2011-12-02 16:54:36

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ(30.11.11)


ውድ ወንድሞችና እኅቶች፤ በመጨረሻዎቹ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮዎች ስለ ብብሉይ ኪዳን የሚገኙ አንዳንድ የጸሎት ምሳሌዎች አሰላስለናል። ዛሬ በኢየሱስ በመመልከት፣ መላው ሕይወቱን እንደ ምሥጢራዊ መስኖ ሆኖ ኑሮው ግንኙነቱና እንቅስቃሴው እየመገበ የመራው ስለ ጸሎቱ ልጀምር እሻለሁ። ኢየሱስ በጸሎት እንደ የእግዚአብሔር አብ የፍቅር ዕቅድ መሠረት ጽናትና ቀጣይነት ባለው ሁለመናውን ለእርሱ በመስጠት ነው። ኢየሱስ የጸሎት አስተማርያችን ነው፣ ወደ እግዚአብሔር አብ ለምናቀርበው እያንዳንዱ ጸሎት ሁሉ እርሱ ንቁና ቅርብ መጠግያችን ነው። እውነቱም አዲሱ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ እንደሚገልጠው “ጸሎት በሙላት የተገልጠውና በተግባር የዋለው በኢየሱስ ነው” (541-547)። በሚከተሉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮዎች ስለእርሱ እንመለከታለን።
የኢየሱስ የሕይወት ጉዞ ልዩ ትርጉም ያለው በዮርዳኖስ ፈለግ ከተጠመቀ በኋላ የሚከተለው ጸሎት ነው። ወንጌላዊው ሉቃስ እንደሚተርከው ኢየሱስ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር ሆኖ በመጥምቁ ዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ ረዘም ባለ ግላዊ ጸሎት ይጠመዳል፣ “ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፥ መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ” (ሉቃ 3፤21-22) ብሎ ይጽፋል። “ሲጸልይ” ማለት ከጠቅላላ ሕዝቡ ጋር በዮርዳኖስ ወንዝ እየመጡ ያደረጉትን ተግባር የሚያበራ ከአባቱ ጋር ያደረገው ውይይት ነው። እየጸለየ ለዚሁ የጥምቀት ተግባር ለየግል የሚሆነና የአጠቃላይ መስመር ያዝይዘዋል።
መጥምቁ ዮሐንስ ከእርሱ ሊጠመቁ ለወጡት ሕዝብ ንስሓ ግቡ ለንስሐ የሚገባ ፍሬም አድርጉ፤ በማለት በእውነት እንደ “አብርሃም ልጆች” መመላለስ እንዳለባቸው ኃይለኛ ጥሪ በማቅረብ ያሳስባቸዋል (ሉቃ 3፤7-9)። ወንጌላዊ ማርቆስ እንደሚያስታውሰ በዚህ ጥሪ የተቀሰቀሱ እስራኤላውያን እጅግ ብዙ እንደነበሩ፣ “የይሁዳም አገር ሁሉ የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፥ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር” (ማር 1፤5) ብሎ ይፋል። መጥምቁ አዲስ ነገር አመጣላቸው፣ ጥምቀቱ ለመቀበል መወሰን ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ያመልክት ነበር፣ ይህም ከኃጢአት ጋር የተሳሰረውን የድሮ ጠባይ ትቶ አዲስ ሕይወት መጀመርን ያመለክታል። ኢየሱስም ይህንን ጥሪ ይቀበላል፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ዳር ከተሰበሰቡ ብዙ ኃጢአተኞች ጋር ይሰለፋል። ሆኖም ግን ይህ ድርጊት ለጥንታውያን ክርስትያኖች እንዳስቸገረ ሁሉ ዛሬ ለእኛም መረዳቱ ሊያስቸግረን ይችላል፣ ኢየሱስ ለምን ይህንን የንስሐና የለውጥ ጥምቀት ለመቀበል በፈቃዱ ወሰነ? የሚናዘዛቸው ኃጢኣት አልነበሩትም፣ ስለዚህ ንስሐ መግባት አያስፈልገውም ነበር። እንታድያ ለምን ይህ ጥምቀት አስፈለገ? ወንጌላዊ ማቴዎስ የመጥምቁ መደነቅና ግራ መጋባት እንዲህ ሲል ይገልጠዋል፣ “ዮሐንስ ግን። እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር” (ማቴ 3፤14)። የኢየኡስ መልስ ደግሞ “ኢየሱስም መልሶ። አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው” (ማቴ 3፤15)። “ጽድቅ” የሚለው ቃል በቅዱስ መጽሐፍ አገላለጽ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በሙላት መቀበልን ያመለክታል። ኢየሱስ ከሕዝቡ ጋር ያለውን ቅርበት ለማሳየት መጥምቁን በመከተል የአብርሃም ልጅ መሆን ብቻ በቂ አለመሆኑ ነገር ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ መፈጸም መሆኑን ለማመልከት ከእግዚአብሔር ለአብርሃም የተሰጠውን ኪዳን በእምነት ለመመለስ ይነሣል። ስለዚህ ኢየሱስ አለምንም ኃጢአት በዮርዳኖስ ወንዝ በመውረድ ኃጢአታቸውን በመታመን ንስሐ ለመግባትና ሕይወታቸውን ለመለወጥ ከመረጡ ጋር አጋርነቱን በማሳየት፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል መሆን በእግዚአብሔር የሚኖር አዲስ ሕይወት ውስጥ መግባት መሆኑን ያስረዳል።
ኢየሱስ በዚህ ተግባር መስቀልን ያስቀድማል፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ ለመፈጸም የጠቅላላ የሰው ልጆች ስሕተት ክብደት በትከሻው በመሸከም የኃጢአተኞች ቦታ ይዞ ለሚፈጽመው ግብረ ተልእኮው ጅማሬ ይሰጣል። በጸሎት እየተጠመደ ከሰማያዊ አባቱ ጋር ያለውን ትስስር በማሳየት አባትነቱን እያጣጣመ የእርሱ ፍቅር ጣዕም ይቀበላል ከአባት ጋር በሚያደርገው ውይይትም የተልእኮው እርግጠኝነት ያገኛል። ከሰማይ በሚመጡ ቃላት የመስቀልና የትንሣኤ ተልእኮ የሆነው የምሥጢረ ፋሲካ ተልእኮን አስቀድሞ ይነግራል። “የምወደው ልጄ” የሚለው መለኮታዊ ቃል በኦሪት የይስሐቅን ታሪክ እያስታወሰ አብርሃም የሚወደው ልጁን እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ ለመሥዋዕት እንዳዘጋጀ ነው (ዘፍ 22፤1-14)። ኢየሱስ የመሲሐዊና ንጉሣዊ ትውልድ የዳዊት ልጅ ወይም እግዚአብሔር በእርሱ ደስ የሚለው ባርያ ሳይሆ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ እንደ ይስሐቅ ተወዳጅ ልጅ፣ ለዓለም ድኅነት እግዚአብሔር የሚሰጠው ነው። ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጸለይ ጥልቅ የሆነው ልጅነትና የእግዚአብሔር አባትነት ሲያጣጥም “የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ” (ሉቃ 3፤22)። መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ ይህ መንፈስ ቅዱስ በአጠቃላይ ተልእኮው ይመራዋል፣ የቤተ ክርስትያን ተግባር እንዲበራም ይህንን ተልእኮ በመስቀል ከፍ ብሎ ይመሠርተዋል (ዮሐ 1፤32-34; 7፤37-39)። እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን የፍቅር ዓላማ እስከ መጨረሻ እተግባር ላይ ለመዋል ኢይሱስ ሁሉ አለማቋረጥ በጸሎት ከአባቱ ጋር ይገናኝ ነበር።
ኢየሱስ በእስራኤላውያን ሕዝብ ሃይማኖታዊ ባህል ጥልቅ በሆነ መንገድ በተሳሰረች ቤተ ሰብ ሲኖር ሕይወቱ ባጠቃላይ በዚህ ልዩ ጸሎት የሰጠመ ነበር። ይህንን በወንጌሎቹ የምናገኝቸው ዝርዝሮች በደምብ አስቀምጠውታል፣ ግዝረቱ (ሉቃ 2፤21) በቤተ መቅደስ መቅረቡ (ሉቃ 2፤22-24) በናዝሬት በቅድስት ቤት ማደጉና መማሩ (ሉቃ 2፤39-40 እና 2፤51-52)። ይህ ታሪክ የ“ሰላሳ ዓመት አከባቢ” ዕድሜ ነው (ሉቃ 3፤23)፣ ምንም እንኳ እንደ በኢየሩሳሌም ባደረጉት ንግደትና (ሉቃ 2፤41) ሌሎች ባህላዊ አጋጣሚዎች ቢሳተፍ ለአንድ ድብቅና የዕረፍት ግዜ ኑሮ ይህ እጅግ ረዥም ጊዜ ነው። ሉቃስ ወንጌላዊ ኢየሱስ በ12 ዓመት ዕድሜው በቤተ መቅደስ በሊቃውንት መሀከል ተቀምጦ ያደረገውን ውይይት (ሉቃ 2፤42-52) ሲተረክ ያ በዮርዳኖስ ከተጠመቀ በኋላ በጸሎት የሚጠመደው ኢየሱስ በባህሎቹ የተመሠረተ ከቤተ ሰቡ ጋር ሲኖር ከሳቸው ባካበታቸው ወሳኝ ተመኩሮዎች በእሳቸው አገባብ ከአባቱ ከእግዚአብሔር ጋር ለረዥም ግዜ በጥልቀት የመወያየት ልምድ እንደነበረው ለማየት ያስችለናል። ለማርያምና ለዮሴፍ ከአንድ የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ የተሰጠው መልስ ያ ከጥምቀት በኋላ የተገለጠውን መለኮታዊ ልጅነት ያመለክታል፣ “ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን? (ሉቃ 2፤49) ኢየሱስ ጸሎቱን ከዮርዳኖስ ወንዝ ውኃ ከወጣ በኋላ አይደለም የጀመረው፣ ከአባቱ ጋር የነበረውን የተለመደውን ቀጣይ ግኑኝነት ይቀጥላል፣ ይህ ከአባቱ ጋር ያለው ጥልቅ ግኑኝነት ከነበረው የናዝሬት ድብቅ ሕይወት ወደ ግልጥ ሕዝባዊ ተልእኮ ያሻጋግረዋል።
እርግጥ ኢየሱስ ስለ ጸሎት የሚያስተምረው ከቤተ ሰቡ የጸሎት አገባብ ነው የመጣው፣ ሆኖም ግን የእግዚአብሔር ልጅ ከመሆኑ የተነሣ የገዛ ራሱ የሆነ ጥልቅና መሠረታዊ ምንጭ አለው። የካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ፣ ኢየሱስ እንዲህ አድርጎ ጸሎት ማሳረግ ከማን ተማረው? ለሚለው ጥያቄ ሲመልስ “ኢየሱስ እንደሰው ልብ ጸሎት ማሳረግ ከእናቱ ከዕብራውያን ልማድ ተማረው። የእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ልጅ በመሆኑ ደግሞ ጸሎቱ ከምሥጢራዊ ምንጭ ይፈልቃል፣ ስለዚህ በቅድስት ሰብአውነቱ ፍጹም የሆነ ውሉዳዊ ጸሎቱ ወደ አባቱ ያሳርጋል” (541) ብሎ ይመልሳል።
በወንጌላዊ ትረካ፣ ኢየሱስ ጸሎት ሲያሳርግ ይጠቅምበት የነበረው አግባብና አካባቢ በነበረው የዕብራውያን ጸሎት ልማድና እርሱ በሚያስተምረው ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረገው ልዩ ግላዊ ግኑኝነት መገናኛ ነበር። ብዙ ግዜ ብቻውን የሚሄድበት ቦታ “ምድረ በዳ” (ማር 1፤35; ሉቃ 5፤16) ለመጸለይ የሚወጣው “ተራራ” (ሉቃ 6፤12; 9፤28) ብቻውን ሆኖ ለመጸለይ የሚመች ግዜ “ሌሊት” (ማር 1፤35; 6፤46-47; ሉቃ 6፤12) ሁሉንም አንድ በአንድ የተመለከትን እንደሆነ ከብሉይ ኪዳን የጀመረው የእግዚአብሔር የመዳን ዕቅድ ግልጸት ሂደት ያስታውሳሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ለእግዚአብሔር ፈቃድ በታማኝነት በመታዘዝና አውቆና ወዶ ይህንን ዕቅድ ለሚቀበል ለኢየሱስ ልዩ አስፈላጊነት የነበራቸው አጋጣሚዎች መሆናቸው ይገለጣል።
እኛም በጸሎታችን ሁል ግዜ በበለጠ በዚሁ ኢየሱስ የእርሱ ጠርዝ በሆነው የደኅንነት ታሪክ መሳተፍን መማር አለብን፣ በእግዚአብሔር ፊት ለፈቃዱ ክፍት እንድንሆን የገባነውን ግላዊ ውሳኔ በማሳደስ፣ እርሱ ለእኛ ላለው የፍቅር ዕቅድ በመታዘዝ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ፍላጎታችን ከእርሱ ፍላጎት ጋር እንዲስማማ ኃይል እንዲሰጠን እንለምነው።
የኢየሱስ ጸሎት እያንዳንዱን የተልእኮው አጋጣሚና መዋዕሉን ሙሉ በሙሉ ያካትታል። ድካሞችም አያጓድሉትም። ቅዱስ ወንጌል ኢየሱስ የሌሊት ክፍልን በጸሎት ያሳልፍ እንደነበር ያበራራሉ። ቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ ከእነዚህ ሌሊቶች ስለአንዲት ሌሊት እንጀራ የማብዛት ተአምር ካሳየበት ዕለት በኋላ ስላለችው ሌሊት እንዲህ ይላል፣ “ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳ ገብተው ወደ ማዶ ወደ ቤተ ሳይዳ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። ካሰናበታቸውም በኋላ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ታንኳይቱ በባሕር መካከል ሳለች እርሱ ብቻውን በምድር ላይ ነበረ” (ማር 6፤45-47) ይላል። መውሰድ ያለባቸው ውሳኔዎች አስቸኳይና የተደባለቁ እንደመሆናቸው መጠን ጸሎቱም ረዥምና ጥልቅ ይሆናል። ለምሳሌ፣ የ12 ሐዋርያት የመምረጥ ግዜ በደረሰ ግዜ ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ እንደሚያመለክተው ለዚህ እንዲዘጋጅ ኢየሱስ ያሳረገው ጸሎተ ሌሊትን ያሰምርበታል፣ “በነዚህም ወራት ይጸልይ ዘንድ ወደ ተራራ ወጣ፥ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ። በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፥ ከእነርሱም አሥራ ሁለት መረጠ ደግሞም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው” (ሉቃ 6፤12-13)።
የኢየሱስ ጸሎት ስንመለከት በኅልናችን የሚከተሉ ጥያቄዎች መነሣት አለባቸው፣ እኛስ እንዴት እንጸልያለን? ከእግዚአብሔር ጋር ላለኝ ግኑኝነት ምን ያህል ግዜ እሰጠዋለሁ? ዛሬ ለጸሎት በቂ ትምህርትና ሕንጸት እየተደረገ ነውን? አስተማሪስ ማን ሊሆን ይችላል? “የጌታ ቃል” ቨርቡን ዶሚኒ በሚለው ሐዋርያዊ ምዕዳን ቅዱስ መጽሓፍን በጸላዪ መንፈስ እንዲነበብ አደራ ብየ ነበር። በሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኑ ከሲኖዶስ አበው ጳጳሳት ጉባኤ አደራ የተሰጠው “ለክስዮ ዲቪና” የተሰኘው ትርጉሙም በቃለ እግዚአብሔር መጸለይ ለሚለው አስምርየበት ነበር። ማዳመጥ ማስተንተን እግዚአብሔር ሲናገር ጸጥ ብሎ ማዳመጥ ጥበብ ነው። እርግጥ ነው ጸሎት መቀበልን የሚጠይቅ ስጦታ የእግዚአብሔር ተግባር ነው፣ ሆኖም ግን እኛ በበኩላችን ደግሞ ሥራየ ብለን ልንተጋበትና ጸንቶ መቀጠልን ይጠይቃል፣ በተለይ ደግሞ ጽናትና ቀጣይነት አስፈላጊዎች ናቸው። ከእግዚአብሔር አባትነትና ከመንፈስ ቅዱስ ውኅደት የሚፈልቀው የኢየሱስ ጸሎት በረዥሙና ታማኝ ልምምዱ እስከ መስቀልና የደብረ ዘይት ጸሎቶች ዓይነት ጥልቀት እንዲኖረው ሆነ። ባለነው ዘመን ዓለማችን ለመለኮታዊ ነገሮችና እግዚአብሔርን ለማስገኘት ከሚችል ተስፋ ራሱን ስላገለለ፣ ክርስትያኖች የጸሎት ምስክሮች እንዲሆኑ ተጠርተዋል። ከኢየሱስ ጥልቅ ፍቅር በመፍጠር ከአባቱ ጋር ያለውን ውሉዳዊ ግኑኝነት በእርሱና ከእርሱ ጋራ አብረን የእግዚአብሔር ሰማያዊ መስኰቶች መክፈት እንችላለን። ምንም እንኳ በክርስትያናዊ ጸሎት እየተጓዙ ሌሎች ጉዞዎች እንደሚከፈቱ እውነት ቢሆን፣ ከሰው አመለካከት ወጣ ብለን በጸሎት ጎዳና እየተጓዝን ሌሎችን እንዲጓዝዋት ለመርዳት እንችላለን።
የተከበራችሁ ወንድሞችና እኅቶች፤ ኢየሱስ እንደሚያስተምረን፣ በተቈራረጠ ጸሎት ሳይሆን፣ ቀጣይ እምነት የሞላበትና ሕይወታችንን በሚያበራ ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር ጥብቅ ግኑኝነት እንዲኖረን እንማር። በመንገዳችን ለምናገኛቸው ባጠገባችን ለሚኖሩ ሰዎች የመኖር ብርሃን የሆነውን ጌታ በማግኘት የሚምትገኘውን ደስታ እንድናደርስላቸው እንዲያስችለን ጌታን እንለምነው።








All the contents on this site are copyrighted ©.