2011-09-09 11:14:22

የብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የ2004 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ለምዕመናን ያስተላለፉት መልእክት።


በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
“ኢየሱስም እንዲህ አላቸው የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምን ከቶ አይጠማም፣” (ዮሐ 6.35)
የተወደዳችሁ ምዕመናን
ክቡራን የቤተክርስቲያን አገልጋዮች
በሀገር ውስጥና ከአገር ውጪ ያላችሁ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራውያን ወገኖች"
በጎ ፍቃድ ያላችሁ ሰዎች በሙሉ"
ከሁሉ በማስቀደም ለመላው የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦችና ለካቶሊካውያን ምዕመናን በሙሉ እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ በሰላም አሸጋገራችሁ፣ ልዑል እግዚአብሔር እንኳን ለ2004 ዓ.ም በሰላምና በጤና አደረሳችሁ በማለት ልባዊ የሆነ መልካም ምኞቴን እገልፅላችኋለሁ፣ RealAudioMP3
እግዚአብሔር ሆይ!
ከዘመናት እስከ ዘመናት መጠጊያ ሆነኸናል፤ መዝሙር 89፣1
እኛ የሰው ልጆች የሆንን በሙሉ ይህን የዘመን መለወጫ በዓል ስናከብር በይበልጥ እግዚአብሔር ፈጣሪያችንን የምናመሰግንበት መሆኑን በመገንዘብ ነው፣ እንዲሁም በእሱ መጠጊያነት ያለፈውን ዓመት በሰላም አስፈጽሞን እነሆ አዲሱን ዓመት ስንቀበል ለእርሱ በጎነትና ቸርነት ምስጋና በማቅረብ ሊሆን ስለሚገባ ነው፣
«ነፍሴ ሆይ! እግዚአብሔርን አመስግኚ፤ ቸርነቱንም አትርሺ” ይላል ዳዊት በመዝ.103.2፣
ፈጣሪያችን አዲስ ዓመትን በተለያዩ ወቅቶች ከፋፍሎ ይሰጠናል" ይህም ለኛ ለሰዎች ጥቅም ይውል ዘንድ በማሰብ ነው፣ የአዲስ ዓመት መምጣት አዲስ ሕይወት የሚያመጣልን የሚያድሰንና እንደገና ሙሉ ሰዎች የሚያደርገን ነው፣ ሰለዚህ በዚህ አዲስ ዓመት የተጣሉ ካሉ በዕርቅና በይቅርታ በመታደስ የእግዚአብሔርን ፍቃድ በመፈፀም ለሕይወታቸው ብርታትና ለእምነታቸው ዕድገት የሚበጅ መንፈሳዊ ዕድገት ላይ ለመድረስ የሚያበቃቸውን መልካም ስራ እንዲሠሩ አሳስባለው፣ አምላካዊ ቃልን ሁልጊዜ ማስተዋል ይጠቅመናል! ለዚህም ሐዋርያው ጳውሎስ «ክፉውን ነገር በመልካም ነገር አሸንፍ እንጂ በክፉ ነገር አትሸነፍ” ይላል ሮሜ፤12፣21፣
ዘመናትን የሚሰጥና የሚቆጣጠር እግዚአብሔር ነው! ሰለሆነም እግዚአብሔር የሚነግረንንና የሚፈልግብንን መስማትና ማድረግ ግዴታ አለብን፣ አዲሱ ዓመት በሁላችንም ዘንድ ፍሬ ያለው ሊሆን ይገባል፣ ይህውም ለምድራዊ ኑሮአችን የምናጠፋውን ጊዜና የምናሳየውን ጥረት ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ዘለዓለማዊነት ልናውለውም ይገባል፣ ምክንያቱም ሁሉም የሚሆነው በእግዚአብሔር በመሆኑ በአዲሱ ዓመት አምላክ ይቀርበናል ይባርከናል የእያንዳንዳችንም ወዳጅ መሆን ይፈልጋል፣
በአዲሱ ዓመት እያንዳንዳችን የየራሳችን ዕቅድና ሥራ ይኖረናል፣ በመሆኑም ዕቅዳችንንና ሥራችንን ፈጽመን ልንገኝ ይገባል፣ ለምሳሌ ባሳለፍነው ዓመት ከአቀድናቸው ነገሮች በከፊል የተከናወኑና ያልተከናወኑ ታቅደውም ያልተሞከሩ ነገሮች ይኖራሉ፣ ሰለሆነም ማንኛውም ሰው እግዚአብሔር በሰጠው ጊዜ ያቀደውን ነገር መፈፀም ይኖርበታል እንጂ ማስቀረት የለበትም፣ ጊዜ ወደ ኋላ ሊመለስ አይችልም፣ በሕይወታችን ዘመን ሁልጊዜ እግዚአብሔር አለ! ዘወትር የምንኖረው በእርሱ ፊት ሰለሆነ ጊዜ አለን ብለን የምንተወው ነገር መኖር የለበትም፣ በጊዜያችን ማድረግ የሚገባንን እናድርግ፣ ሕይወታችን ሁልጊዜ በጥሩ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የተመሠረተ መሆን ይገባዋል፣ ይህም ጥሩ ክርስቲያናዊ አካሄድ ያሰከትላል! እርሱም ከፉ በማድረግ ሳይሆን መልካም ነገር በማድረግ መመስከር ነው፣
ዛሬም በዘመናችን ገና ፈውስ ያልገተኘለት የኤች አይቪ ኤድስ በሽታ በመኖሩ" የህብረተሰባችን ግንዛቤም ከፍ ያለ ቢሆንም" ሁላችንም እራሳችንና ቤተሰባችንን ከዚህ በሽታ በመጠበቅ ጤናማ ዜጋ እንዲኖረን አሁንም ግንዛቤን የማስጨበጥ ትምህርቱና ቅስቀሳውን በየአቢያተ ክርስቲያናት" በሐዋርያዊ በማህበራዊና በልማት ስራዎቻችን ቦታና ዕቅዶቻችን ውስጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አደራ እላለሁ፣
መስከረም ሲጠባ ብርሃን ይፈነጥቃል"አበቦች ያብባሉ"ልጆች ይዘምራሉ፣ የአዲስ ተስፋ ጊዜ ነው፣ስለዚህ ሕፃናት"ልጆችና ተማሪዎች በደስታ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወደ ት/ቤት ሲመለሱ በሥነ ምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉና ያገራቸው ብቁ ዜጎች እንዲሆኑ ወላጆች" መምህራንና ህብረተሰቡ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ማስገንዘብ እወዳለሁ፣ ሥነ ምግባር ያለው ዜጋ ፈሪሃ እግዚአብሔር ስለሚኖረውና ሕሊናውም ስለሚገዛው ከወንጀል"ከሙስናና ከኢሰባአዊ ድርጊቶች እራሱንና ሌሎችን ይጠብቃል፣
ክቡራን ምእመናን። ጸሎት የክርስትያኖች ኃይል ነው፣ የሰላም ንጉሥ የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝቦች ሰላም እንዲሰጠን፤ እንዲሁም በሁለቱ ሀገሮች መካከል መልካም ጉርብትና እንዲገነባ፤ አሁንም ሁል ግዜ እንድምለምናችሁ፤ አጥብቀን እንድንጸልይ አደራ እላለሁ፣ ሰላም የጌታ ሥጦታ ነውና፣
ይህን በዓል ስናከብር ድሆችንና አቅመ ደካሞችን በተለያየ ምክንያት ወላጆቻቸውን ላጡ ሕፃናትና ያለጡዋሪ ለቀሩት ቤተሰቦች በማሰብ አቅማችን የሚፈቅደውን በማድረግ በዓሉ የደስታና የፍቅር እንዲሆንላቸው እንድናደርግ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፣
በመጨረሻም በአደረባችሁ ሕመም ምክንያት በሆስፒታሎችና በየቤቱ በሕመም ላይ የምትገኙ ሁሉ “የምሕረት አባት ምሕረቱን ያውርድላችሁ" በከባድ ሀዘን ውስጥም ያላችሁትን “እግዚአብሔር መጽናናትን ይስጣችሁ" በየማረሚያ ቤቶችም ሆናችሁ ይህን ክብረ በዓል የምታከብሩትንም “እግዚአብሔር በምህረቱ ይፍታችሁ" በሥራና በተለያዩ ምክንያቶች ከቤተሰቦቻችሁ ርቃችሁ ለምትገኙ። እንዲሁም በሥደት ላይ ለምትገኙ በሙሉ መልካም አዲስ አመት እንዲሆንላችሁ መልካም ምኞቴ ነው፣
አዲሱ ዓመት። ዘመነ ዮሐንስ፤ የሰላም የጤና የፍቅር የበረከት የብልጽግና የደስታ ዘመን ይሁንልን፣ አሜን!
እግዚአብሔር አገሮቻችንን ይባርክ!!!
+ አቡነ ብርሃነኢየሱስ








All the contents on this site are copyrighted ©.