2011-07-29 13:33:06

የሐዘን መግለጫ መልእክት በቤተክርስትያን


በተለያዩ አገሮች በመጨረሻም ከዚህ ዓለም በሞት እስከ ተለዩበት ቀን እና ሰዓት ድረስ በተባበሩት የአመሪካ መንግሥታት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ወኪል በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ፒየትሮ ሳምቢ፣ የሳንባ ቀዶ ጥገና ሕክምና ተደርጎላቸው በሕክምና ሲረዱ ቆይተው፣ ከትላትና በስትያ ረቡዕ እ.ኤ.አ. ሐምሌ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው የቅድስት መንበር መግለጫ አመለከተ።

በ 73 ዓመት ዕድሜአቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ብፁዕ አቡነ ሳምቢ በሪሚኒ ሰበካ በምትገኘው በሶሊያኖ ሩቢኮነ ክልል የተወለዱ እ.ኤ.አ. በ 1964 ዓ.ም. የክህነት ማዕርግ ተቀብለው፣ በቅድስት መንበር የሐዋርያዊ ልኡክ ኃላፊነት ተመድበው በካሜሩን በእየሩሳሌም በኩባ በአልጀሪያ ኒካራጉዋይ በበልጂም እና በህንድ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ልኡክ በመሆን እንዳገለገሉም ሲገለጥ፣ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 10 ቀን 1985 ዓ.ም. የቤልካስትሮ ስዩም ጳጳስ ሆነው በብሩንዲ ሐዋርያዊ ወኪል ሆነው ተሹመው በብፁዕ ካርዲናል ጆሰፍ ቶምኮ እ.ኤ.አ. ህዳር 9 ቀን 1985 ዓ.ም. ቅብአተ ጵጵስና ከተቀበሉ በኋላ፣ እ.ኤ.አ. በ 1991 ዓ.ም. በኢንዶነዢያ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ወኪል፣ እ.ኤ.አ. በ 1998 ዓ.ም. በቆጵሮስ እና በእስራኤል ጳጳሳዊ ወኪል እና በእስራኤል እና በፍልስጥኤም የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ልኡክ በመጨረሻም ከዚህ ዓለም በሞት እስከ ተለዩበት ቀን እ.ኤ.አ. ከታሕሳስ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምረው በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ልኡክ ሆነው እያገለገሉ እንደንበር የቅድስት መንበር መግለጫ ይጠቁማል።

ነፍሰ ኄር ብፁዕ አቡነ ሳምቢ በእስራኤል እና በፍልስጥኤም የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ልኡክ ሆነው በማገልገል ላይ እያሉ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙት ማኅበረ ክርስትያን ሰብአዊ መብት እና ፈቃድ ጥበቃ ያላሰለሰ ጥረት በማድረጉ ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጎልቶ እንዲታይ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ አገር ቅዱሳት ሥፍራ መንፈሳዊ ንገደት በማነቃቃት አቢይ አስተዋጽዖ እንደሰጡም የቅድስት መንበር መግለጫ ያስታውሳል።

እ.ኤ.አ. መጋቢት 25 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቫቲካን ረዲዮ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ፣ ወደ ቅድስት መሬት መንፈሳዊ ንግደት በማነቃቃት ነጋዲያኑ የዚያ ክልሉ ሁኔታ ቀጥተኛ የዓይን ምስክር እንዲሆን ማድረግ በዚይ ክልል ያለው ችግር በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ በማመን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዱካን በመከተል በዚያ ቅዱስ ሥፍራ መንፈሳዊ ንገደት በመፈጸም ልዩ እና ብቸኛው የክርስትና እምነት ተመክሮ ማካበት እጅግ አስፈላጊ ነው ብለው እንደነበር የቅድስት መንበር መግለጫ በመጥቀስ፣ አክሎም በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም እንዲረጋገጥ በእስራኤል እና በፍልስጥኤም መካከል ፍርሃትን የሚቀሰቅሰው አንዱ በአንዱ ላይ የሚሰነዝረው ወቀሳ ወደ ጎን በማድረግ ሰላም እጅግ የጠማው የፍልስጥኤም እና የእስራኤል ዜጋ ለሰላም የሚደረገው ጉዞ ያለመው ሽቶ ባለ ማረጋገጡ ተዳክሞ እና ተስፋ ቆርጦ እንዳለም ገልጠው፣ ስለዚህ ከሁለቱ አገር ዜጎች ጋር ካካሄዱት ግኑኝነት የክልሉ ሕዝብ ሰላም እንዲረጋገጥ ያለውን ጥማት ለይተው ለመረዳት እንደቻሉም እ.ኤ.አ. ጥር 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቫቲካን ረዲዮ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ አስታውቀው እንደነበርም ይዘከራል።

እየሩሳሌም አንዲት ከተማ ብዙ ችግር የሚፈራረቅባት ብትሆንም ከምትሰጠው አስተዋጽዖ በላይ ለችግር ተጋልጣ እንደምትገኝ ገልጠው፣ ለክርስትናው እምነት እና ክርስያናዊ መለያ ምንጭ እምነት ተስፋ እና ፍቅር የጌታችን ኢየሱስ ክርስትያን የሕይወት ምዕራፎች በሚያወሱ ቅዱሳት ሥፍራ የሚጎላባት ለክርስትያን አማኝ ትልቅ እና አቢይ ትርጉም ያላት ከተማ ነች ሲሉ እ.ኤ.አ. ጥር 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቫቲካን ረዲዮ ጋር አካሂደዉት በነበረው ቃለ ምልልስ ገልጠው እንደነበርም ይታወሳል።

የእየሩሳሌም የላቲን ሥርዓት ለምትከተለው ካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ፓትሪያርክ ብፅዕ አቡነ ፉአድ ትዋል የብፁዕ አቡነ ሳምቢ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ምክንያት ባስተላለፉት የሐዘን መግልጫ መልእክት፣ ነፍሰ ኄር ብፁዕ አቡነ ሳምቢ ቅድስት መሬትን ያፈቀሩ እና በቅድስት መሬት የተፈቀሩ የቤተ ርክስትያን ልጅ በማለት እንደገለጡዋቸው ሲር የዜና አገልግሎት አስታወቀ።All the contents on this site are copyrighted ©.