእግዚአብሔር ጋር መዋሃድ ከዓለም አያርቅም፤ ነገር ግን በዚህ ዓለም በእውነት ለመኖርና ማድረግ የሚገባንን ለማድረግ ኃይል ይሰጠናል፣ ስለዚህ በዕለታዊ የጸሎት ሕይወታችን ምናልባት ልዩ የሰቂለ ኅልና ግዝያት ሊኖሩን ይችላሉ፤ ነገር ግን ጽኑ መሆንና ከእግዚአብሔር ጋር ላለን ግኑኝነት ታማኞች መሆን ያስፈልጋል፣ በተለይም መንፈሳዊ ድርቀት በሚሰማን ጊዜ ውጣ ውረድና ስቃይ በሚበሳበት ጊዜ እንዲሁም እግዚአብሔር የተለየን ሆኖ በሚሰማን ጊዜ ጽናትና ታማኝነት ያስፈልጋል፣ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በክርስቶስ ፍቅር የተያዝን እንደሆነ ብቻ ነው እያንዳንዱን መከራ ለመጋፈጥ የምንችለው፤ እና በመተማመን እንደ እርሱ “ኃይል በሚሰጠን በእርሱ ሁሉን እንችላለን” (ፊሊ 4፡13) ለማለት እንችላለን፣ ስለዚህ ለጸሎት በሰጠነው ጊዜና ቦታ መጠን ሕይወታችን እየተለወጠችና በተጨባጭ እግዚአብሔር ፍቅር ኃይል ስትለማ እናያለን፣ ለምሳሌ እናት ተረዛ ዘካልኩታ ያጋጠማት እንዲሁ ነው፣ ማዘር ተረዛ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ባገጠማባት ጊዜም ይሁን ምንም እንኳ ኃይለ ደካማ ብትሆን ስለ ኢየሱስ በማስተንትን የነገሮች የመጨረሻው ምክንያትና በምታገለግላቸው ድሆች የሚገለጥ ሊታመን የማይቻል ኃይል ታገን ነበር፣ እላይ እንዳልኩት ስለ ክርስቶስ ማስተንተን ከዓለም አያወጣንም፣ ይልቅስ በሰው ልጆች ኑሮ እንድንሳተፍ ያደርገናል፣ ምክንያቱም ጌታ በጸሎት ወደ እርሱ እያቀረበን በፍቅሩ በእያንዳንዱ ሰው ጐን ሆነን ቅርበታችንን እውን ያደርገዋል፣ እግዚአብሔር ይስጥልን፣









All the contents on this site are copyrighted ©.