2011-05-27 17:56:03

ጸሎት ለ150ኛውን የኣንድነት በዓል ላከበረ የኢጣልያ ሕዝብ


ቅዱስ ኣባታችን ትናንትና ማምሻውን በሳንታ ማርያ ማጆረ ባዚሊካ የኢጣልያ ኣገርን በንጹሕ የእመቤታችን ድንግል ማርያም ልብ ጥበቃ ስር ለማበርከት ጸሎተ መቁጠርያ ኣሳርገዋል። ይህ ጸሎት በኣገሪቱ ውስጥ ስምምነትና አንድነት እንዲኖር ያረገ ጸሎት ነው።
የኢጣልያ የኣንድነት ውል ከተፈረመና ኣንድ ኣገር በመሆን መሥራት ከጀመረችበት ዘንድሮ 150 ዓመት በታላቅ ድምቀት ማክበርዋ የሚታወስ ነው።
መልካም ኣጋጣሚ ሆኖ የኢጣልያ ጳጳሳት ጉባኤ መደበኛ ስብሰባውን በቫቲካን እያካሄደ በመሆኑ ጠቅላላ የኢጣልያ ጳጳሳትም ከቅዱስነታቸው በዚሁ ታሪካዊ የተባለ ስለ ኢጣልያ ኣንድነትና ውህደት ያረገ ጸሎተ መቁጠርያ ተሳታፊ ሆነዋል።
በኢጣልያ ታሪክ ጥንታውያን ሮማውያን ቅድስት ድንግል ማርያምን የሮማውያን ጤናና የኣንድነት እናት በማለት ይማጠንዋት ነበር። የትናንትናው ሥር ዓተ ጸሎትም ይህንን ልማድ የተከተለ ነበር፤ በተጨማሪም ወርኃ ግንቦት ለማርያም የተሰጠ በመሆኑ ጥሩ ኣጋጣሚ ነበር።
ቅዱስነታቸው ከእርሳቸው ጋር በዚሁ ጸሎት ለተሳተፉት ይህንን መልእክት ኣስተላልፈዋል፤ መላውን የጣልያን ኣገር ሕዝብ ለኣንድነት እናት ለሆነችው እመቤታችን ድንግል ማርያም ለማማጠን 150ኛውን የፖሎቲካ የኣገሪቱ ኣንድነት ምክንያት በማድረግ ‘በዚሁ መንፈሳውነትና ሥነ ጥበብ ለዓመታት ያዋሃሃደ ባዚሊካ እንገኛለን። ለዚሁ ጉዳይ በየሃገረ ስብከቶቻችሁ ለየት ባለ ዝግጅትና ኣስተንትኖ እንዳደረጋችሁት ኣውቃለሁኝ፤ ይህ ዛሬ የምናሳርገው ጸሎት የዚሁ ክፍል ነው። እኛ በበኩላችን የእያንዳንዱ ሃገረስብከት ሕይወት ተሳታፊዎች ስለሆን በዚሁ ለእመቤታችን በተሰጠ ወር በየገዳማቱ መካነ ንግደቱ ትናንሽና ትላልቅ ኣብያተ ክርስትያናት በሚደረጉ የምስጋናና የልመና ስለቶች ኣብረን ከማኅበረሰቡ እንጸልያለን። በእመቤታችን ድንግል ማርያም ኣማልጅነት እግዚአብሔር ለዚሁ ሕዝቡ ለሰጠው ጸጋ እናመሰግናለን። ጸሎት ማሳረግ ማለት ለእግዚአብሔር ቦታ መስጠት ማለት ጸሎት ስናሳርግ በደህንነት ታሪካችን እንሳተፋለን። ዛሬ በዚሁ የእመቤታችን ድንግል ማርያም የጸሎት ትምህርት ቤት በሆነው መሰብሰባችን የኢየሱስ ሕይወት በመከተል በዮርዳኖስ ወንዝ ወርደን ከእርሱ የጥምቀት ጸጋ በመቀበል በመንፈስ ቅዱስ እንድንጸና በቃና ዘገሊላ በተደረገው ሰርግ ኣብረን በመቀመጥ ከእርሱ በመጀመርያው ተኣምራቱ የተለወጠውን ጥሩ ወይን ለማጣጣም ከእርሱ ጋር ኣብሮ በቤተ መቅደስ በመግባት የምሥራች ቃሉ በመስማት እንድንዘጋጅ በደብረታቦር ወጥተን መስቀላችንን በትንሣኤው ብርሃን ለመኖር እንድንችልና በቅዱስ ቁርባን ማዕድ ከእርሱ ጋር ተቀምጠን ዘለዓለማዊ መሥዋዕቱን በመሳተፍ ሁሉን ፍጥረት በሚያሳድሱ ኣዲስ ሰማያትና ኣዲስ ምድር እንድንኖር ተጠርተናል’ በማለት ማምሻውን ኣብረው ለሚጸልዩት የጸሎተ መቁጠርያ ክፍል ማለት በብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የተጨመረውን በሓሙስ የሚጸለይ የብርሃን ምሥጢር ትርጉም ኣብራርተዋል።
ቅዱስነታቸው ኣያይዘው እመቤታችን ድንግል ማርያም ለሁላችን የእምነት ኣስተማሪ የሕይወት ኣብነት ስለሆነች እርስዋን መከተልና ከእርሷ መማር እንዳለብን በማመልከት ችግር ቢገጥመንም ለእግዚአብሔር የሚሳነው ስለሌለ እመቤታችን በጸሎትዋ እንዳለችውም ሁሌ ትላልቅ ነገሮች በማድረግ ላይ ስለሆነ ኣይዞኣችሁ፤ እንደማርያም ኣለምንም መጠራጠር ሁሉን ነገር በእግዚአብሔር እጅ ያስቀመጣችሁ እንደሆነ ገና እግዚአብሔር ትላልቅ ነገሮች ሊያደርግ ነው፡ በማለት ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል።
በመጨረሻም፤ እግዚአብሔር የሰላም የወንድማማችነትና የጽኑ ብልጽግና ስጦታዎች ያድላቸው ዘንድ ሁሉንም የኢጣልያ ህዝብ በኣንድነት እናት በሆነቸው እመቤታችን ድንግል ማርያም እናማጥነው፤ ሲሉ በሥነ ሥርዓቱ ለተሳተፉት ሁሉ እና ማኅበረሰቦቻቸውን ባርከዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.