2012-03-22 09:46:44

የአሕዛብ ቅጥር ግቢ፦ በፓሌርሞ ‘ውይይት እና የጸረ ወንጀል ትግል ለማጎልበት’


ጳጳሳዊ የባህል ጉዳይ ምክር ቤት “Cortile dei Gentili-የአሕዛብ ቅጥር ግቢ” በሚል መጠሪያ ርእስ ሥር የተመራ የአለማችን አበይት እና አንገብጋቢ ርእሰ ጉዳዮች መሠረት በአማኞች እና በኢአማኒያን መካከል ውይይት ለማነቃቃት፣ እምነትን እና ባህል የሚያወያይ፣ እምነት እና አልቦ እምነት በአንድ አንገብጋቢ ርእስ ሥር ተገናኘተው እንዲወያዩ በሚል እቅድ መሠረት በቦሎኛ በፓሪስ በቡካሬስት በፊረንዘ በሮማና በቲራን ካካሄዳቸው አውደ ጥናቶች በመቀጠል እ.ኤ.አ. ከ መጋቢት 29 ቀን እስከ መጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢጣሊያ ፓለርሞ ከተማ “የሕጋዊነት ባህልና ኅብረሃይማኖተኛ ኅብረተሰብ” በሚል ርእስ ሥር የተመራ አውደ ጥናት እንደሚያካሂድ የባህል ጉዳይ የሚከታተለው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር ብፁዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ ትላትና ከሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ለመረዳት ተችለዋል።
ፓሌርሞ በሚገኘው የሞንረያለ ካቴድራል ተገኝተው አውደ ጥናቱን የሚከፍቱት ብፁዕ ካርዲናል ራቫዚ፣ ኅብረሰብ ባህል እና እምነት ርእስ ዙሪያ አስተምህሮ እንደሚያቀርቡ ሲገለጥ፣ ይኽ ደግሞ ሕጋዊነት እና በኅብረሃይማኖት ውይይት ላይ ያነጣጠረ ነው ብለዋል። ሕጋዊነት የሚለው ቃል በኢጣሊያ በተለይ ደግሞ በሲቺሊያ ሕገ ወጥ ባህል የሚያስፋፋው የወንጀል ቡድን ‘ማፊያ’ የማፍያነት ባህል በፓሌርሞ የሚታጠር ሳይሆን ኵላዊነት ባህርይ ያለውም ነው። ሕገ ወጥነት የአንድ አገር ባህል ሳይሆን በሕገ ወጥነት በመኖር የሚንጸባረቅ ጸረ ሕጋዊነት ባህል ነው። ይኸንን ሕገ ወጥነት ባህል ለመዋጋት አማኒያን እና ኢአማንያን የሚሰጡት አስተዋጽኦ የአሕዛብ ቅጥር ግቢ በተሰየመው መድረክ በማገናኘት ለማወያየት ያቀደ መሆኑ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስምረውበታል።
በዚህ የሥነ ፍልስፍና፣ ሥነ ሕግ፣ ቲዮሎጊያ ሥነ ታሪክ ሥነ ጽሑፍ ሊቃውንቶችን የሚያሳትፈው የጋራው ውይይት እ.ኤ.አ. መጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በስተሪ ሕንፃ የፓሌርሞ መንበረ ጥበብ የጉባኤ አዳራሽ የሚካሄድ መሆኑ ገልጠው፣ በዚህ የፓርሌርሞ አውደ ጥናት መለኮታዊ ሕግ እና ሰብአዊ ፍትህ፣ ሃይማኖቶች እና ሰብአዊ መብት እና ክብር፣ ኅብረአዊነት እና ኵላዊነት፣ ሃይማኖቶች እና ማኅበራዊ ሥፍራ፣ በተሰኙት ርእሰ ጉዳዮች ሥር አስተምህሮ እንደሚቀርብና አስተምህሮ ከሚሰጡት ውስጥ ብፁዕ ካርዲናል ዣን ልዊስ ታውራን፣ ፈላስፋ ረሚ ብራገ፣ የሥነ ማእከላዊ ዘመን ታሪክ ሊቅ ሄንሪ ብረሽ የሥነ ማፊያ ባህል ሊቅ ሳልቫቶረ ሉፖ፣ በፓሌርሞ የጸረ ማፊያ የበላይ ፍርድ ቤት ተጠሪ ምክትል ሻኪታኖ እንደሚገኙበትም አስታውቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የባህል ጉዳይ ተነከባካቢው ጳጳሳዊ ምክር ቤት የአሕዛብ ቅጥር ግቢ በተሰኘው መጠሪያ የሚያካሂደው ባህላዊ መርሃ ግብሮችን ኮርቲለደይጀንቲሊ ነጥብ ኮም በተሰየመው ድረ ገጽ አማካኘንትም ለመከታተል እንደምትችሉ በዚሁ አጋጣሚ ለማስታወቅ እንወዳለን።








All the contents on this site are copyrighted ©.