2011-09-05 17:08:20

የር.ሊ.ጳ የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ (04.09.11)


ውድ ወንድሞችና እኅቶች። በዚች እሁድ የቀረቡልን የቅዱስ መጽሐፍ ንባባት በማኅበረ አማንያን መካከል መኖር ስላለበት ወንድማዊ ፍቅር ይናገራሉ። ይህ ፍቅር በቅድስት ሥላሴ መካከል ካለው ውህደትና አንድነት ይመነጫል፣ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮማውያን በጻፈው መልእክቱ 13።8 ላይ “እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፥ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞታልና። አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በውሸት አትመስክር፥ አትመኝ የሚለው ከሌላይቱ ትእዛዝ ሁሉ ጋር በዚህ። ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ በሚለው ቃል ተጠቅልሎአል።” ሲል ጠቅላላው የእግዚአብሔር ሕግ በፍቅር ሙላት እንደሚያገኝ ይገልጣል፣ የማቴዎስ ወንግል 18 ማኅበረ ክርስትያን እንዴት መኖር እንዳለባቸው ያመለክታል፣ ፍቅር ኃልፊነት እንደሚያሸክምም ያስገነዝባል፣ ስለዚህ ወንድሜ ተሳስቶ ቢበድለኝ ከሁሉም አስቀድሜ በፍቅር መንገድ መቅረብ እንዳለብኝ ሊያመለክት። “ወንድምህ ቢበድልህ፥ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ በደሉን ንገረው። ቢሰማህ፥ እንደገና ወንድምህ ታደርገዋለህ” በማለት ከሁሉም አስቀድመህ ግዜና ሁኔታ መርጠህ በአካል ብቻውን አግኝተህ። ወንድሜ ሆይ አንተ ያልከው ወይንም ያደረግኸው ትክክል አይደለም ትለዋለህ፣ ይህ አግባብ ወንድማዊ መተራረም ይባላል፣ ይህ አገባብ ለተፈጸመው በደል ለመቋወም የሚደረግ ሳይሆን ከወንድማዊ ፍቅር የሚመነጭ ነው፣ ቅዱስ አጎስጢኖስ ስለዚህ ነገር ሲያስተምር “በአንተ ላይ በደል ፈጽሞ የሚያስቀይምህ ለገዛ ራሱ ያቆስላል፣ አንተስ የቆሰለ ወንድምህ አያሳዝንህም ወይ፤ ስለእርሱ አታስብምን፣ መርሳት ያለብህ የተበደልከውን እንጂ የወንድምህን ቁስል አይደለም፣” ይላል፣
ወንድሜ ካልሰማኝስ ምን ይሁን፤ ኢየሱስ በዛሬው ወንጌል ለዚህ ዓይነት ችግር መፍትሔ የሚሆን እንዲህ ሲል ይሰጣል “ባይሰማህ ግን የሁለት ወይም የሦስት ሰዎች ምስክርነት ስለሚጸና ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ይዘህ ወደ እርሱ ሂድ” በማለት በበለጠ እንድትረዳውና የፈጸመውን በደል በይበልጥ ልታስረዳው ሞክር ይላል፣ ሆኖም ግን እነርሱንም አልሰማ ካለ ለማኅበሩ ንገር ይላል፣ ማኅበሩንም አልሰማ ካለ በገዛ ራሱ የፈጠረውን መለየት እንዲረዳ ከቤተ ክርስትያን ኅብረት በመከልከል እንደአረመኔና ተጸጽቶ እንደማይመለስ ኃጢአተና ቊጠረው፣ ይላል፣ ይህ ሁሉ የሚያስረዳው በክርስትያናዊ ሕይወት ጉዞ ውስጥ እርስ በእርስ መተሳሰብና መተሳሰር እንዳለ ያመልክታል፣ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ውሱንነትና ጉድለት በመገንዘብ ወንድማዊ መተራረምን መቀበል እንዳለበትና ሌሎችን በዚህ ልዩ አገልግሎት መርዳት እንዳለበት ያመለክታል፣
ሌላው ፍቅር በማኅበሩ የሚያፈራው መልካም ነገር ደግሞ በጸሎት መተባበር ነው፣ ጌታ ኢየሱስ በዛሬው ወንጌል “ደግሞም እላችኋኣለሁ ሁለቱ ከእናንተ ሁለቱ በምድር ላይ ማናቸውንም ነገር ለመለመን በጸሎት ቢተባበሩ በሰማይ ያለው አባቴ ይፈጽምላቸዋል፣ ምክንያቱም ሁለት ወይንም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት ስፍራ እኔ በመካከላቸው እገኛለሁ” ይለናል፣ እርግጥ ነው የግል ጸሎት አስፈላጊ ነው፣ መቅረት የሌለበትም ነው፣ ሆኖም ግን ጌታ በስሙ በተሰበሰቡ ማኅበር መካከል እንደሚገኝ ያረጋግጥልናል፣ ምክንያቱም ይህች ማኅበር ትንሽም ትሁን ኅብረትዋና አንደነትዋ ፍጹም ተዋህዶ የሆነውን አንድና ሥላሴ የሆነው የእግዚአብሔር አንድነትና ውህደትን ስለሚያንጸባርቅ ነው፣ በክርስትያን መሀከል እንዲህ ዓይነት ስምምነት ያስፈልጋል ለማለት ኦሪጀን ሁላችን በዚህ መመሪያ መመላለስ አለብን ይላል፣ እርስ እርሳችን እንዴት ማረም እንዳለብን መማር አለብን፣ ይህንን ለማድረግ ትሕትና እና የልብ የዋህነት ያስፈልገዋል፣ ለዕርቀ ሰላም ብቻ ሳይሆን ከክርስቶስ ጋር አንድ የሆነች ማኅበር ጸሎትዋ በቀጥታ ወደ እግዚአብሔር እንዲያርግ የሚያደርጉም እነኚህ ትሕትናና የልብ ንጽሕና ናቸው፣
ይህንን ሁሉ በቤተ ክርስትያን እናት በሆነች እመቤታችን ድንግል ማርያምና በትናንትናው ሥርዓተ አምልኮአችን ዝክረ በዓሉን ያስታወስነው የቤተ ክርስትያን ሊቅና ር.ሊ.ጳ በነበረው ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዐቢይ አማላጅነት እንማጠን፣
ከመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ በአንኮና ለሚካሄደው የኢጣልያ ሃገራዊ የቅዱስ ቊርባን ኮንግረስ በሚመለከት ይህንን ብለዋል፣
ዛሬ በአንኮና 25 ሃገራዊ የቅዱስ ቊርባን ኮንግረስ እኔን ወክለው እዛ በሚገኙ ብፁዕ ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ ረ በመሩት መሥዋዕተ ቅዳሴ ተክፍተዋል፣ መልካም የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ እፊታችን እሁድ የዚህ ኮንግረስ መዝግያ ዕለት ላይ ለመገኘት አንኮና መሄዴ ነው፣ አሁንኑ በመጀመር ልባዊ ሰላምታየና ቡራኬየ በዚሁ የጸጋ አጋጣሚ ለሚሳተፉ ሁሉ አድላለሁ፣ ይህ ጸጋ ለሁሉም የሰው ልጅና ለመላው ዓለም የሕይወትና የተስፋ ምንጭ በሆነው በጥቀ ቅዱስ ቊርባን ለሚገኘው ክርስቶስ ስግደትና ክብር በማቅረብ ይገኛል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.