2011-11-10 17:08:32

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ (09.11.11)


“ቃልህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው።” መዝሙር 119፤105
ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፤ ባለፉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮዎች አጠቃላይ የጸሎት ምሳሌ በሆኑ የዳዊት መዝሙሮች በአንክሮ አስበናል፣ መዝሙሮቹ የኃዘን እንጉርጉሮ የእምነትና የክብር ምስጋና መዝሙሮች ነበሩ፣ በዛሬው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በመዝሙር 119 በዕብራይስጡና 118 በግሪክና ላቲን ቅዱስ መጽሐፍ ስላለው በይዞታውና መንፈሱ ልዩ ስለሆነ መዝሙር ለማስተማር እወዳለሁ፣ ከሁሉም በላይ ልዩ የሚያደርገው ርዝመቱ ነው፤ እያንዳንዳቸው 8 ኍልቆች በያዙ። 22 ክፍሎች የቆመ ሆኖ በአጠቃላይ 176 ኁልቆች አሉት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በዕብራይስጡ ፊደላት ቅደም ተከተል የመቆምና የመገጣጠም ጥበብ አለበት፣ የዕብራውያን ፊደላት 22 ናቸውና፣ እያንዳንዱ የዜማ ክፍል ከእነዚሁ ፊደላት ካንዱ ጋር የተዋሃደ ነው፣ እያንዳንዱ የመዝሙሩ ክፍልም በፊደሉ ይጀምራል፣ እንዲህ ለማድረግ ብዙ ድካም የሚጠይቅና አዲስ የድርሰት ጥበብ የሚያሳይ በመሆኑ ደራሲው ይህንን መዝሙር በማቅረቡ ብርታቱን ያሳያል፣
ያም ሆነ ይህ አሁን ለእኛ የሚያስፈልገን የመዝሙሩ ዋና ይዘትና ዓላማው ነው፣ መዝሙሩ በቶራሕ ላይ እምነት የሚያሳድርና ሞገስ ያለው ዜማ ነው፣ ቶራሕ ማለት በዕብራይስጡ ቋንቋ ሕገ እግዚአብሔር ማለት ሲሆን ይዞታው ሰፋ ያለ ነው። ትምህርት ማስጠንቀቅያን የሕይወት ሕገጋት ሊያሰማ ይችላል፣ ቶራሕ ግልጸት ነው። ማለትም የሰው ልጅን በመጥራት በእምነት መታዘዝንና ለጋስ ፍቅርን የሚጠይቅ የእግዚአብሔር ቃል ነው፣ መዝሙሩ የዚህ የእግዚአብሔር ቃል ውበት አዳኝ ኃይልና ሊሰጠው የሚችል ደስታንና ሕይወትን ያከብራል፣ ምክንያቱም መልእልተ ባህርያዊው ሕግ የባርነት ቀንበር ሳይሆን ነጻ የሚያደርግና ወደ ደስታ የሚያደርስ የጸጋ ስጦታ ነው፣ ዘማሪው “በሕግህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልረሳም” (ኍ.16) ይላል፤ በመቀጠልም “በትእዛዝህ መንገድ ምራኝ ምክንያቱም ደስታየ በትእዛዞችህ ነውና” (ኍ.35) ይላል። እንደግናም “አቤቱ፥ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው።” (ኍ.97) ይላል፣ ለዘማሪው ሕይወት ማእከል የእግዚአብሔር ሕግ ማለትም ቃሉ ነው፣ በእርሱ መጽናናትን ያገኛል፣ የአስተንትኖው ዋና ይዘት ይሆናል፣ በልቡም ይመዘግበዋል፣ የዘማሪው ምሥጢር በኍልቍ 11 እንደሚለው “አንተን እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ አኖራለሁ” እንደገናም በኍልቍ 69 “የትዕቢተኞች ዓመፅ በላዬ በዛ፤ እኔ ግን በፍጹም ልቤ ትእዛዛትህን እጠብቃለሁ።” በማለት ይገልጠዋል፣ የዘማሪው እምነት ልክ እንደ እመቤታችን ድንግል ማርያም የተሰጥዋትን ቃላትና እግዚአብሔር በአማካኝነቱ ይገለጠላት የነበሩ አስደናቂ ፍጻሜዎችን “ሁሉ ትጠብቀውና በልባዋ ታኖረው” (ሉቃ 2፤19) እንደነበረች ሁሉ ቃሉን ከመስማት በልብ ከማኖር ከማስተንተንና ከማፍቀሩ ይወለዳል፣ መዝሙራችን በመክፈቻው “በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ። ትእዛዞቹንም የሚጠበቁ” (ኍ.1-2) “ብፁዓን” ብሎ በማወጅ ሲጀምር ይህንን በሙላት የፈጸመችና ዘማሪው የሚገልጠልውን አማኝ ፍጽምት ምሳሌ የምትሆነን እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት፣ ይህ ብፅዕና እመቤታችን ኤልሳቤጥን ለመጐበኘት በሄደችበት ወቅት “ከእግዚአብሔር ዘንድ የነገሩሽ ቃል እንደሚፈጸም የምታምኚ አንቺ ብፅዕት ነሽ” (ሉቃ 1፤45) ብላ የገለጠችው እውነተኛ ብፅዕት ማርያም ነች፣ ኢየሱስም በሕዝብ መሀከል ሲመላለስ አንዲት ሴት “የተሸከመችህ ማኅፀን ብፅዕት ናት” ባለችው ግዜ “ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁ ናቸው” (ሉቃ 11፤27-28) ብሎ የመሰከረው ለእመቤታችን ማርያምና ለእምነትዋ ነው፣ እውነትም ማርያም ብፅዕት ናት። ምክንያቱም አዳኙን በማኅፀንዋ ተሸክማለችና ሆኖም ግን ከሁሉም በላይ ብፅዕት የሚያሰኛት የእግዚአብሔር ብሥራትን በመቀበልዋና ቃሉን በጥንቃቄና በፍቅር በመጠበቅዋ ነው፣
ስለዚህ መዝሙር 119 በዚሁ የሕይወትና የብፅዕና ቃል ዙርያ የተወሳሰበ ነው፣ የመዝሙር ዋና ይዘት የእግዚአብሔር ቃልና ትእዛዛት ቢሆንም በየኍልቁ የሚደጋገሙ የነዚህ ተመሳሳይ ቃላት ሕጋጋት አዋጆች ትእዛዛት ትምህርቶች ተስጋ ፍርድ የሚሉ ቃላት ተደርድረዋል፣ የቃላቱን እተግባር ላይ መዋል የሚያመለክቱ ግሦችም መከታተል መጠበቅ መረዳት ማወቅ ማፍቀር ማስተንተን በእርሱ መኖር የሚሉ እናገኛለን፣ ጠቅላላው የ22ቱ የመዝሙሩ ክፍሎችና አማኙ ከእግዚአብሔር ያለው የእምነት ግኑኝነት የሚገልጡ ቃላት በሙሉ ሲደረደሩ ክብር ምስግና እምነት ይገልጣሉ፣ ይህ ብቻ ሳይሆን ልመና ማንጐርጐርም እናገኛለን ሆኖም ግን በመለኮታዊው ጸጋና በእግዚአብሔር ቃል ችሎታ የሞሉ ናቸው፣ በስቃይና በጨለማ ስሜት የተመለከቱ አብዛኛዎቹ ስንኞችም ሳይቀር ለተስፋ ክፍት የሆኑና እምነት የዘለቀባቸው ናቸው፣ ዘማሪው በኍልቍ 25 ላይ “ነፍሴ ወደ ምድር ተጠጋች፤ እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ።” እንዲሁም ብኍልቍ 83 “በጢስ እንዳለ አቁማዳ ሆኛለሁና፤ ሥርዓትህን ግን አልረሳሁም።” በማለት በእምነት ይጸልያል፣ ይህ የአማኝ ጥሪ ነው፣ እምነቱ ምንም እንኳ በፈተና ብትገኛ በጌታ ቃል ኃይል ታገኛለች። “በቃልህ ታምኛለሁና ለሚሰድቡኝ በነገር እመልስላቸዋለሁ።” (ኍ.42) በማለትም በሚያስጨንቅ የሞት ሁኔታም ቢገኛ የጌታ ትእዛዛት መጠጊያውና የድል ተስፋው መሆናቸውን በጽናት ያረጋግጣል፣ እንዲህም ይላል “ከምድር ሊያጠፉኝ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር፤ እኔ ግን ትእዛዛትህን አልተውሁም።” (ኍ.87)ለዘማሪውና ለእያንዳንዱ አማኝ የጋለ ፍቅር አለኝታ የሆነው መለኮታዊው ሕግ የሕይወት ምንጭ ነው፣ የጻድቅና ለጌታ ታማኝ የሆነ ሰው የሚታወቅበት ልዩ ምልክት ይህንን ሕግ ልትረዳው ልትጠብቀውና ሁለመናህን በእርሱ እንዲመራ የማድረግ ፍላጎት ነው፣ መዝሙር 1፤2 እንደሚለው ሌት ተቀን ሕጉን የሚያስተነትን ብፁዕ ነው፣ ይህ ሕግ በኦሪት ዘፀአት ስማ እስራኤል በሚለው ተመልክቶ እንዳለ በልብ ማኖር ያለብን የእግዚአብሔር ሕግ ነው፣
“እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ። እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው።” (6፤4-7)
የህልውና መሠረት የሆነው የእግዚአብሔር ሕግ ልብ ብለን እንድናዳምጠው ይጠቀናል። ይህ የምናደርገው እንደ ባርያ ተገደን ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር ልጆች አውቀንና ተማምነን መሆን አለበት፣ ቃሉን ማዳመጥ ማለት ከሕይወት ጌታ ከሆነው ጋር የምናደርገው ግላዊ ግኑኝነት ነው። ይህ ግኑኝነት ተጨባጭ ወደሆኑ ምርጫዎች ተለውጦ የሕይወት ጉዞና ጌታን መከተል መሆን አለበት፣ የዘለዓለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ አለብኝ ብሎ ለጠየቀው ኢየሱስ ሲመልስለት መጀመርያ ትእዛዛትን ጠብቅ ነው ያለው፣ ሆኖም ግን ለፍጽምና። “አንድ ነገር ጐደለህ፤ ሂድ፥ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መስቀሉንም ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ አለው።” (ማር 10፤21) ትእዛዛትን መፈጸም ከኢየሱስ ጋር ሆኖ ኢየሱስን መከተል በኢየሱስ መንገድ መሄድ ነው፣ ስለዚህ መዝሙር 119 ከኢየሱስ ጋር እንድንገናኝ ያደርጋል። ወደ ወንጌልም ይመራናል፣ አሁን በመዝሙሩ አንድ ኁልቍ ላይ ለመቆም እወዳለሁ። ቍ. 57 “እግዚአብሔር ክፍሌ ነው፤ ሕግህን እጠብቃለሁ አልሁ።”ይላል፣ ዘማሪው በሌሎች መዝሙሮችም ጌታ ክፍሉ ውርሻው መሆኑን ይገልጣል፣ በመዝሙር 16፤5 “እግዚአብሔር የርስቴ እድል ፈንታና ጽዋዬ ነው፥” ብሎ ይጸልያል፣ በመዝሙር 73 ደግሞ “እግዚአብሔር የልቤ አለት ነው ለዘለዓለምም ክፍሌ ነው” የሚለው የአማኙ አዋጅ ያመለክታል፣ እንደገናም በመዝሙር 142 “አንተ መጠጊያዬ ነህ፥ በሕያዋንም ምድር አንተ እድል ፈንታዬ ነህ።” በማለት ወደ አምላኩ ይጮኻል፣
ይህ “ዕድል ፈንታዬ” የሚለው ቃል ቀድሞ ነገደ እስራኤል ምድረ ተስፋ በደረሱ ግዜ መሬት ሲከፋፈሉ ለሌዊ ምንም ድርሻ ያልተሰጠውን ያመለክታል፣ ምክንያቱም የሌዊ እድል ፈንታ ራሱ እግዚአብሔር ስለሆነ፣ “እግዚአብሔርም አሮንን አለው። በምድራቸው ርስት በመካከላቸውም ድርሻ አይሆንልህም፤ በእስራኤል ልጆች መካከል ድርሻህና ርስትህ እኔ ነኝ።” (ዘኍ 18፤20) በማለት ኦሪት ዘኍልቍ ያውጃል፣ እንዲሁም በኦሪት ዘዳግም “ስለዚህ ለሌዊ ከወንድሞቹ ጋር ክፍልና ርስት የለውም፤ አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው እግዚአብሔር ርስቱ ነው።” (ዘዳ 10፤9, 18፤2; መጽ ኢያ 13፤33; ሕዝ 44፤28) የሚል እናነባለን፣
ስለዚህ ከነገደ ሌዊ የሆኑ ካህናት እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠውን ተስፋ ለማምዋላት ለሕዝበ እስራኤል ርስታቸው እንዲሆን ከሰጣቸው አገር መሬት መውረስ አልተፈቀደላቸውም፣ (ዘፍ 12፤1-7 ተመልከት) የመረጋጋትና የመኖር መሠረታዊ ነገር የሆነው የመሬት ርስት የበረከት ምልክት ነበር፣ ምክንያቱም መሬት መኖር ማለት ቤት መሥራት ልጆችን ማሳደግ አፍርቶ መከር መሰብሰብ በምድር ፍሬ መኖር ያመልክታልና፣ የቅዱሱና የመለኮታዊ ቡራኬ ጠበቃዎች የሆኑት ሌዋውያን ግን እንደ ሌሎች እስራኤላውያን የዚሁ የቡራኬና ምልክትና የመኖር ምንጭ የሆነ ርስት ሊይዙ አይችሉም፣ በአጠቃላይ ለእግዚአብሔር ስለተሰጡ በእርሱ ብቻ መኖር አለባቸው፣ ርስታቸውና መሬታቸው በመሆን እግዚአብሔር በሙላት ስለሚያኖራቸው። አለምንም ርስት በእግዚአብሔር አሳቢ ፍቅርና በወንድሞቻቸው ልግስና ይጠጋሉ፣
ዘማሪው በመዝሙር 119 “ዕድል ፈንታዬ እግዚአብሔር ነው” በማለት ይህንን እውነት ይገልጣል፣ ለእግዚአብሔርና ለቃሉ ያለው ፍቅር እግዚአብሔርን አንድያ ርስቱ እንዲሆን ቆራጥ ውሳኔ ያደርጋል፣ ቃላቱን ከሁሉ ርስትና የዚህ ዓለም ንብረት በላይ መርጦ እንደ ክቡር ስጦታ ለመጠበቅ ይወስናል፣ ይህ ሐረግ በሁለት መንገድ ሊተረጐም ይቻላል፣ አንድም “ዕድል ፈንታዬ ጌታ ሆይ ቃላትህን እጠብቃለሁ አልኩ” ተብሎ ሊተረጐም ይችላል፣ ሁለቱም ትርጓሜዎች አይቃረኑም። አንዱ አንዱን ያምዋላል፣ ዘማሪው ዕድል ፈንታው እግዚአብሔር መሆኑ። ርስቱ ደግሞ መለኮታዊ ቃላቱን መጠበቅ መሆኑን ይገልጣል፣ ለዚህም በኍልቍ 111 ላይ “የልቤ ደስታ ነውና ምስክርህን ለዘላለም ወረስሁ።” ይላል፣ የዘማሪው ደስታ ይህ ነው፣ ልክ እንደ ሌዋው ለእርሱም ቃለ እግዚአብሔር ርስት ሆኖ ተሰጠው፣
ውድ ወንድሞችና እኅቶች፤ እነኚህ ጥቅሶች ዛሬ ለእኛ ሁላችን ታላቅ አስፈለጊነት አላቸው፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ አለምንም መድን ወይም ዋስትና ጌታን እንደ አንድያ ንብረታቸውና አንድያ የሕይወት ምንጫቸው አድርገው ለጌታና ለቃሉ ብቻ ለመኖር ለተጠሩት ካህናት እጅግ ያስፈልጋል፣ ካህናት በመንግሥተ ሰማያት መልካምነቱና ኃይሉን ለሚገለጥላቸው የድንግልና መሐላ የሚያደርጉት ነጻ ምርጫ በዚህ ይብራራል፣ ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን እነዚህ ጥቅሶች ለሁሉም አማኝ፦ ቅዱስ ጴጥሮስ ለእግዚአብሔር የተገቡ “የካህናት መንግሥት” (1ኛ ጴጥ 2፤9; ራእዩ ለዮሐንስ 1፤6; 5፤1) ብሎ የሚጠራቸው ለእግዚአብሔር ብቻ የሚገቡ ሕዝበ እግዚአብሔርንም ያስፈልጋል፣ በወንጌል መሠረት “ሊቀ ካህናት” ተብሎ የተጠራው ክርስቶስ ለመላው ዓለም ድኅነት መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርበውን ክርስቶስ (ዕብ 2፤17; 4፤14-16; 5፤5-10; 9፤11 ወዘተ) ያሳለፈውን ሕይወት እንዲመስክሩ ለተጠሩ ለሁሉም ምእመናን ያስፈልጋሉ፣ በአንድነትና በደስታ የምንኖርበት ርስታችን እግዚአብሔርና ቅሉ ናቸው፣
እግዚአብሔር ለቃሉ የሚሆን ፍቅር በልባችን እንዲያኖር እና ዘወትር እርሱና የእርሱ ቅዱስ ፍቃድ የሕይወታችን ማእከል ሊሆነን እንዲሰጠን ዘንድ እንፍቀድለት፣ ጸሎታችንና መላው ሕይወታችን በቃለ እግዚአብሔር እንዲበራ መዝሙር 119፤105 እንደሚለው “ቃልህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው።” በማለት በሰው ልጆች መሬት የምናደርገው ጉዞአችን ዋስትና ያለው እንዲሆን ዘንድ እንጸልይ፣ ቃሉን የተቀበለችና የወለደችው። መሪያችንና አጽናኛችን ማርያምም የንጋት ኮከብ በመሆን የደስታ መንገድ ትሁንልን፣
ዘማሪው በመዝሙር 16 ላይ እንደሚለው። እኛም ከጌታ ስለምንቀበላቸው ያልጠበቅናቸውና የማይገባን ዕድል ፈንታዎች ጸሎት ስናሳርግ ደስተኞች ለመሆን እንችላለን፣
“እግዚአብሔር የርስቴ እድል ፈንታና ጽዋዬ ነው፥ ዕጣዬንም የምታጠና አንተ ነህ። ገመድ ባማረ ስፍራ ወደቀችልኝ፥ ርስቴም ተዋበችልኝ።” (መዝ 16፤5-6)









All the contents on this site are copyrighted ©.