2012-04-02 17:39:49

በዓለ ሆሳዕና በላቲን ሥርዓተ አምልኮ


የላቲን ሥርዓተ አምልኮ የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ትናንትና በዓለ ሆሳዕና በታላቅ ድምቀት አከበረች። ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ትናንትና በዓሉን ለማክበርና ከዚህ በዓል ጋር የተያያዘውን ዓመታዊው የወጣቶች ቀን ለማስታወስ፡ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ከሮማና ከመላው ዓለም የተሰበሰቡ ወጣቶች ከአፋፍ እስከ አፋፍ በሞሉበት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ መሥዋዕተ ቅዳሴ አሳርገዋል። በዓሉን አመልክተው በሰጡት ስብከትና ለወጣቶች ባቀረቡት ጥሪ “ለታላቁ የእግዚአብሔር ሥጦታ የሆነው፡ ጌታ ኢየሱስ በዚሁ ሶሙነ ሕማማት የሚያሳድሰውን የደህንነት ሥጦታ፡ ራስን በመስጠት ብቻ ሊመለስ ይችላል” ሲሉ የሰሙነ ሕማማት ትርጉምና መወሰድ ያለበት እርምጃ አሳስበዋል። ትላንትና በአደባባዩ በነበረው ሥርዓት፡ የወይራና የዘንባባ ቅርጫፎች በማወዛወዝ ዑደተ ሆሳዕና ማድረግ፡ የጌታን ሕማማት እንደገና በማስታወስ የወንጌላውያን ትረካ በጥሞና ማዳመጥ፡ እንዲሁም መሥዋዕተ ቅዳሴ በመጨረሻም የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮና ሐዋርያዊ ቡራኬ፡ በተለይ ከመላው ዓለም ለተሰበሰቡ ወጣቶች ልዩ ስሜት ፈጥረዋል።
ቅዱሰነታቸው ባደረጉት ስብከት በዓለ ሆሳዕና “የሰሙነ ሕማማት መባቻ ታላቅ በር ነው። ኢየሱስ ተልእኮውን ለማገባደድ ወደ ኢየሩሳሌም በታላቅ ክብር ይገባል። ቅዱሳን ጽሑፎች ያሉት ይፈጸም ዘንድ ደግሞ፡ በመስቀል ይንጠለጠላል። ይህ መስቀል ዘለዓለማዊ ግርማዊነቱን በመልበስ ለዘለዓለም መንግሥቱን የሚያስተዳድርበት ዙፋን ነው። ለዚህ ታላቅ ክብር በር የሚከፍቱ ሁለት ድንቅ ነገሮች ተመልክተዋል፡ አንደኛው የዕውሩ በርተመዎስ መፈወስ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ መላዋ ኢየሩሳሌም “ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር ሆሳዕና ለወልደ ዳዊት፡ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ብሩክ ነው፡ ለዳዊት ልጅ ሆሳዕና” በማለት በታላቅ ክብር ይጠባበቁት የነበሩት መሲሕ መምጣት ሲያበስሩ፡ ብሩክ ተብሎ በሕዝቡ የታወጀው ኢየሱስ፡ በእርሱ ዘመደ አዳም ሁሉ ተባረከ።” በማለት የሆሳዕና ዕለት ታሪክ ከዘረዘሩ በኋላ የዚህ ታሪካዊ ዕለት መልእክት ምን ይሆ፡ ዛሬ ለኛ የሚለው ምንድር ነው፡ በማለት ጠይቀው ይህንን መልስ ሰጥተዋል፧ “የዚህ ዕለት መልእክት ባጠቃላይ ዓለማችንን በሚያቋቋሙ የተለያዩ የሰው ልጅ ባህሎችና ሥልጣኔዎች እንዲሁም በሰው ልጅ ዘር ያለን አመለካከትን ለማስተካከል ጥሪ የሚያቀርብ ነው። ማንኛው አማኝ ከክርስቶስ የሚያገኘው አመለካከት የቡራኬ አመለካከት መሆን አለበት። ብልሃትና ፍቅር የተሞላበት አመለካከት፡ የዓለማችን መልካምነት የሚረዳና መንኮታኮትዋን አውቆ በርኅራኄ የሚንከባከባት አመለካከት መሆን አለበት። እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ለሰው ልጆች እና የእጁ ሥራ ለሆነችው ተፈጥሮ ያለው አመለካከት በዚሁ ዓይነት አመለካከት ይንጸባረቃል።” በማለት ዋናውን የበዓሉ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ ወደ የእያንዳንዱ አማኝ ሕይወት መለስ ብለው፡ የሚከተሉትን ኣንገብጋቢ ጥያቄዎች አቅረበዋል። “ክርስቶስን በሚጠራ ሰው ልብ ምን አለ፧ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ማን ነው፧ እግዚአብሔርን የሚመለከት አስተያየታችን ምን ይመስላል፧ የሚሉ ጥያቄዎች በዚሁ ሶሙነ ሕማማት ማስተንተንና መመለስ ያለብን መሠረታዊ ጥያቄዎች መሆናቸውን እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል። “በዚሁ ሳምንት መስቀልን እንደመንበረ መንግሥት የመረጠ ክርስቶስን ለመከተል ተጠርተናል። የዚህ ዓለም ደስታ የሚያረጋግጥ መሲሕ ሳይሆን ሰማያዊ ደስታ፡ የእግዚአብሔር ብፅዕና የሚያረጋግጥልን መሲሕ ለመከተል የተጠራን ነን። በዚህ አስደናቂ ግልጸት በእውነት የምንጠባበቃቸው ምን ናቸው፧ ዛሬ በዓለ ሆሳዕናን ለማክበርና ሶሙነ ሕማማትን ለመጀመር እዚህ ጋር ይዘናቸው የመጣን ጥልቅ የሆኑ ፍላጎቶች የትኞቹ ይሆናሉ፧ ብለን ገዛ ራስችንን መጠየቅ አለብን፧ በማለት ለአስተንትኖ ከጠሩ በኋላ ሃሳባቸውን ወደ ወጣቶቹ በማዞር “በ18 ዓመት ዕድሜዋ የክርስቶስ ለመሆን የመወሰን የእምነትና የፍቅር ድፍረት የነበራት ቅድስት ክያራ ዘአሲዚ ምሳሌ” እንዲከተሉ አደራ ብለዋል።
ቅዱስነታቸው አያያዘው “የሆሳዕና በዓል ቍርጡን የመወሰን ዕለት ይሁንላችሁ። ጌታን ለመቀበልና እስከ መጨረጻ እንድትከተሉት የፋሲካ ሞቱና ትንሣኤው የክርስትያን ሕይወታችሁ ትርጉም እንዲሆን የምትወስኑት ዕለት ነው። ይህ ውሳኔ በሕይወታችሁ ደስታ የሚያመጣ ውሳኔ ነውና። በዚሁ ሳምንት የሰው ልጅ አእምሮ ከሚረዳው በላይ የሆኑትን ታላላቅ ስጦታዎች ማለትም የጌታ ኢየሱስ የሕይወት ስጦታ የሰውነት ስጦታ የደም ስጦታ እና የፍቅር ስጦታ ስንቀበል ለጌታ የክብርና ምስጋና የማቅረብ ስሜት ሊወረን ይገባል። ሆኖም ግን ይህን ያህል ለሚልቀው ስጦታ በቂና ተገቢ ስጦታ በማቅረብ መመለስ አለብን፡ ይህንን ለማድረግ የምንችለው ደግሞ ገዛ ራሳችንን በመስጠትም ይሁን፡ ግዝያችንን ለእርሱ መሥዋዕት በማቅረብም ይሁን፡ ጸሎታችንን በማቅረብ እና ለእኛ ሲል ከሚሰቃይ ከሚሞት እና ለእኛ ሲል ከሞት ከሚነሣ ክርስቶስ ጋር ካለን ጥልቅ ፍቅር ፍጹም አንድነት በመፍጠር ልናደርገው እንችላለን።” ሲሉ ሰሙነ ሕማማትን እንዴት ባለ ጥልቅ መንፈሳውነት ማሳለፍ እንዳለብን አመልክተዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.