2012-01-06 12:40:27

ታህሳስ 24 ቀን 2004 ዓ.ም
ታላቅ የመዝሙር ኮንሰርት ዝግጅት ተካሔደ


በአዲስ አበባ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ቅጥር ጊቢ ውስጥ ሊገነባ ለታቀደው አዳራሽ በደተደረገው እንቅስቃሴ እና በተገኘው ውጤት እግዚአብሔር አምላክን ለማመስገን፣ በቀጣይ ሥራው ያለውጣውረድ እንዲሔድ ጸሎት ለማድረስና ሁለገብ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ምሥጋና ለማቅረብ እሁድ ታህሳስ 22 ቀን 2004 ዓ.ም በቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ታላቅ የመዝሙር ኮንሰርት ዝግጅት ተካሂዷል፡፡
በዕለቱ ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ ክቡራን ካህናት፣ ከቁምስኖች የተወጣጡ ዘማሪያንና ምዕመናን ተገኝተዋል፡፡ ብፁዕ አባታችን ቁምስናውና የሆሳዕና ሕብረት በማድረግ ላይ ያሉትን እንቅስቃሴ በማድነቅ ግንባታው አስፈላጊ በመሆኑ ሁሉም ከጎናቸው እንዲቆም አሳስበዋል፡፡
ክቡር አባ እዮብ ኃ/ሚካኤል የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያ ቆመስና አቶ አሥራት ኃ/ማርያም ከሆሳዕና ሕብረት በበኩላቸው ብፁዕ አባታችን ላበረከቱት የገንዘብ ሥጦታና አባታዊ ምክር ከፍ ያለ ምሥጋና በማቅረብ ግንባታውን ለማከናወን ይረዳ ዘንድ ቤተሰቦች፣ ግለሰቦች፣ ገዳማትና ድርጅቶች ላበረከቱት አስተዋጽኦም ላቅ ያለ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ አዳራሹን ለመገንባት በተደረገው እንቅስቃሴ በጎ ምላሽ ቢኖርም ግንባታን ለማከናወን የሚያስፈልገው ብር 6.6 ሚሊዮን በመሆኑ በቀጣይም የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ለዚህ በጎ ዓላማ በጸሎትና በገንዘብ እገዛቸውን እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ቁምስኖች የተወጣጡ ዘማሪያን ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ዝማሬዎችን በማቅረብ ዕለቱ በምስጋናና በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ደምቆ እንደዋለ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሪፖርተር/ ኤዲተር፡- ራሔል ዓቢይ

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት








All the contents on this site are copyrighted ©.