2012-01-05 09:45:29

ታህሳስ 26 ቀን 2004 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ የ2004 ዓ.ም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓል ምክንያት በማድረግ የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላለፉ፡፡
በዛሬው ዕለት ከብዙኃን መገናኛ ለተወጣጡ ጋዜጠኞች ይህንኑ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ነው ፡፡


በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !!
ክቡራን ምዕመናን
በአገር ውስጥና በተለያዩ አገራት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት
ክቡራን የቤተክርስቲያን አገልጋዮችና
በጎ ፊቃድ ያላችሁ ወገኖች ሁሉ፡
’’ነገር ግን የተወሰነ ዘመን በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከልን እርሱ ከሴት ተወለደ ለሕግም ታዛዥ ሆነ’’ (ገላ 4፡4)
የተወደዳችሁ ምዕመናንና መላው የአገራችን የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ ከሁሉም አስቀድሜ እንኳን ለ2004 ዓ.ም የጌታችን የመድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ በማለት በራሴና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስም መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ቅዱስ ዮሴፍ በነብዩ በሚከያስ የተነገረው ትንቢት እንዲፈፀም ወደ ቤተልሔም ለምዝገባ በደረሱ ጊዜ የእንግዳ ማረፊያ ሁሉ ተይዞ ስለነበር የሚያድሩበት ሥፍራ አጡ፡፡ በከብቶች በረት ውስጥ ማደር ግድ ሆነባቸው በዚያም እመቤታችን ኢየሱስን ወለደች፡፡ በእግዚአብሔር ዙፋን ተቀምጦ የነበረው ጌታ በበረት ውስጥ ታናሽና ድሃ ሆኖ ተወለደ፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ልደትም አማኑኤል ወልደ እግዚአብሔር በሰዎች መካከል አደረ፡፡
ጌታችን የዓለም ብርሃን እንደሆነ ለኛ ለሰዎች የዓለም ብርሃን ለመሆን መጥቶአል፤ እኛም የሱን ብርሃን ተቀብለን ለሰዎች እንድናበራ ይጋብዘናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌያችን ነው፡፡ በመሆኑም አቋማችን የክርስቶስን ሊመስል ይገባል፡፡ ሰማያዊ ጌትነቱን ክብሩን ትቶ ለኛ ደኅንነት ሲል እንደ መጣ የእርሱን በዓል ስናከብር በክርስቶስና በመንፈስ እንጂ በሥጋ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ በክርስቶስ መሆናችን የሚገለጠው የእኛ ዓላማ ክርስቶስን ለማወቅና በእርሱም መንገድ ለመሄድ ሁላችንም ፍቃደኞች ሆነን ስንገኝ ነው፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወታችን ምሳሌያችን፣ ብርታታችን እንዲሁም የእምነታችንና የተስፋችን ምንጭ ነው፡፡ ስለሆነም እግዚአብሔር በክርስቶስ የሰጠንን ፀጋና መንፈሳዊ በረከት እንድናውቅና በመልካም አኗኗር እንድንኖር ያስፈልጋል፡፡ በእርሱ ያመኑትን አንድ በማድረግ ሰላማቸው ሆኗል፡፡ በመሆኑም ክርስቲያኖች ሁላችን ራሳችንን በክርስቶስ ልደት አማካይነት ለእግዚአብሔር ልንሰጥ ይገባል፡፡
ሐዋርያው ጰውሎስ ወደ ቆላስያሰ ሰዎች በጻፋው መልዕክት ላይ ’’ክብር የሚገኝበት ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ነው’’ (1፡27) ይላል ፡፡ እኛ የክርስቶስን ልደት ተቀብለን ክርስትናችንን በመያዝ ክርስቶስን ለዓለም ለማወጅ ከእግዚአብሔር እንደተወለድን ልጆች በመኖር መመስከር ይኖርብናል፡፡ እንደዚሁም በፍቅር፤ በንጽህናና በእግዚአብሔር ቃል ብርሃን መመላለስ እንደሚኖርብን ላስገነዝብ እወዳለሁ፡፡ በእምነት የክርስቶስ ወገን የሆንን ሁላችን እርሱ ባደረገልን ነገር በሕይወት እንኖራለን፣ ምክንያቱም እርሱ ሕይወታችንና የእምነታችን ምንጭ ሆኗልና፡፡
የጌታን ልደት ስናከብር እግዚአብሔር ከኛ የሚፈልገው ነገር በትንቢተ ሚኪያስ እንደምናገኘው ’’እርሱ ገና የሚፈልገው ትክክል የሆነውን ነገር እንድናደርግ ደግነት የተሞላበትን ፍቅር እንድናሳይና ከአምላካችን ጋር በፍፁም ትህትና እንድራመድ ነው’’ (6፡8) የሚለውን ካላደረግንና ካልፈፀምን በልባችንም ካልጠበቅነው የርሱ ነን ልንል አንችልም፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ አገራችን በተጎናፀፈችው ሰላም ተመርኩዛ የዕድገትና የመሠረታዊ ለውጥ ጉዞ ቀይሳ ተግባራዊ ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት እያደነቅን መላው የአገራችን ሕዝቦች አንድ ልብና አንድ መንፈስ ሆነው ለተግባራዊነቱ ይረባረቡ ዘንድ አደራ ለማለት እወዳለሁ፡፡
ኢየሱስ በእውነተኛ ቤተሰብ ውስጥ ተወለደ፤ ኖረ፤ የቤተሰብን ባህሪያት ሁሉ ተቀበለ፤ ለትዳር ተቋም ትልቁን ክብር ሰጠ፤ የአዲሱ ኪዳን ምስጢርም አደረገው (ማቴ 19፡3-9);; ቤተሰብ በአንድ ወንድና በአንድ ሴት መካከል በተደረገ ጋብቻ ላይ የተመሰረተ ማህበራዊ ገጽታ ያለው መለኮታዊ ተቋም ነው;; በእግዚአብሔር ከፀናው የጋብቻ ሥርዓት ውጭ ያለውን ማንኛውንም ተቃራኒ ግንኙነት ቤተክርስቲያናችን ጥንትም አሁንም የማትቀበለውና የምታወግዘው ነው፡፡
አገር መልማትና ማደግ የምትችለው ጤናማ ዜጎች ሲኖሩ ነውና በጤና መስክ እየታዩ ያሉ ለውጦች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፤ ህብረተሰቡም ስለ ኤች አይ ቪ ኤድስ ያለው ግንዛቤ ከፍ እያለ በመምጣቱ በዚህ በኩል የአገራችን ገጽታ እየተለወጠ በመሄዱ አሁንም መላው ህዝብ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በመፍራት ተወስኖ ከተያዘና ከተንቀሳቀሰ እራሱንም በጋብቻ ካጸና የበሽታው መስፋፋት በአጭር ጊዜ ከአገራችን እንደሚጠፋ እምነታችን ነው፡፡ መንግሥትም ለዚህ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀሱን ከልብ እያደነቅን አሁንም ከሃይማኖት ተቋማትና ከበጎ አድራጊ ድርጅቶች ጋር ተባብሮ በሽታዎችን በመከላከልና በበሽታ የተያዙትን ደግሞ አስፈላጊውን የመድኃኒት አቅርቦትና እንክብካቤ የሚያገኙበትን መንገድ በበለጠ አጠንክሮ ይሠራ ዘንድ አደራ እላለሁ ፡፡
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፣ በተለይም በአሁኑ ጊዜ በመንፈሳዊም ሆነ በዓለማዊ
ጉዳይ ለሁላችንም አነጋጋሪና አሳሳቢ የሆነው በሴቶች እናቶቻችን፤ እህቶቻችንና ልጆቻችን ላይ እየተፈፀመ ያለው አስከፊ የጥቃት ድርጊት ነው። የሰው ሕይወት ከቡርና ውድ መሆኑን አውቀን አንዱ የሌላውን ሕይወት እንደራሱ ሕይወት በመመልከት ከወንጀልና ከጥፋት ራሳቸንን በመጠበቅ፤ያለመግባባት ካለ ጉዳያችንንም በንግግርና በውይይት በመፍታት፤ ግድ የሌሽነትን አስወግደን እራሳችንን በመቆጣጠርና በመግዛት እንድንኖር በቤተክርስቲያናችን ስም አደራ እላለሁ፡፡
የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጆች የሆኑ የሃይማኖታችን ምዕመናኖች በሙሉ በዚች የተቀደሰች በዓል አማካይነት እርስ በርስ በመፋቀር የተቀደሰ በዓል እንድናከብርና ድሆችን፣ አስተዋሽ ያጡትን በማስታወስ እንደተለመደው የአቅማችንን ሁሉ በማድረግ በማብላትና በማጠጣት በዓሉ የደስታና የፍሰሓ በዓል ሆኖ እንዲያልፍ ለአምላካችሁ ያላቸሁን ፍቅር በመጨመር በረከቱንና ፀጋውን ታገኙበት ዘንድ አደራ እላለሁ፡፡
በመጨራሻም በሆስፒታልና በቤታችሁ በህመም ላይ ለምትገኙ፣በማረሚያ ቤት ለምትገኙ፤ በሥራና
በተለያዩ ምክንያት ከወላጆች ከዘመድ እርቃችሁ ለምትገኙት፣ ለአገር ደኅንነትና ሰላም ዳር ድንበርን በማስከበር ሥራ ላይ ለምትገኙት ወገኖች በሙሉ በድጋሚ እንኳን ለ2004 ዓ.ም የጌታችን የመዲኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልዕክቴን አስተላልፋለሁ ፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ !



+ ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል
ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

ሪፖርተር/ ኤዲተር፡- ራሔል ዓቢይ
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት
ማህበራዊና ህዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ








All the contents on this site are copyrighted ©.