2011-04-26 12:20:17

ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ክርስቶስ የነጻነት የፍትሕና የሰላም ጐዳና ይክፈትልን፤


ቅ.ኣ.ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ በበዓለት ትንሣኤ ምክንያት በየዓመቱ እንደሚያደርጉት ሁሉ ትናንትና በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ ለተሰበሰቡት ከ100 ሺ በላይ ለሚሆኑ ም እመናን ‘ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ክርስቶስ የነጻነት የፍትሕና የሰላም ጐዳና ከፈተልን’ ሲሉ ስለትንሣኤ ምሥጢር ካስተማሩ በኋላ ኡርቢ ኤት ኡርቢ ለከተማዋና ለመላው ዓለም የተሰኘውን የትንሣኤ መልካም ምኞት በተለያዩ ቋንቋዎች ገልጠዋል።

ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን ሲከፍቱ ‘ክርስቶስ ተንሥኣ እሙታን፤ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ’ የሚለው የሰው ልጅ ታሪክን ለኣንዴና ለመጨረሻ የለወጠው መልካም ዜና ዛሬም ከሁለት ሺ ዓመታት በኋላ በመላው ዓለም እያስተጋባ ነው። የዕለቱ መዝሙር እንደሚለው ‘ይትፌሣሕ ሰማይ ወትትሐሰይ ምድር፤ ማለትም ሰማይና ምድር ደስ ይበላቸው’ ይህም የሰው ልጅ የመዳን ጎህ መቅደዱን የሚያመለክት ትልቅ ደስታ በኢየሱስ መዳኑን ነው።

ዛሬ የምንኖርባት ዓለም በመገናኛ ብዙኃን እጅግ ወደፊት መጥቃ ብትገኝም የክርስትና እምነታችን የሚመሠረተው ከሙታን ተለይቶ የተነሣውን ክርስቶስ ያዩ ሰዎች በሰጡን ምሥክርነት ይመሠረታል።

የክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ መነሣት የኣስተንትኖ ውጤት ኣይደለም። የሰቂለ ኅሊና ውጤትም ኣይደለም። ከታሪክ ባሻገር የሚጓዝ ፍጻሜ ነው፤ ሆኖም ግን እርግጠኛ በሆነ ወቅት የተከናወና በሰው ልጅ ታሪክ የማይደመሰስ ማኅተም ያኖረ ፍጻሜ ነው። የጌታ ኢየሱስ መቃብር በመጠበቅ ላይ የነበሩት ወታደሮች ዓይኖችን ያጭበረበረ ብርሃን ግዜና ቦታን ተሻግሮኣል፤ የተለየ ብርሃን ነው፤ መለኮታዊ ብርሃን ነው፤ ይህ ብርሃን የሲኦልና የሞት ጨለማን ጥሶ የእውነትና የርኅራኄ ጮራ የሆነውን የእግዚኣብሔር ጮራ ለዓለም ያስገኘ ብርሃን ነው።

የክርስቶስ ትንሣኤ ለሰው ልጅ ተስፋ ኃይልና ትርጉም ይሰጣል፡ ሆኖም ግን በዘመናችን ከትንሣኤ ሃሌ ሉያ ዜማ በትይዩነት የሚሰማ ኣሰቃቂ የሥቃይ እሪ የድህነት የረሃብ የሕመም የውግያ የዓመጽ እሮሮ እየተሰማ ነው፡ ክርስቶስ የሞተው ይህንን ለማቃለል ቢሆንም ቅሉ የሰው ልጅ ልቅሶ ገና ኣላበቃልም፤

ስለዚህ ለሁሉም የሰው ልጆች ከሁሉ ይልቅ ግን ባሁኑ ግዜ የቀራንዮ ሕማማት በሚያሳልፉ ማኅበረሰቦች ይህ መልእክቴ እንደ ትንቢታዊ መልካም ዜና እንዲደርስ እፈልጋለሁ፤ ‘ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ክርስቶስ የነጻነት የፍትሕና የሰላም ጐዳና እንዲከፍትላቸው’ ምኞቴ ነው።

ቅዱስነታቸው ለመላው ዓለም ዕርቅና ሰላም እንዲወርድ ምኞታቸው ሲግለጡ በተለይ በቅድስት መሬት በመካከለኛው ምሥራቅና በኣይቮሪ ኮስት የሰላምና የሰው ልጅ ክብር ብርሃን የሆነው የትንሣኤ ብርሃን በሃገራቱ ላይ ነግሦ ባለው የመለያየት የጥላቻና የዓመጽ ጨለማን ድል እንዲነሣ፤ እንዲሁም በሊብያ የብዙ ሰዎች ሕይወት በመቅዘፍ ላይ የሚገኘውን ጦርነት እንዲወገድ መፍትሔውም ከጦርነትና ከጦር መሣርያ ሳይሆን ከውይይትና ከስምምነት መሆኑን በመረዳት በግጭቱ መሃከል ታጉረው ላሉ ደግሞ ሰብ ኣዊ እርዳታ እንዲደረግላቸው ኣደራ ብለዋል።

የጦርነት የረሃብና የኣምባገነን ጨቋኝ መንግሥታት ሰለባ በመሆን በስደት ላይ ስለሚገኙት ኣውስተውም እንዲህ ብለዋል። ‘ባለ በጎ ፍቃድ ሰዎች እነኚህን ችግረኞች ለመቀበል ልባቸውን እንዲከፍቱ ጌታ በትንሣኤው እንዲያብራላቸውን ለስደተኞች ወንድሞቻችን ኣጋርነት በማሳየት ተጨባጭ እርዳታ እንዲያደርጉ ኣሳስባለሁ፤ ኣብነታዊ በሆነ መንገድ ምስክነታቸውን ለሚሰጡ በለጋስነት እንዚህን ችግረኞች በመርዳት ለሚገኙት ደግሞ የሚያደርጉትን በጎ ሥራ በልብ እንደምናደንቀውና እንደምናመሰግናቸው ለመግለጥ እወዳለሁ’ ሲሉ ሁላቸው የተቻላቸውን እንዲያበረክቱ ኣደራ ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በስብከታቸው መገማደጃ ላይ በባህርያዊ ኣደጋ ለተጐዱ ወገኖች በተለይም ብዙ ሕይወትና ንብረት የወደመባቸው የጃፓን ሕዝብን በማስታወስ ጽናትና ተስፋ አንዲያገኙ ምኞታቸውን ገልጠዋል።

በመጨርሻም በእምነታቸው ምክንያት በስደትና በሥቃይ ለሚገኙት ክርስትያኖች በማስታወስ ‘የጌታ ትንሣኤ መልካም ዜና ጽናትና እምነት ይስጣቸው’ ብለዋል።

በልባችን ውስጥ ደስታና ኃዘን ኣለ፤ እፊታችን ላይ የደስታ ፈገግታና የሥቃይ እንባ ኣለ፤ በዚህ ዓለም እስካለን ድረስ ሕይወታችን እንዲሁ ነው፤ ሆኖም ግን ከሙታን ተልይቶ የተነሣው ክርስቶስ በመሀካላችን ይገኛል ከእኛ ጋር ይራመዳል፤ ስለዚህ ለተል እኮኣችን ታማኞች በመሆን ፊታችን ወደ ሰማይ በማዞር እየዘምርን እንራመድ’፤ ካሉ ብኋላ በ65 ቋንቋዎች የመልካም ትንሣኤ ምኞት ገልጠዋል፤ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝብም ብሩክ ፋሲካ ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጠዋል።







All the contents on this site are copyrighted ©.