2011-05-05 09:36:41

የር.ሊ.ጳ. ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቅዱሳት አጽም


እ.ኤ.አ. ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. እንተ ላእለ ኵሉ ቤተ ክርስትያን በቅዱስ ጴጥሮስ ተከታይ ውሳኔ መሠረት በይፋ ብፅዕና ያወጀችላቸው የር.ሊ.ጳ. ብፁዕ ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቅዱስ አጽም ከውስጥ እና ከውጭ አገር የመጡት በብዙ ሺህ የሚገመቱት መንፈሳውያን ነጋድያን በተለየ የአምልኮ ሥርዓት አማካኝነት አክብሮቱን እና እግዚአብሔር እኚህ አቢይ ር.ሊ.ጳ. ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ስለ ሰጠን በቅዱስ አጽማቸው ፊት ምስጋናውን እና አምልኮውን ከቀረበ በኋላ ይኸው ከትላትና በስትያ ጀምሮ በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ውስጥ በሚገኘው የቅዱስ ሰባስቲያን ቤተ ጸሎት ውስጥ እንዲያርፍ መደረጉ ተገልጠዋል።

በዚህ የር.ሊ.ጳ. ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቅዱስ አጽም ወደ ቅዱስ ሰባስቲያን ቤተ ጸሎት ለማድረስ በአገረ ቫቲካን ኅየንተ ብፁዕ ካርዲናል አንጀሎ ኮሞስትሪ ተመርቶ በተካሄደው ሥርዓተ ዑደት የሐዋርያዊ ቤተ ኑዛዜ ጉባኤ አባላት የቅድስት መንበር ዋና ጸሓፊ ብፁዕ ካርዲናል ታርቺዚዮ በርቶነ እና ሌሎች የቅዱስ አባታችን የቅርብ ተባባሪዎች ብፁዓን ካርዲናሎች እና ብፁዓን አቡኖች እንዲሁም የር.ሊ.ጳ. ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የግል ዋና ጸሓፊ በመሆን ያገለገሉ የክራኮቪያ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ስታኒስላው ድዝዊች እና ከኢጣሊያ እና ከውጭ አገር የመጡ ምእመናን መሳተፋቸው ሲገለጥ፣ ብፁዕ ካርዲናል ኮማስትሪ ባሰሙት የምስጋና ቃል፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኚህ ቅዱስ እረኛ የበጎቹ እውነተኛ አርአያ አባት ለቤተ ክርስትያኑ ስለ ሰጠ የተመሰገነ ይሁን፣ በሁሉም ቅዱሳት አማላጅነት በተለይ ደግሞ በሁሉም አርእስተ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱሳት እና ብፁዓን አማላጅነት በቅድስና የጉዞ ጎዳና እንድንገኝ አግዚአብሔር ይርዳን እንዳሉ የቅድስት መንበር መግለጫ ያመለክታል።

ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ የር.ሊ.ጳ. ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዓመታዊ በዓል የመለኮታዊ ምኅረት ዓመታዊ በዓል ቀን ጋር ተያይዞ እንዲውል ውሳኔ ማስተላለፋቸው ቀደም ተብሎ መገለጡ የሚታወስ ሲሆን ይኸንን ጸጋ ከተቀበሉት የመለኮታዊ ምኅረት አቢያተ ክርስያን ውስጥ ከክራኮቪያ ሊቀ ጳጳስ የር.ሊ.ጳ. ብፁዕ ዮሓንስ ጳውሎስ ቅዱሳት ትሩፋት የተረከበ እዚህ ሮማ የቅዱስ መንፈስ ዘ ሳሲያ የመለኮታዊ ምኅረት ቅዱስ ሥፍራ መሆኑ ሲገለጥ የዚህ ቅዱስ ሥፍራ አለቃ ብፁዕ አቡነ ጆሰፍ ባርት ከቫቲካን ረዲዮ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ፣ ይህ ቅዱስ ሥፍራ በቅዱስ አባታችን ውሳኔ መሠረት የመለኮታዊ ምኅረት አምልኮ እና ስግደት መስፋፋት ቀዳሚ ተሳታፊ እንዲሆን በማለት በመለኮታዊ ምኅረት ስም በመጥራት ለዚህ ሥም በመሰጠታቸው ምክንያት እና የር.ሊ.ጳ. ብፁዕ ዮሓንስ ጳውሎስ ቅዱሳት ትሩፋት እንዲያርፍበት በመደረጉ አቢይ ጸጋ ነው ካሉ በኋላ እ.ኤ.አ. ነሓሴ 17 ቀን 2002 ዓ.ም. ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ምኅረት ከአጽናፍ አጽናፍ እንዲስተጋባ በጸለያቸው ዘክረው ይኸንን ጸሎት መርህ በማድረግ ይኽ ቅዱስ ሥፍራ የር.ሊ.ጳ. ብፁዕ ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የመልኮታዊ ምኅረት ሥልጣናዊ ትምህርት እና ምዕዳን የሚያስፋፋ ጭምር ይሆናል። ስለዚህ በተለያየ ችግር የሚሰቃየው ሁሉ ተስፋ ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንዳሉትም አዲስ ብርኃን እንዲያገኝ የሚጸለይበት ቅዱስ ሥፍራ ነው ብለዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.