2011-07-19 14:12:50

ዘመነ ትንሣኤ


የተደፈነ መቃብር፣ የተዘጋ በር የለም!!!- ዘመነ ትንሣኤ
ከዓርብ ስቅለት በኋላ ብዙውን ጊዜ ሀሳባችን ትንሣኤ ማለትም ፋሲካን ማሰብ ሲሆን በሁለቱ መካከል ግን የክርስቶስን ፍቅር የሚገልጽና ለሕይወታችን ትርጉም የሚሰጥ ቀን አለ - ቀዳም ስዑር። በዚህ ቀን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለንና ቤተ ክርስቲያንም እንደምትመሰክርልን ክርስቶስ ከስቅለቱ በኋላ ወደ ሲዖል ማለትም ሞተው ወደ ነበሩት ወረደ። ይህ ዝም ብለን በጸሎተ ሃይማኖት ደግመነው መታለፍ የሌለበትና የብዙ ሃይማኖቶች መጽናኛ ሊሆን የሚገባው መሠረታዊ ሃሳብን የያዘ ነው። ከአዳምና ሔዋን ውድቀት ወዲህ በሙታን ዓለም ተዘግተው የነበሩትን ነፍሳት በርሱ ሞት መፈታታቸውን ለማብሰር ክርስቶስ ወደ ሲዖል ወረደ።
በወንጌሎች ውስጥ የክርስቶስን ሕይወት ስንመለከት እንደ ሰው አባባል ጠያፍ ሊባሉና ለሱ የማይመጥኑ ልንላቸው ቦታዎች ሲገባ ይስተዋላል፤ ሆኖም እሱ በሄደበት ጨለማ ቦታዎች ሁሉ የእግዚአብሔር የሆነውን ብርሃን ያበራል፣ ይፈውሳል። ኃጢአተኞችና የኃጢአተኞች ቦታ ተብሎ እንደ ነውር የሚቆጠሩ ሰዎችና ቦታዎች ጋር ኃጢአትን ሳይሆን ኃጢአተኛውን ፍለጋ ይሄድ ነበር። በነበረው የአስተሳሰብ ግንዛቤም በሽታንና ሞትን በተለየ ሁኔታ መጠየፍ ተቀባይነት የነበረው ወግ ነው፤ ይልቁንም ለመጀመሪያው ክፍለ ዘመን አይሁዳውያን ሰው የተፈጠረው በሕይወት ሆኖ በእግዜአብሔር እንዲደሰት ነው ብለው ያምኑ ስለነበር የሞት ዓለም ማለት መርገም፣ ገሃነም ማለትም ከእግዚአብሔር ህልውና የራቀና ምንም ተስፋ የሌለበት የስቃይ ዓለም ነበር። ስለዚህም ለእነርሱ ክርስቶስ ወደ ሙታን ወረደ ወይም ሞተ ማለት እግዚአብሔር የሌለበት እዚያ የገሃነም አዘቅት ውስጥ ገባ ማለት ነበር።
ለእኛ ለክርስቲያኖች ክርስቶስ በቀዳም ስዑር ወደ ሞት ወረደ ስንል ከአምላክ ተነጥለው በዚያ የሰቆቃ ዓለም ውስጥ ለነበሩ ነፍሳት ተስፋቸውን እንደመለሰላቸውና ከእግዚአብሔር ጋር በኅብረት እንዲኖሩ ማስቻሉን እናምናለን። ይህም በወንጌላት እንደምናነበው ከትንሣኤው በኋላ ደቀ መዛሙርቱ በፍርሃትና ተስፋ ቁርጠት በራቸውን ቆልፈው በተሰበሰቡበት ገብቶ ሰላምለእናንተ ይሁን ሰላምና ስክነትን እንዳበሰራቸው ሁሉ ወደ ሙታንም ወርዶ ድልንና ነጻነትን አበሰረ። ስለዚህ የቀዳም ስዑር የክርስቶስ ተግባር ራሱ የትንሣኤው ዋነኛና ተቀዳሚ ዓላማ እንጂ አንድ ወደ ሲዖል ወረደ የሚል መስመር በጸሎተ ሃይማኖት ላይ ለመጨመር የታሰብ ድርጊት አይደለም።
ይህን እውነት ለክርስቲያናዊ ሕይወታችን ስንተረጉመው ዛሬም በጣም ይሠራል። ክርስቶስ ዛሬም ሰላምንና ይቅርታን ሊያውጅላቸው የሚሹ የተለያዩ የሲዖል ዓይነቶች በሕይወት አሉ፤ የጭንቀት፣ የተስፋ ቁርጠት፣ የደስታ ቢስነት፣ የረዳት የለሽነት፣ የብስጭት፣ ማለቂያ የሌለው የቂምና የጥላቻ ኑሮ፣ በጥልቁ የቆሰለ ልብ ሸክም፣ ራስን የመጥላትና የማጥፋት እቅድ የሰነቀ ስብእና፣ የሱስ ባርነት…ይህንና መሰል ነገሮችን ስናስብ ለክርስቶስ የተዘጋና ማንም ሊገባበት የማይችል ሕይወትና ልብ የተሸከምን፣ እግዚአብሔርም ላይደርስብን እኛም ላንደርስበት የተማማልን እስከሚመስለን ከእርሱ የራቀ ሕይወት በተዘጋ ልባችን ውስጥ እንኖር ይሆናል። ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከዓለም ሁሉ ዘግናኙ እሥር ቤት የተዘጋ ልብ ነው ያሉት እውነት በክርስቶስ ብቻ ነው በሩ ሳይከፈት በውስጥ ገብቶ ሰላም ላንተ/ላንቺ የሚል ብስራት ሊሰማ የሚችለው፤ ይህም የትንሣኤው በዓል ትልቅ መልእክት ነው። ይህን ተስፋ አድርጋ ቤተ ክርስቲያን በዘመነ ፋሲካ ተናዘን መቁረብ እንድንጀምር ታዘናለች፤ ምክንያቱም አንዴ ተዘግቶ እስከ ወዲያኛው ተከርችሞ የሚቀርና ክርስቶስ የማይሰብረው ልብ የለምና ነው። በርግጥ በእንደዚህ ዓይነት አናኗር ውስጥ ራሳችንን ስናገኝ ወደ ሰው ወይም ወደ ነገሮች መፍትሔ ፍለጋ ማሰባችን ግድ ነው ሆኖም ግን የውስጥ ውስጣችን ጋር መድረስ ለሰውና ለነገሮች አይቻላቸውም፤ ክርስቶስ ብቻ በተዘጋውና በተቆለፈው ውስጠኛ ማንነታችን ወይም ግላዊ ሲዖላችን የመግባትና የመታደግ ብቃትም ሆነ ፍላጎት አለው። ይህ የአናኗር ትንሣኤ ሲከናወን ብቻ ነው እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ፋሲካችን ማለትም መሸጋገሪያችን ክርስቶስ ነው ማለት የምንችለው።
መልካም ዘመነ ትንሣኤ!!!
ምንጭ፡ የሲታውያን ድረገጽ
All the contents on this site are copyrighted ©.