2011-11-30 13:54:16

የቤተሰብ ጉዳይ ተንከባካቢ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ምሉእ ዓመታዊ ጉባኤ
ብፁዕ ካርዲናል አንቶነሊ፦ “ክርስትያን ቤተ ሰብ የክርስቶስ ኅልውና እና ፍቅር መግለጫ ነው”።


በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ይኽ ደግሞ ፋሚሊያሪስ ኮንሶርዚዮ-ቤተ ሰብአዊ ማኅበርነት/ወዳጅነት” በሚል ርእስ ሥር እ.ኤ.አ. ኅዳር 22 ቀን 1981 ዓ.ም. የደረሱት ሐዋርያዊ ምዕዳን እና በሳቸው ውሳኔ እና መልካም ፈቃድ መሠረት የቤተሰብ ጉዳይ ተንከባካቢ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ምሥረታ 30ኛው ዓመት መታሰቢያ፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ. ከግንቦት 30 ቀን እስከ ሰነ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. RealAudioMP3 በኢጣሊያ ሚላኖ ከተማ ሊካሄድ ተወስኖ ስላለው ሰባተኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ ርእሰ ጉዳዮች የሚወያይ የቤተሰብ ጉዳይ ተንከባካቢ ጳጳሳዊ ምክር ቤት 20ኛው ዓመታዊ ምሉእ ጉባኤ ትላትና እ.ኤ.አ. ኅዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም. መጀመሩ ሲገለጥ፣ በዚህ እስከ ነገ የሚቀጥለው ጉባኤ ትላትና ሐዋርያዊ ምዕዳን “ፋሚሊያርሲ ኮንሶርዚዮ - ቤተሰብአዊ ማኅበርነት/ወዳጅነት” ከሰላሳ ዓመት በኋላ በሚል ርእሰ ጉዳይ ሰፊ አስተምህሮ ቀርቦ ውይይት መካሄዱ ሲገለጥ፣ በዚሁ ርእሰ ሥር ንግግር ያሰሙት ጳጳሳዊ የቤተሰብ ጉዳይ ተንከባካቢ ምክር ቤት ሊቀ መንበር ብፁዕ ካርዲናል ኤኒዮ አንቶኔሊ፣ ይኽ ጉባኤ ቤተ ክርስትያን በአንቀጸ ሃይማኖት እና በሐዋርያዊ ግብረ ኖልዎ ደረጃ ስለ ቤተሰብ ጉዳይ የምታስተምረው ኵላዊ አስተምህሮ “ፋሚሊያሪስ ኮንሶርዚዮ” ሐዋርያዊ ምዕዳን መሠረት ቤተ ሰብ በዚህ በወቅታዊው ዓለም ጥሪው እና ኃላፊነቱ የቤተሰብ ሰብአዊ ክብሩ በምሥጢረ ተክሊል የሚጸናው ትርጉሙ፣ ይኸንን መሠረት በማድረግ ቤተሰብ ሊኖረው የሚገባው እሴቶች እና የሕይወት ክብር በመተንተን እግብር ላይ ለማዋል የሚያስችለው ሥልጣናዊ መንገድ የሚያመለክት መሆኑንም ገልጠው፣ ቤተሰብ በተለይ ደግሞ ክርስትያን ቤተሰብ በአንቀጸ ሃይማኖት መሠረት የምሥጢረ ሥላሴ አምሳያ፣ በእግዚአብሔር የ“አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ” ፍጹም አካላዊ/ሰብአዊ ሱታፌ ያለው ነው። የሚሰዋ ፍቅር የሚኖርበት ይኽ ደግሞ በምድር የእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳያ መሆን ማለት ነው ብለዋል።
ምሥጢረ ተክሊል፣ አዲስ ኪዳናዊ ቅዱስ ምሥጢር በሚል ስያሜ ጥልቅ ትርጉሙን እና የጥሪው ጥልቀቱን እና የላቀው ተግባሩን የሚገልጥ መሆኑ በማብራራት ይኸንን አንቀጸ ሃይማኖት መሠረት ያለው ጥልቅ ትርጉም በሐዋርያዊ ግብረ ኖሎው መሠረት በቁምስናዎች ሰበካዎች ዘንድ ጎልቶ ብፁዓን ጳጳሳት ካህናት ይኸንን የቤተሰብ ጥልቅ ትርጉሙን ማነቃቃት እና በምእመናን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አጋጣሚዎች በሁሉም ዘንድ ምሥጢረ ተክሊል ተፅእኖ ሳይሆን መልካም እና ቅዱስ ጥሪ መሆኑ ቅዱስ መጽሐፍ ቲዮሎጊያ እና የቤተ ክርስትያን ትውፊት መሠረት እንዲሰርጽ የማድረግ ሐዋርያዊ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
በዚህ በምንኖርበት ዓለም ክርስትያን ቤተ ሰብ ታማኝ የወንጌል ምሥክርነት ለማቅረብ መሠረት የሆነው በቤተሰብ አባላቱ ዘንድ የሚኖረው ውስጠ ግኑኝነት እርሱም ለጋስነት እና ኃላፊነት፣ ተዋልዶ፣ የልጆች ሕንጸት እንክብካቤ፣ በተሰማሩበት የሙያ ዘርፍ ንቁ አገልጋይነት፣ ለድኻው የኅብረተሰብ ክፍል የሚያስብ፣ ጸላይ፣ በመሥዋዕተ ቅዳሴ ሱታፌ በቁምስና በተለያዩ ዘርፎች ንቁ ተሳታፊ በመሆን የቤተሰብ ቤተ ክርስትያናዊ ገጽታውን መኖርን ይጠይቃል፣ ይኽ ጉዳይ በትክክል ሐዋርያዊ ግብረ ኖሎዎ የሚመለከት ነው። ስለዚህ ይኸንን ሁሉ እግምት ውስጥ በማስገባት ቤተሰብ በቤተ ክርስትያን ማእከላዊ ሥፍራ ያለው ነው እንዳሉ የቅድስት መንበር መግለጫ አስታወቀ።
ር.ሊ.ጳ. ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የእውነተኛው ጾታዊ ስሜት ትርጉም በመግለጥ፣ ጾታዊ ስሜት በወንድ እና በሴት መካከል በሚሥጢረ ተክሊል በሚጸናው አንድነት አማካኝነት የሚኖር ነው። ጾታዊ ስሜት፣ በተመለከተ የሚነዙት በሴተ እና ወንድ መካከል ከሚጸናው ቤተሰብዊ ኑሮ ውጭ የተለያዩ አማራጭ ኪዳናዊ ውህደት ተምሳይ የሆኑት በአሁኑ ወቅት ሕጋዊነት ለማልበስ የሚደረገው ሽርጉድ የእውነተኛው ነጻነት እና እኩልነት ትርጉምን የሚቀናቀን ለአደጋ የሚያጋልጥ ሆኖ፣ እያስከተለው ያለው ግብረ ገባዊ ቀውስ መፍትሔ እንደሚያገኝ የማያጠራጥር ነው። ቤተ ክርስትያን የምታስተምረው እና የምትገልጠው ቤተሰብ ለኅብረተሰብ ኅልውና መሠረት ነው። በጾታዊ ስሜት የሚገለጠው ፍቅር የሚሰዋ ፍቅር መሠረት ያለው እርሱም ገዛ እራስን እንደ ጸጋ መስጠት ለሚለው ፍቅር መግለጫ ነው። ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ ዲዮስ ካሪታስ ኤስት በተሰኘው ርእስ ሥር የደረሱት ዓዋዲ መልእክት ጠቅሰው፣ የአጭር ግዜ ቦግ ብሎ ለሚጠፋው እርካታ ሳይሆን ያ ወደ ላይ ያቀናው ወደ ፍጽምና እና ወደ ተቀደሰው የማቅናቱ የኅልውና ግብ ቅድመ ሁኔታ የሚገልጥ ነው። ስለዚህ ቤተሰብ በሁለመናው የክርስቶስ እና የእግዚአብሔር ኅልውና እና ፍቀር የሚያንጸባርቅ እና መግለጫ ሆኖ መኖር ተቀዳሚ ዓላማው መሆኑ አብራርተዋል። ይኽ ደግሞ የሚላኖ ልኂቅ ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ተታማንዚ እንዳሉት፣ ቤተ ሰብ የዳኑት እና ለአዲስ አስፍሆተ ወንጌል በማዳን እቅድ፣ መድኅናዊ ሱታፌ ያለው ማኅበረሰብ ማለት ነው ያሉትን ሐሳብ የሚያጎላ ነው። ቤተሰብ በቤተ ክርስትያን እና ከቤተ ክርስትያን ጋር የእግዚኣብሔር ቃል የሚመሰከርበት ቤት ነው እንዳሉ የቅድስት መንበር መግለጫ አስታወቀ።







All the contents on this site are copyrighted ©.