2011-04-21 12:01:46

የኢትዮጵያ ካቶሊላዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ የ2003 ዓ.ም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤን በዓል በማስመልከት ለመላው ምዕመናን ያስተላለፉት መልዕክት፡፡


RealAudioMP3 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ክቡራን ምዕመናን

በአገር ውስጥና በተለያየ አገራት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት

ክቡራን የቤተክርስቲያን አገልጋዮችና

በጎ ፍቃድ ያላችሁ ወገኖች ሁሉ፣

ከሁሉ አስቀድሜ እግዚአብሔር አባታችን በምህረቱና በቸርነቱ ሁላችንንም በሰላም ጠብቆ ይህን የጌታችን የመድኃኒችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤን በዓል እንድናከብረው ለዚች ዕለት ያደረሰን አምላክ የተመሰገነ ይሁን በማለት በኢትዮጵያ ካቶሊላዊት ቤተክርስቲያንና በራሴ ስም መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ፡፡ ‹‹በመስቀል ላይ የመለኮትን ውርደት ከምንም ሳይቆጥር የመስቀልን መከራና ሞት ታገሠ፤በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝም ተቀመጠ››፡፡ (ዕብ .12፤2)

አምላካችን ስለወደደን በፊቃዱ የሰዎች ልጆችን በደል እርሱ ተሸክሞ እስከ መስቀል ሞት ድረስ ታዛዥ ሆኖአል፡፡ በትህትና ከሁሉም ራሱን ዝቅ አድርጐ ሞትን ቀመሰ፡፡ እርሱ በእግዚአብሔር ፀጋ ስለሁላችን ሞተ፤ ይህን ሁሉ ስንመለከት ምን ያህል የሰው ልጆችን ለማዳን የፍቅር ሥራ እንደሠራ ልብ ልንል ይገባል ፡፡

ክርስቲያኖች በክርስቶስ ኢየሱስና አዳኝ በሆነ መስቀሉ ምህረት ተደግፊው ከድካማቸው መነሣት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም የመስቀሉ ፍቅር ዘለዓለማዊ ነው፡፡ ፍፁም ነው፡፡ በጌታችን ኢየሱስ ሁል ጊዜ መዳንና መጠገን ስላለ እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ተቤዥተን ሕይወትንና ተስፋን ስለሰጠን ልናመስግነው ይገባል፡፡

ሐዋርያው ጴጥሮስ ‹‹ክርስቶስ ራሱ ወደ እግዚአብሔር ያቀርበን ዘንድ እርሱ ፃድቅ ሆኖ ሳለ ጽድቅ ለሌለን ለእኛ በኃጢያታችን ምክንያት በማያዳግም ሁኔታ አንድ ጊዜ መከራን በመቀበል ሞቶአል፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈሱ ግን ህያው ሆነ ››ይላል ፡፡ (1ኛ ጵጥ. 3፤18)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፋሲካችንና ትንሣኤያችንም በመሆን በእርሱ ትንሣኤ የኛን የክርስቲያኖች ትንሣኤ በማብሰር እርሱ የትንሣኤ መጀመሪያ ሆኖ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ መልካም ሥራ የሚሠሩ የትንሣኤ መጀመሪያ የሆነውን ክርስቶስን መስለው መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቶ በሞቱ ሕይወትን አስገኘልን (ማቴ28፤1-10) ፡፡ ሞት የሰው ልጅ መደምደሚያ ሳይሆን ወደ ዘለዓለም ሕይወት መሸጋገሪያ ነው ፡፡ ስለዚህ በእምነታችን ጸንተንና በርትተን ከፊታችን ወዳለው የዘለዓለም ተስፋ እናቅና « ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፡፡” (ዮሐ፤11፤25)

በጌታ ትንሣኤ ተስፋችን ለምልሞአል፤ መዳናችንም ተረጋግጦአል፡፡ ስለዚህ ትንሣኤውን ስናከብር በትንሣኤው ለመኖር ነው፡፡ ስለሆነም እኛ ክርስቲያኖች ሁልጊዜ ልንወደውና ልንከተለው ያስፈልጋል ፡፡ በእምነት ሆነን በጽድቅ ተግባራት ላይ ስንሳተፍ እውነተኛ ክርስቲያኖች በመሆን ለብዙ ክርስቲያኖች አርዓያ እንሆናለን፡፡ ዓለም ጣፋጭነትን ያገኝው በክርስቶስ ሕይወት ነው፡ በመሆኑም ምዕመናን በዚህ ትንሣኤ ራሳችውንና ማንነታቸውን ለእግዚአብሔር መስጠት ይኖርባቸዋል ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁላችንም መልካም እምነት እንዳስተማረን ሁሉ እኛም መልካም ምግባር ይዘን መጔዝ አለብን፡፡ ለዚህም ጌታችን ባስተማረን ፀሎት «እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን” ብሎ መፀለይ ቀላል የማይሆንላቸው አሉ፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቻችን «በደሉን” ወይም «ጎዱን; የምንላቸው ሰዎች ያደረሱብንን በደል መርሳት ስለሚያስቸግር ነው፡፡ ቢሆንም ግን ይህ የጌታ ጸሎት ሁልጊዜ ይቅርታ በመስጠትና በመቀበል ሕይወት ውስጥ መኖር እንዳለብን ያስገነዝበናል ፡፡በመሆኑም የሃማኖት አባቶች የጀመሩት የዕርቅ ሥራ በክርስቶስ ትንሣኤ እንዲቀጥልና ፍሬያማ እንዲሆን ሁላችንም ከልብ እንድንፀልይ አደራ እላለሁ፡፡ለመጪው ትውልድ ይቅርታን እንጂ ቂም በቀልን ማውረስ አይገባም፡፡

የተወደዳችሁ ምእመናን በዚህ በፋሲካ በዓል ዕለት ብዙ የሚደሰቱ እንዳሉ ሁሉ ብዙዎች በችግር ላይ እንዳሉ ልብ ልንል ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በችግርና በህመም፤በስቃይ እና በጎዳና የሚኖሩ እንደዚሁም በኤች አይ ቪ ሕመም ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ህፃናት ብሎም ሰብሳቢና ጧሪ ያጡ አረጋዊያንና አረጋዊያት ስላሉ ሁላችንም በተቻለን መጠን በክርስቲያናዊ መንፈስ ልንረዳቸውና በዓሉን በጋራ እንድናከብር አሳስባለሁ፡፡

የትንሣኤው ክብር የሁላችንም ነውና በአሁን ጊዜ መንግሥት ሥራ ለሌላቸው ወገኖች ትኩረት ሰጥቶ በተለያዪ የሙያ መስኮች በማስልጠን ወገኖቻችን ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ የያዘውን ዕቅድ እያደነቅን ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም የሥራ ባህልን በመልመድ ሥራን በማክበር አገራችንና ህዝባችንን ከድኅነት ለማላቀቅ የሚደረገው እንቅስቃሴ እግዚአብሔር እርዳታ ተጨምሮበት ውጤታማ እንዲሆን ሁላችንም እንድንቀሳቀስ አደራ እላለሁ፡፡

በማጠቃለያም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች፤በመላው ዓለም ምትገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖች፤ ለህሙማን፤ በተለያዩ ሥራ ላይ ላላችሁ፤ ለአገር ደኅንነት ሥራ ለተሰማራችሁ ሁሉ፣ እንደዚሁም በማረሚያ ቤቶች ለምትገኙ ወገኖች በሙሉ እንኳን ለሁለት ሺህ ሦስት ዓ.ም የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ እላለሁ፡፡

የሰላም ንጉሥ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓሉን የደስታና የምህረት በዓል ያድርግልን፡፡



እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክልን!!!





+አቡነ ብርሃነየሱስ

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን








All the contents on this site are copyrighted ©.