2011-08-29 16:48:56

የር.ሊ.ጳ የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ (28.08.11)


ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ። በዛሬው ወንጌል ጌታ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ስለሕማማቱ እንዲህ ሲል ይገልጥላቸዋል፣ “ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ አለብኝ። እዚያም ከሽማግሌዎች ከካህናት አለቆችና ከሙሴ ሕግ መምህራን መከራ እቀበላለሁ። ከሞትኩም በኋኣላ በሦስተኛው እነሣለሁ” (ማቴ 16።21) ለሐዋርያት ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆነባቸው። ልባቸውም ተረበሸ፣ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ የሆነው ክርስቶስ እንዴት ይህ ሊደርስበት ይችላል፤ እንዴት እስከ ለመሞት ይሰቃያል፤ በማለት ሐዋርያው ጴጥሮስ አሻፈረኝ ይላል፣ ይህ መንገድ አልዋጥ ስላለው ጌታ ኢየሱስን ለብቻ ገለል አድርጎ እንዲህ ሲል ይናገራል፣ “ጌታ ሆይ! ይህ ከቶ አይሆንም! ይህ ነገር በአንተ ላይ አይድርስብህ” (16።22) በዚህ አጋጣሚ በእግዚአብሔር ዕቅድና በሰው ልጅ ዕቅድ ልዩነት እንዳለ እየጐላ መጣ፣ አንድያ ልጁን በመስቀል በመሰዋት በአባታዊ ፍቅር የተቀናጀ ሰው ልጅን የመዳን ሰማያዊ ዕቅድና። ሐዋርያቱ ይጠባበቁት የነበሩዋቸው ፍላጎቶችና ዕቅዶች እንደ ሰማይና ምድር ተለያዩ፣ ይህ ቅራኔ ዛሬ በዘመናችንም እየተደገመ ነው፣ ማለት የሕይወት ጉዞ ዓላማን በማኅበርሰባዊ ኑሮአችን ድል መቀዳጀት መልካም ጤና ማግኘት ሃብት ማካበት ከሆነ ሰብአዊ አስተሳሰብ እንጂ የእግዚአብሔር አስተሳሰብ ሊሆን አይችልም፣ ለዚህም ነው ጌታ ኢየሱስ ጴጥሮስን “ከእኔ ወዲያ ሂድ፥ ሰይጣን፤ አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ስለማታስብ መሰናክል ትሆነብኛለህ” ያለው፣ እንደ ሰው ማሰብ እግዚአብሔርን እጐን ማስቀመጥ ነው፣ የእርሱን የፍቅር ዕቅድ አለመቀበል ነው፣ የእርሱ ጥበብ የሞላበአት ፈቃድ እንዳይፈጸም እንደመግታት ነው፣ ለዚህም ነው ኢየሱስ ለጴጥሮስ ኃይለ ቃል በሞላበት አነጋገር “ሂድ ከኔ ራቅ አንተ ሰይጣን ዕንቅፋት ትሆነብኛለህ” ያለው፣ ጌታ ለሐዋርያት ያስተማረው የሐዋርያቱ ጉዞ እርሱን መከተል ማለት ከእርሱ ጋር መጓዝ ማለትም ፍኖተ መስቀል የመስቀል መንገድ መሆንን ነው፣ በሶስቱም ተመሳሳይ ወንጌሎች ማለት ማቴዎስ ማርቆስና ሉቃስ ጌታን መከተል በዕፀ መስቀል ምልክት ራስን በመካድ መሆኑን ያብራራሉ፣ አለበለዚያ የሰው ልጅ ራሱን ለማግኘት ወይም መዳን አይችልም፣ በቊጥር 24 ላይ ተጽፎ ያለው “እኔን መከተል የሚፈልግ ራሱን ይካድ መስቀሉ ተሸክሞ ይከተለኝ፣ ሕይወቱን ለማዳን የሚፈል ሁሉ ያጠፋታል። ሕይወቱን ስለእኔ የሚያጠፋት ግን ያገኛታል፣ ሰው ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ቢሆንና ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል፤ ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ዋጋ ሊከፍል ይችላል” በማለት ጌታ ኢየሱስ ለሐዋርያት ያቀረበውን ጥሪ ዛሬ ለእኛ በድጋሚ ያቀርብልናል፣ እያንዳንዱ ክርስትያን መስቀሉን በፍቅር ተቀብሎ ከተሸከመ ጌታን እንደሚከተል ያመለክታል፣ ይህ ሁኔታ በዓለም ዓይን ስንመለከተው ሽንፈት ወይንም ጌታ በወንጌሉ እንዳለው ሕይወትን ማጥፋት ነው፣ እያንዳንዱ ክርስትያን መስቀሉን በፍቅር የሚቀበለው መስቀሉን የሚሸከመው ብቻው ሳይሆን ከኢየሱስ ጋር መሆኑን በማወቅና የጌታ ራስን የመስጠት ጉዞ በመካፈል ነው፣ የእግዚአብሔር አገልጋይ ር.ሊ.ጳ ጳውሎስ 6ኛ በጌታ ደስ ይበላችሁ በሚለው ግንቦት 9 ቀን 1975 ዓም በጻፉት ሐዋርያዊ ምዕዳናቸው ስለዚህ ነገር እንዲህ ብለው ነበር፣ “ክርስቶስ ራሱ ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ ከሰው ልብ የማምሰልን ኃጢአት ከሥር ነቅሎ ለመጣልና ለአባቱ ውሉዳዊና የተዋሃደ ትእሳስ ለማሳየት በመስቀል ላይ ሞትን ወዶ ተቀበለው፣” ኢይሱስ ወዶ ሞትን በመቀበል የሰው ልጅ ሁሉ መስቀልን ይቀበላል፣ በዚህም ለሰው ልጅ ዘር ሁሉ የደህንነት ምንጭ ይሆናል፣ የኢየሩሳሌም ቅዱስ ቄርሎስም ስለመስቀል እንዲህ ብሎ ነበር፣ ድል የተቀዳጀው መስቀል በድንቁርና ዓይኑን ለታወረው ሰው ሁሉ ያበራል፣ የኃጢአት ባርያ የነበርውን ሁሉ ነጻ አወጣ፣ ደህንነትን ለሰው ልጅ ዘር ሁሉ ሰጠ፣” እያንዳንዳችን ጌታን በመስቀል መንገድ መከተሉን እንድናውቅና ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚለው “መልካሙንና ደስ የሚያሰኘውን ፍፁም የሆነውንም የእግዚአብሔር ፈቃድ ማወቅ እንትችሉ፣ አእምሮአችሁ ታድሶ ሕይወታችሁ ይለወጥ ዘንድ” (12።2) እንዳለው። በመለኮታዊ ጸጋው እንድንለወጥና እንድንታደስ ዘንድ ጸሎታችን በእመቤታችን ድንግል ማርያም እና ዛሬ ዝክረ በዓሉን በምናከብረው ቅዱስ አጎስጢኖስ እናማጥን፣







All the contents on this site are copyrighted ©.