2011-11-18 11:55:50

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ


ውድ ወንድሞችና እኅቶች፤ ዛሬ የጸሎተ መዝሙረ ዳዊት ትምህርተ ክርስቶስ ስጨርስ እጅግ ገናና ከሆኑት ንጉሣውያን መዝሙሮች። ኢየሱስ ራሱም የጠቀሰውና የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ከመሲህ ጋር በማያያዝ በስፋት የጠቀሱትና ያነበቡት መዝሙር ላይ በማስተንተን እንድዘጋው እፈልጋለሁ፣ መዝሙሩ በጥንታዊትዋ ቤተ ክርስትያንና በሁሉም ዘመን ምእመናን እጅግ ተወዳጅ የሆነ ሆኖ መዝሙር 110 በግሪክና ላቲኑ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ መዝሙር 109 ነው፣ ይህ ጸሎት መጀመርያ የተደረሰበት አጋጣሚ ምናልባት ከአንድ የቤተ ዳዊት ንጉሥ ሥያሜ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን ትርጉሙ ከአንድ የልዩ ታሪክ ፍጻሜ ወዲያ በማሻገር ለሌላ ሰፋ ያለ የትርጓሜ አድማስ ክፍት ይሆናል፡ በዚህም ድል የነሣና በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠው የመሲሁ በዓልን ያመልክታል።
መዝሙር ወግ ባለው አዋጅ እንዲህ ሲል ይጀምራል፤
“እግዚአብሔር ጌታዬን፡ ጠላቶችህን በሥልጣንህ ሥር እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው።” (ኍ.1)
እግዚአብሔር ንጉሡን የታላቅ ክብርና ባለ ፍጹም መብት በሚያደርግ ምልክት በቀኙ እንዲቀመጥ በማድረግ ለክብር ይሾመዋል። ንጉሡ የሕዝብና የመለኮታዊ ግርማዊነት ሸምጋይ በመሆን በመለኮታዊ ግርማዊነት እንዲሳተፍ ተፈቅዶለታል። የንጉሡ ግርማዊነት እግዚአብሔር ራሱ ጠላቶቹን በእግሩ መቀመጫ ሥር እንዲሆኑ በሚያደርገው ድል መንሳትም ተጨባጭ ይሆናል። በጠላቶች ላይ ድል መንሳት የእግዚአብሔር ነው፡ ሆኖም ግን ንጉሡ የድሉ ተካፋይ እንዲሆን ተደረገ፡ ድል መንሳቱም በመለኮታዊ ሥልጣን ምስክርና ምልክት ይሆናል።
በመዝሙሩ መጀመርያ ላይ የተገለጠው ንጉሣዊ ክብር በአዲስ ኪዳን እንደ የመሲሁ ትንቢት ተወስደዋል፣ በዚህም ይህ ጥቅስ በብዙ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች እንደ ቀጥታ ጥቅስ ወይም እንደ ድጋፍ በብዛት ከሚጠቀምዋቸው መካከል አንዱ ነው፡፡ ኢየሱስ ራሱም ይህ ጥቅስ መሲህን እንደሚመለከትና መሲሁ ከዳዊት ይልቅ እንደሚበልጥና የዳዊት ጌታ መሆኑን ለማስተማር ይህንን ጥቅስ ይጠቀማል። (ማቴ 22፤41-45; ማር 12፤35-37; ሉቃ 20፤41-44) ቅዱስ ጴጥሮስም በጴንጠቆስጤ ባደረገው ንግግር ይህ ንጉሣዊ ሥያሜ በክርስቶስ ትንሣኤ እንደተፈጸመና፡ ክርስቶስ አሁን እግዚአብሔር በዓለም ላይ ካለው ንግሥነት እየተሳተፈ በቀኙ ተቀምጦ እንደሚገኛ ሲገልጥ ይጠቅሰዋል፣ (ግሐ 2፤29-35) ልክ ኢየሱስ ለፍርድ በሊቀ ካህናት ፊት በቆመበት ስለራሱ እንደተናገረው (ማቴ 26፤63-64; ማር 14፤61-62¸ሉቃ 22፤66-69)፣ እውነትም ይህ የተሾመው ንጉሥ፡ በእግዚአብሔር አብ ቀን እጅ የተቀመጠና በደመና ወደ ሰማይ ያረገው የሰው ልጅ ክርስቶስ ነው። በትንሣኤ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ እጅ የመቀመጥ ክብር የገባ እውነተኛ ንጉሥ እርሱ ኢየሱስ ነው፡፡ (ሮማ 8፤34; ኤፈ 2፤5; ቆላ 3፤1; ዕብ 8፤1;12፤2) ከመላእክት በላይ የሆነውና በሰማይ ከሁሉ ሥልጣን በላይ ከፍ ብሎ የተቀመጠው ጠላቶቹም ሁሉ፡ ያች የመጨረሻ ጠላት የሆነችው በእርሱም ላንዴና ለመጨረሻ የተሸነፈችውን ሞት ሳይቀር፡ በእግሩ ሥር ያኖረ ኢየሱስ እውነተኛ ንጉሥ ነው። (1ቆሮ 15፤24-26; ኤፈ 1፤20-23; ዕብ 1፤3-4:13; 2፤5-8; 10፤12-13; 1ጴጥ 3፤22) ይህ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ የተቀመጠና በመንግሥቱ የሚሳተፍ ንጉሥ፡ ከዳዊት ተከታይ ሰዎች ሳይሆን ሞትን ያሸነፈና በእውነት በእግዚአብሔር ክብር የሚሳተፍ አዲሱ ዳዊት የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ወዲያውኑ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚሰጠን ንጉሣችን ነው።
በመዝሙራችን በከበረው ንጉሥና በእግዚአብሔር መካከል የማይለያይ ግኑኘት አለ፣ ዘማሪው በሁለተኛው ኁልቍ እግዚአብሔር ራሱ የኃይል ብትር ሰጥቶ በጠላቶቹ ላይ እንዲገዛ ሥልጣን እንደሰጠው እንደሚያመለክተው ሁለቱም አብረው አንድ መንግሥት ያስተዳድራሉ።
“እግዚአብሔር የኃይልን ብትር ሰጥቶ የመንግሥትህን ሥልጣን ከጽዮን ያስፋልህ፤ በጠላቶችህ ላይ ሥልጣን ይኑርህ፣” (ኍ.2)
የሥልጣኑ አስተዳደር ንጉሡ በቀጥታ ከእግዚአብሔር የሚቀበለው ሥልጣን ነው፣ ይህ ኃላፊነት በእግዚአብሔር መጠጋትንና ለእርሱ በመታዘዝ የሚኖር ሲሆን፡ ንጉሡ በሕዝቡ መካከል የእግዚአብሔር ቻይና አሳቢ ህልውና ምልክት ይሆናል። የንጉሡ በመጥሮ ነገር ላይ የተገኘው የመለኮታዊ ድል ሸምጋይ መሆን የሚያመለክቱ፣ ጠላቶችን መግዛት፡ ክብርና ድል የታደሉ ስጦታዎች ናቸው። እርሱ ጠላቶችን እየለወጠ ይገዛቸዋል፣ በፍቅሩ ያሸንፋቸዋል፡፡
ስለዚህ ተከታዩ ኍልቍ በቍ.3 ላይ የንጉሡን ታላቅነት ያከብራል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ኁልቍ ሲተረጐም ትንሽ ያስቸግራል፡ በዋነኛው የዕብራይስጥ ጽሑፍ ሠራዊቱ የሠራዊቱ መሰባሰብ በንጉሣቸው የሹመት ቀን ሕዝቡ ለቀረበልት ጥሪ ለጋስ መልስ በመስጠት ንጉሣቸውን መከበባቸውን ሲያመለክት፣ በ3ኛ ወይም በ2ኛ ከክርስቶስ ልደት በነበረው ክፍለ ዘመን በ70 ሊቃውንት ሰፕትዋጂንት በተደረገው የግሪክ ትርጓሜ ግን የንጉሡ መለኮታዊ ልጅነትን በማመልከት የንጉሡ ልደት ወይም የትውልድ ሐረግ ከእግዚአብሔር ወገን መሆኑ ይገልጣል፣ ቤተ ክርስትያንም ሁሌ ይህንን ትርጓሜ ስትከተል ኖራለች፡፡ ስለዚሁ ኁልቁ እንደሚከተለው ይላል፣
“ቀዳማዊ በኃይልህ ቀን፥ በቅዱሳን ብርሃን ከአንተ ጋር ነበር፥ ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ።” (ኁ.3)
ይህ ለንጉሡ የተሰጠ መለኮታዊ ቃል ምንጩ ምሥጢራዊ የሆነና ሊጠየቅ የማይቻል፣ የእርሻ መሬትን በማሸብረቅ ለማሳው አስደናቂ ውበት በመስጠት ፍሬ እንዲሰጥ በሚያደርገው የሚያሸብርቅ የአጥብያ ኮከብ ብርሃንና የጥዋት ጠል የሚመሰል፡ በብርሃንና በምሥጢራዊ ሕይወት ያሸብረቀ መለኮታዊ ትውልድ እንዳለ ያረጋግጣል፡፡ እንዲህ በማለቱ በእውነት ከእግዚአብሔር የሚመጣው ሰማያዊ ንጉሥ ምሳሌ የሆነው መሲህ ለሕዝቡ መለኮታዊ ሕይወት የሚያመጣ እንዲሁም የቅድስናና የድኅነት ሸምጋይ የሚሆነው ለዘለዓለም ከሰማያዊ ነገር የተያያዘ መሆኑን ያስረዳል። እዚህ ላይ የምንረዳው ይህ ሁሉ ከዳዊት ዘር በሆነ ንጉሥ ሳይሆን በእውነት ከእግዚአብሔር በሚመጣ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን እንገነዘባለን። እርሱ መለኮታዊ ሕይወትን ወደ ምድር የሚያመጣ ብርሃን ነው።
በዚሁ በአንድምታ ሊተረጐም ክፍት በሆነና ቅኔያዊ ምሳሌ የመዝሙሩ መጀመርያ ክፍል ይደመደማል፣ ሌላ አዲስ አድማስ የሚከፍት መለኮታዊ ቃል ከግርማዊነት ጋር የተሳሰረ ስለ ክህነታዊ መንግሥት ይናገራል። በኍልቍ 4
“እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት አንተ ለዘላለም ካህን ነህ፥ እግዚአብሔር ማለ አይጸጸትም።” ይላል።
መልከጼዴቅ የሳሌም ካህን ንጉሥ ነበር፣ አባታችን አብርሃም የወንድሙ ልጁ ሎጥ እንደተማረከ በሰማ ጊዜ ከጠላቶች እጅ ለማዳን ተዋግቶ ድል በተቀናጀ ግዜ መልከጼዴቅ አብርሃምን የባረከና እንጀራና የወይን ጠጅ መሥዋዕት አቅርበዋል። (ኦሪ ዘፍ 14፣19) በመልከጼዴቅ ምሳሌ ክህነታዊና ንጉሣዊ ሥልጣን ይዋኃዳሉ ጌታም ለዘለዓለም መሆናቸውን ያውጃል። በመዝሙሩ የተጠቀሰው ንጉሥ ከእግዚአብሔር በሚሰጠው ቡራኬ አማካኝነት በሕዝቡ መካከል ሕያው የሆነው መለኮታዊ ህልውና ሸምጋይ በመሆን ለዘለዓለም ካህን ይሆናል። ይህ ቡራኬ በሥርዓተ አምልኮ ሕዝቡ ከሚያቀርበው ምስጋና ጋር ይገናኛል።።
የዕብራውያን መልእክት (5፤5-6.10; 6፤19-20) ይህንን ኍልቍ በቀጥታ ይጠቅሳል፣ ምዕራፍ ሰባት በሙሉ ደግሞ በክርስቶስ ክህነት በማስተንተን በዚሁ ኍልቍ ያተኵራል፡፡ የዕብራውያን መልእክት በመዝሙር 110 (109) በመመርኮዝ የመልከጼዴቅ ክህነትን ፍጽምና ላይ በማድረስ ሙላት የሚሰጣቸው እውነተኛና ወሳኝ ካህን ኢየሱስ ነው። ዕብራውያን መልእክት እንደሚያመለክተው መልከጼዴቅ “አባትና እናት የትውልድም ቍጥር የሉትም፥” (7፤3) ስለዚህ ክህነቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ ከሚተላለፈው የነገደ ሌዊ ክህነት ይለያል። እርሱ ግን የክርስቶስ ምሳሌ በመሆን “ለዘመኑም ጥንት ለህይወቱም ፍጻሜ የለውም” እና ለዘለዓለም ካህን ነው። ሊቀ ካህናት ክርስቶስም “በማያልፍም ሕይወት ኃይል እንጂ በሥጋ ትእዛዝ ሕግ ሳይሆን ሌላ ካህን በመልከ ጼዴቅ ምሳሌ ቢነሳ፥ ይህ እጅግ አብልጦ የሚገለጥ ነው።”(7፤16) ስለዚህ የመዝሙሩ ትንቢትና የመልከጼዴቅ ክህነት ምሳሌ፣ ከሙታን ተለይቶ በተነሣና ወደ ሰማይ ባረገ በእግዚአብሔር ቀኝም በተቀመጠ ኢየሱስ ክርስቶስ ሙላት አገኘ፡፡ ምክንያቱም “እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው” (7፤24) ስለተባለ ነው፡፡ በአብርሃም ዘመን በመልከጼዴቅ የቀረቡ እንጀራና የወይን ጠጅ፡ ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ኢየሱስ በእንጀራና በወይን ጠጅ ባቀረበው ቅዱስ ቊርባን ራሱን መሥዋዕት በማቅረብ ሞትን አሸንፎ ለምእመናን ሁሉ ሕይወት በመስጠት ሙላት ሰጠው። እርሱ በዕብራውያን መልእክት እንደተመለከተው “ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።” (7፤25)
ከዚሁ በመቀጠል በኁልቍ 4 ከቀረበው መለኮታዊ ቃልና ከበድ ያለው ቃል ኪዳኑ በኋላ የመዝሙሩና የደራሲው አስትያየት ይለወጣል። “ጌታ በቀኝህ ነው” (ኍ.5)ሲልም በቀጥታ ያውጃል። በመጀመርያው ኍልቍ የክብርና የመዓርግ ምልክት በሆነው በእግዚአብሔር ቀኝ በሚቀመጠው ንጉሥ ሲገለጽ በዚሁ ኍልቍ ግን ጌታው ንጉሡን በውግያ ግዜ በጋሻው እንዲከላከልና ከማንኛውም አደጋ እንዲያድነው ብቀኙ ይቀመጣል። ንጉሡ በጽኑ ቦታ ነው ያለው፡ እግዚአብሔር ተከላካዩ ነው፡ አብረውም ይዋጋሉ ክፋትን ሁሉ ያሸንፋሉ። የመዝሙሩ የመጨርሻ ኁልቆች በጌታ የተጠጋና ከጌታ ሥልጣንና ክብር የተቀበለው የአሸናፊው ንጉሥ ራእይ እግምት ውስጥ በማግባት የሚቃወሙትን እያሸነፈ ሃገራትን እየፈረደ ጠላቶቹን ይቋማቸዋል። ትዕይንቱ የውግያ ድራማንና የንጉሣዊ ድል መንሳት ፍጽምናን ለመግለጽ በብሩህ ቀለማት የተቀባ ነው። በጌታ ከለላ ሥር ያለው ንጉሡ ማንኛውም እንቅፋት ያወድማል በእርግጠኝነት ደግሞ ወደ ድል ይራመዳል። በዓለማችን ውስጥ ብዙ መጥፎ ነገር እንዳለ እንዲሁም በበጎና በመጥፎ መካከል ዘለዓለማዊ ውግያ እንዳለ እናያለን እንደሚመስለውም መጥፎ ነገር ያየለ ይመስላል፡፡ እንደዛ አይደለም፡ እውነተኛው ንጉሣችንን ካህናችን ክርስቶስ ጌታችን ከሁሉም ያይላል፡ ምክንያቱም ምንም እንኳ ታሪክ በድል የመወጣት ሁኔታን ጥርጣሬ ውስጥ ቢያገባው ክርስቶስ በሙሉ የእግዚአብሔር ኃይል ስለሚዋጋ ጥላቻ ሳይሆን በጎ ነገር እንዲሁም ፍቅር ያሸንፋል።
መዝሙራችን የሚደመደምበት ቅኔአዊ ምልክት እንዲሁም ኃይለ ቃል ያለው ኁልቍ እንዲህ ይላል፡
“በመንገድ ከፈሳሽ ውኃ ይጠጣል፡ ስለዚህ ራሱ ከፍ ከፍ ያደርጋል” (ኍ.7)
በውግያ ትንተና መሃከል ውግያ በሚቆምበትና በዕረፍት ጊዜ በመንገድ ከፈሳሽ ውኃ በመጠጣትና አዲስ ኃይልና ዕረፍት በማግኘት ጉዞውን የወሳኝ ድል ምልክት በሆነው ራሱን ከፍ ከፍ በማድረግ እንደገና ይጀምራል፡፡ ይህ ባለ ብዙ ትርጉም ቃል ለቤተ ክርስትያን አባቶች ሊተረጕሙት እጅግ አስተቸግሮአቸው እንደበር እርግጥነው፡፡ በዚህም ለምሳሌ ቅዱስ አጎስጢሮስ “ይህ ፈሳሽ ውኃ የሰው ልጅ ሰብአውነት ነው፡ ክርስቶስ ሰው በመሆን ከዚህ ፈሳሽ ውኃ ጠጣ በዚህም በሰው ልጅ ሰብአውነት በመግባት ራሱን ከፍ አደረገ አሁን ከፍ የሚለው ደግሞ የምሥጢራዊ አካሉ ማለት የእኛ ራስ ወሳኙ አሸናፊ ነው” ይላል፡፡
ውዶቼ፡ የአዲስ ኪዳን የትርጓሜ መስመር በመከተል የቤተ ክርስትያን ባህል ይህንን መዝሙር መሲህን ከሚገልጡ እጅግ አስፈላጊ ጽሑፎች አንዱ አድርጎ ይጠቀምበታል፡፡ የቤተ ክርስትያን አባቶችም አክብሮት በመላው አገባብ ይህንን መዝሙር ክርስቶሳዊ ትርጓሜ እየሰጡ ጠቅሰውታል። መዝሙሩ የተዘመረለት ንጉሥ የእግዚአብሔር መንግሥትን የሚገነባና የዓለም ሥልጣናትን የሚያሸንፍ በእርግጥ ክርስቶስ ነው። ከፍጥረት ሁሉ አስቀድሞ ከንጋት በፊት ከአባቱ የተወለደ ሥጋ የለበሰው አንድያ ልጁ የሞተው ከሙታን ተለይቶ የተነሣውና ወደ ሰማያት ያረገው፣ ዘለዓለማዊ ካህን በምሥጢረ እንጀራና ወይን የኃጢአት ሥሬትና ከእግዚአብሔር መታረቅን የሚሰጥ፡ በትንሳኤው በሞት ላይ በነሣው በድል ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ንጉሥ ነው። ቅዱስ አጎስጢኖስ ስለዚህ መዝሙር ከጻፈው ጥቂት ለማስታወስ ያህል፣ “ባህርያችን ለብሶ ሰው ለመሆን በሰዎች መካከል የሚመጣውን አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ ማወቅ አስፈላጊ ነበር፡ እርሱ ሞተዋል ከሞት ተነሣ ወደ ሰማያት አረገ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ተቀምጦ ተስፋ የሰጠውን ሁሉ በሰው ልጆች መሀከል ፈጸመ። ይህ ሁሉ በትንቢት መነገር ነበረበት፡ እንዴት መምጣት እንደነበረበት አስቀድሞ መነገር መመልከት ነበረበት። ምክንያቱም በድንገት ሳይታወቅ የመጣ እንደሆነ ሰዎችን እንዳያደንግጥ ሰዎች በእምነት በደስታና በመጠባበቅ እንዲቀበሉት መምጣቱ አስቀድሞ አሳወቀ። መዝሙሩ እርግጠኛና ግልጽ በሆኑ ቃላት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትን በትንቢት በመናገር የዚህ ተስፋ አካል ይሆናል። በዚህም እኛ በዚህ መዝመር በእውነት ክርስቶስ እንደታወጀ ልንጠራጠር አንችልም።” ይላል።
የክርስቶስ ምሥጢረ ፋሲካ የዚህ መዝሙር መፍቻ በመሆን የንግሥነት እውነተኛ ትርጉም ለመረዳት ክርስቶስን እንድንመለከት እንደሚያስፈልግና እርሱ እስከ መጨረሻ ባደረገው የመታዘዝና የፍቅር ጉዞ ባሳየው አገልግሎትና ራሱ የመሰዋት እውነት ውስጥ መኖር እንዳለብን ያመለክታል። (ዮሐ 13፣1 እና 19፣30) በዚህ መዝሙር ስንጸልይ፡ እኛም ንጉሡ መሲህ ክርስቶስን በመከተል በመንገዱ እንድንጓዝ ከእርሱ ጋር አብረን ወደ መስቀሉ ተራራ እንድንወጣና በዚህም በእግዚአብሔር አብ ቀኝ የተቀመጠውንና ምሕረትና ድኅነት ለሁሉም የሰው ልጆች ለሚሰጠው፡ አሸናፊ ንጉሥና ካህን ስናሰላስል ከእርሱ ጋር አብረን ወደ ክብር እንድንገባ፡ እንለምናለን። በእግዚአብሔር ጸጋ “የተመረጠ ትውልድ፡ የንጉሥ ካህናትና ቅድስት ሃገር” (1ጴጥ 2፣9) የሆንን እኛም ውኃን ከሕይወት ምንጮች በደስታ ለመቅዳት እንችላለን። (ኢሳ 12፣3) ለመላው ዓለምም “ከጨለማ ወድሚያስደንቅ ብርሃኑ የጠራን” (1ጴጥ 2፣9) እግዚአብሔር ያደረገልል አስደናቂ ነገሮች ለመላው ዓለም እናውጃለን። ውድ ጓደኞቼ፣ በዚሁ የመጨረሻ ትምህርት ክርስቶስየ በቅዱስ መጽሐፍ የምናገኛቸው ተወዳጅ ጸሎት የሆኑና ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖሩን ስለሚችሉ የተለያዩ የሕይወት ሁኔታዎችና የመንፈስ አቋም የሚያስተነትኑ አንዳንድ መዝሙሮች ላቀርብላችሁ እወዳለሁ። ሁላችሁም በመዝሙረ ዳዊት እንድትጸልዩ ያቀረብኩትን ጥሪ ለመድገም እወዳለሁ፡ የቤተ ክርስትያን መጽሐፈ ሰዓታት ሥርዓተ አምልኮ እንድትለማመዱት በጥዋት ኪዳን ዘነግህ ጸሎተ ዋዜማ ኪዳን ዘሰርክም ማታ ከመተኛታችሁ በፊት ደግሞ ጸሎተ ንዋምን እንድታሳርጉ አደራ እላለሁ። ከእግዚአብሔር ያለን ግኑኘት በየዕለቱ ከእርሱ ጋር በመሆን ወደ እርሱ የምናደርገው ጉዞ በታላቅ ደስታና እምነት እውን በመሆን ይበልጥ ባለጠጋ ይሆናል።








All the contents on this site are copyrighted ©.