2011-08-17 16:32:31

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ


ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ። ገና በፍልሠታ በዓል ብርሃን እያሸበረቅን ነው፣ ይህ በዓል የተስፋ በዓል መሆኑን ገልጬ ነበር።። እመቤታችን ድንግል ማርያም መንግሥተ ሰማያት ገባች፣ ለእኛም መድረሻችን ይሄ ነው፣ እኛ ሁላችን መንግሥተ ሰማያት መግባት እንችላለን፣ ዋነኛው ጥያቄ እንዴት፤ የሚለው ይሆናል፣ እመቤታችን ድንግል ማርያም መንግሥተ ሰማያት ገባች። ቅዱስ መጽሓፍም ስለእርስዋ “ጌታ ያላት ነገር እንደሚፈጸም ያመነች” (ሉቃ 1።45) ይላል፣ ስለዚህ እመቤታችን ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር በመተማመን እምነትዋን ገልጠች በዚህም የጌታን ፈቃድ ፈጸመች፣ የመንግሥተ ሰማያት ቀጥተኛ መንገድ እንታድያ አማኝ መሆን በጌታ መታመምን ፍቃዱ መፈጸም፣ ይህ መሠረታዊ የመንግሥተ ሰማያት አቅጣጫ ነው፣ በዛሬው ትምህርተ ክርስቶስ ስለሁሉም ነገር መናገር አልችልም፣ ይልቁንስ ስለ አንድ ነገር ትንሽ ለመናገር እፈልጋለሁ። ከእግዚአብሔር ጋር የመገናኘት ሕይወት ስለሆነው ስለ ጸሎት እናገራለሁ፣ ጸሎት ማለት አስተንትኖ ነው፣ አስተንትኖ ማለት እግዚአብሔር ያደረገልንን ማስታወስ ብዙ መልካም ነግሮቹን አለመርሳት ነው (መዝ 103።2)፣ አጋጣሚ ሆኖ በሕይወታችን ብዙ ግዜ ጎልተው የሚታወሱ መጥፎ ነገሮች ናቸው፣ ሆኖ ግን ከእግዚአብሔር እጅ የምንቀበላቸው መልካም ነገሮችን ማስታወስም ያስፈልጋል፣ ስለዚህ በቤተ ክርስትያን ሕይወት የኅልና ጸሎት በማለት ስለሚታወቀው እንመለከታለን፣ ብዙ ግዜ እኛ የምናወቀው ጸሎት በቃላት ወደ እግዚአብሔር የምናቀርበውን ልመና ነው፣ ይሁን እንጂ በዚህ ጸሎት ልባችንና አእምሮአችን አብረው መጓዝ አለባቸው፣ የዛሬ አርእስት ግን ከዚህ ለየት ያለ ነው፣ ጸሎተ ኅሊና ወይም አስተንትኖ፣ በዚህ ዓይነት ጸሎት ኅሊናችን ከእግዚአብሔር ልብ ጋር ይገናኛል፣ እመቤታችን ድንግል ማርያም የዚህ ዓይነት ጸሎት ታላቅ አብነት ናት፣ ሉቃስ ወንጌልዊ በተለያዩ ክፍሎች “ማርያም ግን ይህንን ሁሉ በልብዋ ታሰላስለው ነበር ይለናል” (ሉቃ 1።19; 51)፣ በልብዋ የምታሰላስላቸው ነገሮች ጌታ ያደረላትንና ያላትን ሁሉም ሲሆን ዋና ተግባርዋ ደግሞ በእነዚህ ነገሮች በማስተንተን ከጌታ ጋር ትገናኝ ነበር። ይህ ግኑኝነትም ከቀን ወደ ቀን በልብዋ እያደገና ጥልቀት እየጨመረ ይጓዝ ነበር።። መልአኩ ገብርኤል ባበሰራት ግዜ ጌታ ያለው እንደሚፈጸም ያመነች እመቤታችን ድንግል ማርያም አምላክና ሰው የሆነውን ጌታ ኢየሱስን በልብዋ ተቀበለችው። እግዚአብሔር ያደረገላትን ነገሮችንና የእርሱን ፈቃድ በዕለታዊ ሕይወትዋ እንዴት መፈጸም እንዳለባት አስተንተነች፣ የእግዚአብሔር ልጅ ምሥጢረ ሥጋዌ እና የእመቤታችን ድንግል ማርያም እናትነት ትላልቅ ምሥጢራት ስለሆኑ በጥልቀት የማሰላሰል ሂደት ያስፈልጋቸዋል፣ እንደ አንድ ቁሳዊ ፍጻሜ በስተ ውጭ ብቻ የሚፈጸም ነገር ብቻ ሳይሆን ጥልቅ በመሆኑ ወደ ውስጥ ተመልሶ ማስተንተን ያስፈልጋል፣ እመቤታችን ድንግል ማርያም ልትተረጉማቸውና የተከደነውን ነገርና የሚያስከትለውን ለመረዳት በአእምሮዋ የነገሮቹን ጥልቀት ታሰላስል ነበረች፣ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ዕለት ዕለት በጽሞና ጌታ በእርስዋ የሚያደርገውን ነገር በልብዋ በማሰላሰል እስከ በትንሣኤ ክብር በተገለጠው የመስቀል ፈተና ኖረች፣ በዚህም እመቤታችን ድንግል ማርያም ተልእኮዋን ተዋጣች፣ ዕለታዊ ግዴታዋን ስትፈጸም ስለጌታ ቃልና ፍቃድ ለማስተንተን ማለትም ጌታ ያደረገላትንና ስለ ልጅዋ ሕይወት ምሥጢራት ለማሰላሰል በኅሊናዋ ውሳጣዊ ግዜና ቦታ መደበች፣
በዘመናችን ግዜው የሚያልፈው የተለያዩ ተግባራትን በመፈጸም ይህም ከስራ መስክ ጀምሮ እስከ ተለያዩ የራሳችን መዝናኛና እንዲሁም ችግሮችና ሐሳቦች የኑሮ ውጣ ውረዶች ነው። ይሁን እንጂ ለኛ ለግላችን ውስጣችንን ለማየትና ለማስተዋል ነፍሳችንን በመንፈሳዊ ምግብ ልንመግባትና ከፈጣሪዋ ጋር እንድትገናኝ ለማስተዋል ግዜ የለንም፣
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የምታስተምረን ምንም እንኳን ሕይወታችንን በተለያየ መስኩ በቀን ውስጥ በተለያየ ስራ ቢጠመድም ነገር ግን በየዕለቱ የተወሰነ ግዜ ለጌታ ፈጣሪያችን መድበን ግዜ በመስጠት ምን ሊያስተምረን እንደሚፈልግ ብናሰላስል በሕይወታችንም በወቅቱና በውኅላም ጣልቃ በመግባት እንዴት እንደሚሰራ ለማየት ግዜ መስጠት እንዳለብን ነው፣
ቅዱስ አጎስጢኖስም የፈጣሪያችንን ሚስጥራት ሲያሰላስል የሚያስተምረን ቃሉን ብቻ መስማት ከማዳመጥ ነው የሚለውን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ከብቶች ምግብ በልተው እነሚያመነዥጉ ሁሉ እኛም እንዲሁ ቃሉን እንደ ምግብ ተመግበን በሰውነታችን ውስጥ እንደሚዋሃድና እንደሚገነባም አድርጎ ያስተምረናል፣
ሌላው ቅዱስ ቦናቬንቱራ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላትን አስመልክቶ የሚያስተምረን እንደየዕለታዊ ምግብ በደንብ ማላመጥና በነፍሳችን ውስጥ እንደእሳት መንደድ እንዳለበት ያስተምረናል።
ስለዚህ በፀሎተ ሕሊና ወይም ሕሊና ምርመራ ማለት ለኛ ግዜ በመስጠት ውስጣችንን በመመልከት የእግዚአብሔር ቃልን በማሰላሰልና ይህም በእምነት ጌታ በሕይወታችን ውስጥ ሊያደርግ የፈቀደውን እንዲያደርግ ነው። ይህም ባለፈውና በሚመጣው ብቻ ሳይሆን ነግር ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌን በመውሰድ ወንጌልን፡ የሐዋሪያት ስራንና የሐዋሪያት መልዕክትን በማንበብ በደንብ ማሰላሰል እንችላለን፣
በተጨማሪም የመንፈሳዊያን ሰዎች ጽሁፍ በማንበብ በመንፈሳዊነት እራሳችችን መመገብ እንደምችልና ይህም በየዕለቱ በምንኖረው ሕይወት ፈጣሪያችን ጎናችን እንደሆነ ይረዳናል አሊያም ከመንፈሳዊ አባቾች ጋር በመወያየትና በመመካከር ያነበብነው ጽሑፍ ጌታ ለኔ ምን ያስተምረኛል ምን ሊናገረኝ ይሻል በማለት ነፍሳችንን እንቀስቅስ እናነቃቃት፣
ቅዱስ መቁፀሪያም ቢሆን እራሱን የቻለ የፀሎት አስተንትኖ ነው። ይህም በተደጋጋሚ ሰላም ለኪ ማርያም ስንል የተለያዩ ሚስጥራትን የምንፀልይበት እንደምናሰላስል ነው፣ ሌላው ደግሞ መንፈሳዊ ተሳትፎችን ቅዱስ ቁርባንን የጌታን እራት በመቀበል ነው። በተለይም በቅዱስ ቁርባን በተለይያ መልኩ ከፈጣሪያችን ጋር በጸሎተ ሕሊና ማሰላሰልና መጠጋት ሲያስተምረን ከዚያም ባሻገር ወደ መንግስተ ሰማይ መንገዱን ያሳየናል፣
ወድ ባልጀሮቼ በየዕለቱ ያለማቋረጥ በትጋት ለጌታ አምላካችን ግዜ ብንሰጠው ለመንፈሳዊ እድገታችን መሰረት ነው፣ ጌታ እራሱ ማንነቱን ሚስጥራቱን ቃሉን በመገለጥ ሲያስተምረን እግዚአብሔር ከኛ ጋር ሲነጋገር ማየቱ እራሱ በጣም ደስ ያሰኛል እሱ ከኔ ምን እንደሚፈልግ ያስተምረኛል ። የሕሊነ ምርመራ ፀሎትም ትርጉሙ ይሄ ነው ሁሌ በእግዚአብሔር ላይ ታምነን በፍቅርና በእምነት እጆቹን እየጠብቅን በሱ ፈቃድ ስንኖር ብቻ ደስተኞች መሆናችንን እናውቃለን፣








All the contents on this site are copyrighted ©.