2011-06-03 17:05:48

በደርግ ባለስልጣናት ላይ የተፈረደው የሞት ፍርድ ወደ የዕድሜ ልክ እስራት ተቀየረ


ግንቦት 24 ቀን 2003 ዓ.ምበደርግ የአገዛዝ ዘመን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተፈጸመውን በደልና ጥፋት በይቅርታና በዕርቅ ለመጨረስ የኢትዮጵያ የሃይማኖት መሪዮች ባደረጉት ከፍተኛ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ መንግስት የሞት ፍርድ ለተፈረደባቸው የደርግ ባለስልጣናት ይቅርታ እንዲያደርግ ታህሳስ 9 ቀን 2003 ዓ.ም መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ በዚሁ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግስት በ23 የደርግ ባለስልጣናት ላይ የተፈረደውን የሞት ፍርድ ቀይሮ የእድሜ ልክ እስራት ማድረጉን የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ በቤተመንግስት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቀዋል፡፡
በጋዜጣዊው መግለጫ የሁሉም የሃይማኖት አባቶች በመገኘት ንግግር ያደረጉ ሲሆን ብፁዕ አቡነ ብርሀነየሱስ ሊጳጳሳት ዘካቶሊካዊያንን ወክለው በቦታው የተገኙት ክቡር ዶር. አባ ሀይለገብርኤል መለቁ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት ምክትል ጸሐፊና የሐዋሪያዊ ሥራ አስተባባሪ በበኩላቸው ባሰሙት ንግግር ግንቦት 24 ቀን ትልቅ የደስታና የምስራች የሰማንበት ዕለት በመሆኑ ለመንግስታችን ከፍተኛ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ትምህርት ያገኘበት ቀን ነው፡፡ የቀይ ሽብር ሰለባ ቤተሰቦችም መንግስት የሰጠውን ይቅርታ በመቀበል በግንባታው ሥራ መሳተፍ ይገባቸዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች ደክመዋል ‹‹የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው ››ማቴ 5፡9 የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ዛሬ በመስማታቸው የድካማቸው ፍሬ መሳካቱን ያሳያል፤ በጣም ደስ ብሎናል፡፡ ይህ ለትውልድ የሚተላለፍ ከፍተኛ ኃላፊነት ነው፡፡ ሌሎች የሃይማኖት አባቶችም እንደተናገሩት ይህ የተከፈተው የይቅርታ መድረክ ግማሽ ይቅርታ እንዳይሆን ይቅርታው በሙላት ይፈጸም ዘንድ እንጠይቃለን ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት
ማህበራዊና ህዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ








All the contents on this site are copyrighted ©.