2011-12-23 16:30:42

የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሳምንታዊ የዕለተ ረቡዕ አጠቃላይ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ (እ.ኤ.አ. 21/12/2011)


ውድ ውንድሞችና እኅቶች፤ የጌታ ልደት ለማክበር ጥቂት ቀኖች በቀሩት ባቀርበው ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የምቀበላችሁ በታላቅ ደስታ ነው። በዚህ ቀናት በሁላችን አንደበት የሚቀርቡ ሰላምታዎች “መልካም ልደት! የልደት በዓላት መልካም ምኞት!” የሚሉ ናቸው። በዘመናዊው ኅብረተሰብ የሚደረጉ የስጦታ ልውውጦች የበዓሉ ጥልቅ ትርጉም እንዳያደበዝዙት፤ እንዲሁም በዓሉ የልብ አውታሮችን በሚነኩ በአፍአዊ ነገሮች እንዳይዋጥ መጠንቀቅ አለብን። እርግጥ ነው እነኚህ አፍአዊ ምልክቶች መልካም ናቸው፣ ደስም ያሰኛሉ፣ ሆኖም ግን እነኚህ ነገሮች ከዋናው ነገር የሚያደናቅፉ ሳይሆን ይህንን ቅዱስና ክርስትያናዊ የሆነሆነው የልደት ዘመን በእውነተኛ መንፈስ እንድንኖረው ሲያግዙን ደስታችን ደግሞ አፍአዊ ሳይሆን ጥልቅ እንዲሆን እንዲያግዙን ይሁን።

በልደት በዓል ሥርዓተ አምልኮ ቤተ ክርስትያን በትልቁ የምሥጢረ ሥጋዌ ምሥጢር ታቀርበናለች፣ በዓለ ልደት የኢየሱስ ልደት ዓመታዊ በዓል የምናስታውስበት እንደማንም አጋጣሚም ቢሆን ነገር ግን ከዚህ በበለጠ አኳሃን የሰው ልጅ ታሪክ የለወጠና ገና የሚለውጥ ምሥጢር የምናከብርበት በዓል ነው፣ “እግዚአብሔር ራሱ ከእኛ ጋር ለመኖር መጣ” (ዮሐ 1፤14) በእውነት ከእኛ አንዱ ሆነ፣ ይህ ምሥጢር እምነታችንና ህልውናችንን ይመለክታል፣ ይህንን ምሥጢር ሁሌ ሥርዓተ አምልኮ በምናሳርግበት ግዜ በተለይም መሥዋዕተ ቅዳሴ በምናሳርግበት ግዜ በእውነት እንኖረዋለን። አንዳንድ ሰው የሚከተለውን ጥያቄ ሊያኖር ይችላል፣ ከረዥም ግዜ በፊት የተፈጸመውን ነገር እንዴት አሁን ልኖረው እችላለሁ? ከሁለት ሺ ዓመታት በፊት በተፈጸመው የእግዚአብሔር ልጅ ልደት እንዴት አድርጌ ፍርያም በሆነ ነገር ለመሳተፍ እችላለሁ? በበዓለ ልደት ሌሊት በሚያርገው መሥዋዕተ ቅዳሴ “ዮም ተወልደ መድኃኒነ - መድኃኒታችን ዛሬ ተወለደ” የሚለውን ምልጣን እንደጋግማለን። ይህ “ዛሬ” የሚለው ተውሳከ ግሥ በልደት ሥርዓቶች ተደጋግሞ እናገኘዋለን የወልደ እግዚአብሔር ምሥጢረ ሥጋዌንና በእርሱ የመጣልንን ደኅንነት በማስታወስ የኢየሱስ ልደትን ያመለክታል። በሥርዓተ አምልኮ ይህ ፍጻሜ ግዜንና ቦታን ተሻግሮ ያንን ፍጻሜ በዛች ቅጽበት እውን ያደርገዋል፣ ይህ ፍጻሜ የሚያስከትለው ፍሬ ጨለማ በወረራቸው ቀኖችም ይሁን ለዓመታትና ለዘመናት እውን እየሆኑ ናቸው። ዮም ተወልደ ኢየሱስ - ኢየሱስ ዛሬ ተወለደ ሲል ሥርዓተ አምልኮው ትርጉም የሌለው ሐረግ አይደለም የሚደጋግመው ነገር ግን የሚያሰምርበት ኣውነት፣ ይህ ልደት መላውን ታሪክ እንደሚያካትትና እንደሚዘልቅ ነው። ዛሬም በሥርዓተ አምልኮ ልንደርስበት ያለብን አንድ ሁኔታ አለ። የልደት በዓል ማክበር ለእኛ ለአማኞች፣ እግዚአብሔር ሥጋ ለብሶ በእውነት በእኛ መሀከል የመኖሩን እርግጠኝነት ያሳድሳል፣ ከአባቱ ጋር ሰማየ ሰማያት ካለ ዘወትር አጠጋባችን ነው። በቤተልሔም በተወለደው ሕፃን እግዚአብሔር በእውነት ወደ ሰው ልጅ ቀርበዋል፣ እንደኛ ሰው ስለሆነም አሁኑኑ በዚሁ መጨረሻ በሌለው ዛሬ ልናገኘው እንችላለን።

የዘመናችን ሰው በተጨባጭ ነገርና በሳይንሳዊ ሙከራ በመጠጋት ዓይነ ልቦናውን በእግዚአብሔር ዓለም ለማስፋት ስለሚያስቸግረው ስለዚህ ነገር ጥቂት ለማጥበቅ እወዳለሁ። እርግጥ ነው የሰው ልጅ ደኅንነት በታሪክ ሊታወቅና ትክክለኛ በሆነው በናዝራዊው ኢየሱስ ልደት ተፈጽመዋል፣ ሆኖም ግን ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፣ ራሱ እግዚአብሔር ነው፣ ከሰው ልጅ ጋር የተናገረ፣ ተአምር ያሳየና በደኅንነት ታሪክ ሁሉ የመራው ብቻ ሳይሆን ሥጋ በመልበስ ሰው ሆነ ሰው ሆኖም ይኖራል። ከእርሱ ጋር ዛሬ መገናኘትን እውን እንዲያደርግ ዘለዓለማዊው በግዜና በቦታ እንዲወሰን በታሪካችን ገባ። የልደት ሥርዓተ አምልኮ ጽሑፎች በክርስቶስ የተከናወኑ የደኅንነት ተግባሮች ዘወትር ሕያው እንደሆኑ ለመረዳት ይረዱናል፣ ለማንኛውም ሰውና ለሁሉም የሰው ልጆችም አስፈላጊዎች ናቸው። “ዛሬ መድኅን ተወልዶልናል” የሚሉ ቃላትን ስናወሳ ወይንም ስንሰማ ባዶ የሆነ በዘልማድ የሚወራ ነገር አይደለም የምንጠቀመው፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ለእኔና ለእያንዳንዱ ሰው ይህንን “ዛሬ” አሁን ብለን የምንጠራውን ግዜ እንደሚለግስልን፣ በቤተ ልሔም እረኞቹ እንዳደረጉት፣ እርሱ በሕይወታችን ተወልዶ ሕይወታችንን እንዲያድሰው እንዲያበራው በጸጋው እና ከእኛ ጋር በመሆኑ እንዲለውጠው አሁኑኑ እንድናቀውና እንድንቀበለው ዕድል ይሰጠናል።


ስለዚህ በዓለ ልደት ብዙ የሥርዓተ አምልኮ ጽሑፎች ያኛውንና ይህንን በዓይናችን እንደገና እንድንኖረው የሚያቀርቡልንን ኢየሱስ ከድንግል ማርያም በሥጋ መወለዱን ሲዘክር፣ በዓለ ልደት ለእኛ የጸጋ ግዜ ነው። ር.ሊ.ጳ ልዮን ማኞ የዚህ በዓለ ልደት ጥልቅ ትርጉም ሲገልጽ ምእመናኑን በሚከተሉት ቃላት ጥሪ ያቀርብላቸው ነበር። “ውዶቼ በጌታ ደስ ይበለን፣ ለንጹሕ ደስታ ልባችንን እንክፈት፣ ለእኛ ጥንታዊትዋ ዝግጅትና ዘለዓለማዊ ደስታ የሆነችው አዲስ መዳንን የምታመለክት ቀን ወጣችልን። በዓመት ዙርያ ከፍ ያለው የመዳናችን ምሥጢር ይታደስልናል፣ ይህ ደኅንነት በመጀመርያ በተስፋ የተሰጠን በዘመናት ፍጻሜ ደግሞ የተረጋገጠልና መጨረሻ የሌለው ነው” ብለዋል። ቅዱሱ ልዮን ማኞ በሌላ የልደት ስብከት ደግሞ ይህንን ያረጋግጣል። “ዛሬ የዓለም ፈጣሪ ከአንዲት ድንግል ከርሥ ተወለደ፣ ሁሉን ነገር የፈጠረ እርሱ ከፈጠራት ከአንዲት ሴት ተወለደ። በሰው ዓይን ከቶ ታይቶ የማይታወቅ የእግዚአብሔር ቃል ዛሬ ሥጋ ለብሶ ብቅ በማለት የሚታይና የሚጨበጥ ሆነዋል። ዛሬ እረኞቹ መድኅን በተጨባጭ በሥጋችንን በነፍሳችን መወለዱን ከመላእክት ድምጽ ሰምተዋል።” ብለዋል።

አጠር ባለመንገድ ለመግለጥ የምሻው ሌላ ፍጻሜም አለ፣ የቤተ ልሔም ክንዋኔ በምሥጢረ ፋሲካ ብርሃን መታየት አለበት፣ አንዱም ሌላውም የክርስቶስ የደኅነንት ተግባር አንድ አካል ናቸው። ምሥጢረ ሥጋዌና የክርስቶስ ልደት ቀልባችን ወደ ሞቱና ትንሣኤው እንዲያተኩር ጥሪ ያቀርባሉ። በዓለ ልደትና በዓለ ትንሣኤ የመዳን በዓላት ናቸው። በዓለ ፋሲካ የሰውና አምላክ የሆነው ክብር እንደቀን ብርሃን ሲያንጸባርቅ የመጨረሻን ግዜ በማመልከት በኃጢኣትና በሞት ድል መንሣትን ያከብራል፣ በዓለ ልደት ደግሞ ቀኑን ሊያበራ እንደሚቀድ ጎህ የሰው ልጅን ወደ እግዚአብሔር ለማድረስ እግዚአብሔር በሰው ልጅ ታሪክ መግባትን ያከብራል። ሆኖም ግን የጎህ መቅደድ ቀኑን በመቅደም የቀኑን ብርሃን አስቀድሞ እንደሚያጣጥም በዓለ ልደት የመስቀልና የትንሣኤ ክብርን ያውጃል። በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች የሁለቱ በዓላት ቀናት የሚገልጡት ነገር አለ። በዓለ ትንሣኤ ፀሓይ የክረምቱ ቀዝቃዛና ጨለምለም ያለ ጭጋግና ብርድ በማሸነፍ የምድር ገጽታን በሚያሳድስበት ወቅት ሲዘከር፣ በዓለ ልደት ደግሞ የፀሐይ ብርሃንና ሙቀት ተፈጥሮን ከሸፈነው ሆኖም ግን ከሽፋኑ በታች የሕይወት ትርግታ በሚቀጥልበት ከቅዝቃዜው ሊያነቁት በማይችሉበት በክረምት መጀመርያ ላይ ይዘከራል።

የቤተክርስቲያን አበው፣ የክርስቶስን መወለድ በምሥጢረ ፋሲካ በተፈጸመው በመላው የደሕንነት ታሪክ ብርሃን ይተረጉሙት ነበር።
የእግዚአብሔር ልጅ ምሥጢረ ሥጋዌ እንደ የመጀመሪያው የመዳን ምልክት ሆኖ የቀረበልን ብቻ ሳይሆን የመዳናችን ምሥጢር ዘወትር በመሀከላችን መኖሩን ያመለክታል። እግዚአብሔር ለኛ ሲል ሰው ይሆናል፡ እንደኛው ሕፃን ሆኖ ይወለዳል፣ የኛን ሥጋ በመውሰድ ሞትና ኅጢአትን ያሸንፋል። የቅዱስ ባሲልዮስ ሁለት ጽሑፎች የዚህ ትርጉም ያብራራልናል፡ ቅዱስ ባሲልዮስ ለአማኞች እንዲህ ይላቸው ነበር። “እግዚአብሔር ሥጋ የለበሰው በሥጋ ውስጥ የተደበቀውን ሞት ለመደምሰስ ነው። መርዝ የጠጣ ሰው የመርዙ ተቀራኒ መድሃኒት ሲወስድ የመርዙ ኃይል እንደሚደመስሰው፣ እንዲሁም በቤት ውስጥ ያለው ጨለማ በፀሐይ ብርሃን እንደሚጠፋ ሁሉ በሰብዓዊ ፍጡር ይገዛ የነበረ ሞት፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር በመገኘት ደመሰሰው። በሌሊት ብርድና ጨለማ እስካሉ ድረስ በረዶ ደረቅ ሆኖ ሊቆይ እንደሚችል ነገር ግን በፀሐይ ሙቀት ወዲያው እንደሚቀልጥ ሞት እንዲሁ ክርስቶስ እስከሚወለድ ጊዜ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ገዝቶ ነበር። የእግዚአብሔር አዳኝ ጸጋባ የፍትሕ ፀሐይ በወጡ ግዜ ሞት “ከሕይወት ጋር አብራ ለመኖር ስላልቻለች በድል ተዋጠች” (1ኛ ቆሮ 15፤54)። በተጨማሪ ቅዱስ ባሲልዮስ በሌላው ጽሑፉ “የሰው ልጆች ልደት የሆነውን የዓለም መዳንን እናክብር፣ ዛሬ የአዳም ኅጢአት ተሰረየ። የምድርን ቡቃያ ትበላለህ። ወደ መጣህባት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ። (ዘፍ. ም.3ቁ. 19) አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ ሳይሆን የምንለው በአንድነት ከሰማይ ከመጣው ጋር ወደ ሰማይ እንገባለን ነው የምንለው።” ብሎ ጽፈዋል።


በበዓለ ልደት ድክመቶታችንና ኃጢአታችን በመልበስ እስከ እኛ ዝቅ የሚለውን ለሰብአዊ ድንበር የሚገዛ የእግዚአብሔር ርኅራኄና ፍቅር በኛ ላይ ሲከናወን እናግኘዋለን። ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚለው “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ”(ፊሊ 2፤6-7)። የቤተልሔምን ዋሻ እንመልከት፣ እግዚአብሔር እራሱን ዝቅ በማድረግ በበረት ውስጥ ይወለዳል፣ ይህ እኛን ለማዳን በሕማማቱ ሰዓት ዝቅ ለሚለው መቅድም ነው። በእግዚአብሔርና በሰው ልጅ መሀከል ያለው የፍቅር ታሪክ መተሳሰር በቤተልሄም በረትና በኢየሩሳሌም መቃብር ይፈጸማል።

ውድ ወንድሞችና እኅቶች፤ በመቀራረብ ላይ ያለውን የገና ግዜን በደስታ እንኑር። ይህ ድንቅ የሆነው ወልደ እግዚአብሔር እንደገና “ዛሬ” በመወለዱ በእውነት እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ቅርብ ሊገናኘንም ይፈልጋል፣ ከሱ ጋር እንድንሆን ይፈልጋል። እሱ በሕይወታችን በሰው ልጆች ሁሉ ውስጥ ያለውን ጨለማና ስጋት የሚያጠፋ እውነተኛ ብርሃን ነው። የጌታን ልደት እግዚአብሔር በምሥጢረ ሥጋዌ፣ በልጁ ሕማማት፣ በሞቱና በትንሣኤው ያሳየንን የጥልቅ ፍቅሩ ጉዞ ምልክቶች በማስተንተን እናሳልፈው። ቅዱስ አጎስጢኖስ እንደሚለው “እኛን የክርስቶስ አለመሞት ተካፋዮች ሊያደርግ በእርሱ የአንድያ ልጅ መለኮታዊነት የኛ ሞት ተካፋይ ሆነ”። በተለይም የልደት ማእከል የሆነውን ምሥጢረ ቅዱስ ቁርባን በምናከብርበት ጊዜ ይህንን ምሥጢረ ሥጋዌ እናሰላስላለን እንኖራለንም። በምሥጢረ ጥቀ ቅዱስ ቍርባን ከሰማይ የወረደ ኅብስትና ለደኅነንታችን የተሰዋ እውነተኛ በግ የሆነው ኢየሱስ በእውነት አለ።

ለእናንተ ለሁላችሁና ለቤተሰቦቻችሁ በእውነት የክርስትያን ልደት እንድታከብሩ፣ በበዓሉ የምትለዋወጡዋቸው መልካም ምኞትም እግዚአብሔር ቅርባችን መሆኑና ከእኛ ጋር የሕይወት ጉዞአችን ለመጓዝ እንደሚሻ ከማወቅ የመነጨ ደስታ እንዲሆን መልካም ምኞቴን እገልጣለሁ።








All the contents on this site are copyrighted ©.