2011-04-15 17:07:13

ዘኒቆዲሞስ


(ከሲታውያን ድረ ገጽ የተወሰደ) ከእኔነት ቅርፊታችን መውጣት - ዳግም መወለድ 
ምስባክ ዘደብረ ዘይት፦ ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ፤ አመከርከኒ ወኢተረክበ ዓመፃ በላዕሌየ፤ ከመኢይንብብ አፉየ ግብረ ዕጓለ እመሕያው።

ልቤን ፈተንከው በሌሊትም ጎበኘኸኝ፤ ፈተንከኝ ምንም አላገኘህብኝም፤ የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው።

መዝ.16:3-4

ንባባት፦- ዮሐ.3:1-11 - ሮሜ.7:1-18 - 1ዮሐ.4:18-21 - ሐዋ.5:34-42

ለሕማማት ሳምንት ብሎም ለብርሃነ ትንሣኤው በምንዘገጃጅበት በዚህ የጾም ወቅት ላይ የዛሬው ሰንበት ወንጌል የኒቆዲሞስንና የክርስቶስን ግላዊ ንግግር ያቀርብልናል። ኒቆዲሞስ አንድ ታሪካዊ ሰው መሆኑን ወንጌሉ አስረግጦ ቢነግረንም ግቡ ግን እንደወትሮው በኒቆዲሞስ ቦታ ራሳችንን አስቀምጠን ከኢየሱስ ጋር ግላዊ የነፍሳችንን ጉዳይ እንድንወያይ ለመጋበዝ ነውና ለዚህ ዓላማ የሚያግዙንን አንዳንድ ነጥቦች እንካፈል።

ኒቆዲሞስ በጊዜው በነበሩ የሰው መስፈርቶች በሙሉ “አንቱ” ሊያሰኙት የሚችሉ ነገሮችን ያሟላ ሰው እንደነበረ ወንጌል “ከፈሪሳውያን ወገን የሆነ፣ የአይሁድ አለቃ፣ የእስራኤል መምህር መሆኑን” በማለት ያስረዳናል። በሰው እይታ አዋቂና የተከበረ ሰው እንደነበረ አያጠራጥርም፤ በክርስቶስም ዓይን የተከበረ መሆኑ ቢቀጥልም አዋቂነቱ ግን ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። ኢየሱስ “አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ይህን አታውቅምን?” ሲለው ገና ማወቅ የሚገባው ብዙ ነገር እንዳለ ያሳየናል። ለኛ ይህ መነሻ ነጥብ ነው፤ በኢየሱስ ፊት ሁል ጊዜ ነገሮችን ለማወቅና ለማድረግ ዝግጁ መሆን አለብን።

ማንም ሰው በእግዚአብሔር ቃል ፊት ሁሉን ጠቅልሎ ሊያውቅ አይችልም። ስለ ደኅንነት ቢወራ ገና በየቀኑ ማወቅ የሚገባንና ማድረግ የሚጠበቅብን ነገር አለ፤ ስለ ማፍቀርና ይቅር ማለትም ቢነገር በየቀኑ የሚያጋጥሙንን ሰዎች ገና እንደ አዲስ ለማፍቀርና ይቅር ለማለት በየቀኑ ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን እንጂ ባለፉት ጊዜያት አፍቅሪያለሁ፣ ይቅር ብያለሁ…ብለን የምንደመድመው ጉዳይ አይደለም። በሕይወት እስካለን ድረስ ዘወትር ለበለጠ ነገር መዘጋጀት አለብን። “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው እንደገና ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” የሚሉት የክርስቶስ ቃላት የሚያንጸባርቁትም እውነት ክርስትና አንዴና ለሁልጊዜ በአንድ ቀን ተአምራዊ ለውጥ ያከተመለት ሕይወት ሳይሆን ሁሌም ለማያልቀው የእግዚአብሔር ጸጋ ራስን ከፍቶ እንደ ሕጻን መሆንን የሚጠይቅ ጥሪ መሆኑን ነው። ድኛለሁ፣ አውቂያለሁ፣ ዳግም ተወልጃለሁ፣ በቃ… ብለን የቆምን ሰዎች እንዳንሆንና ሁለነገራችን በየቀኑ እያደገ ሲሄድ እምነታችንን በየቀኑ ሳናሳድገውና ሳንኖረው የሆነ ደረጃ ላይ ቆሞ እንዳይሆን ራሳችንን እንመርምር።

ኒቆዲሞስ የክርስቶስ ዳግም ተወልድ የሚለው ትእዛዝ ግራ ቢገባው “እንዴት ሊሆን ይችላል?” ይህ የአንዲት ነፍስ ቀጣይ ንግግር ነው። ነፍስ ስለማንነቷና ምንነቷን ከመጠየቅ መቼም ቢሆን አትቦዝንም። ሁሌም “እንዴት” ትላለች፤ እንዴትና ወዴት መጓዝ እንዳለባት ታስባለች። የሆነ ነገሮችን የምታውቅ ይመስላታል ሆኖም ግን ነገሮችን ጠንቅቃ አውቃ የመጨረስ ብቃት ስለሌላት በእግዚአብሔር ቃል ፊት ሁሌ “ምን፣ እንዴት ማድረግ አለብኝ” ማለቱ የግድ ነው። ምናልባት በሰው ፊት ስንቆምና ስንገኝ የፈለግነውን ስእላችንን ማስተላለፍ እንችል ይሆናል፤ በክርስቶስ ፊት ግን ገና ብዙ ማወቅ የሚገባን ነገር እንዳለ እንገነዘባለን። ለዚህም ነው በርሱ ቃል ፊት መምሰልና ማስመሰላችን ለማንነታችን ቦታቸውን የሚለቁት። በሰዎች ፊት መስለን የምንውለው ነገርና በክርስቶስ ፊት የሆንነው ነገር እንዲመሳሰል በጣርን መጠን ዳግም መወለድን እየተገበርነው እንሄዳለን።

መወለድ ማለት መለየት፣ ከአንድ ዓይነት አናኗር ወደሌላ ዓይነት መምጣት ማለት ነው። ልክ ሕጻን ሲወለድ ሕይወቱ ቢቀጥልም ከነበረበትና ራሱን ያኖርበት ከነበር ከእናቱ ማሕጽን መውጣት እንዳለበት በእምነትም ማደግ ካለብን እንዲሁ መላቀቅ የሚገባን ነገሮችን ማሰብ አለብን። ካለነርሱ ልንኖር የማንችል የሚመስለንን ነገር ለመተው መወሰን አለብን። ሕጻን ሲወለድ የምግብ ማስተላለፊያ የነበረው እትብቱ መቆረጥ የግድ ቢሆንም በሌላ መልኩ መመገቡን ይቀጥላል። እኛም መቆራረጥ ካለብን ሕይወት ክርስቶስ “ተወለድ/ጅ” ሲለን ህልውናችንን የሚፈትን ነገር መስሎን እንዴት ልንልና ልንሸሸው እንችል ይሆናል፤ እውነቱ ግን ያ ካልሆነ ማደግ አንችልም። ዛሬ በሕይወታችን ወደ ክርስቶስ ይበልጥ እናድግ ዘንድ መቆራረጥ ያለብን ነገር ምን ይሆን ብለን እናስተንትን።

ብዙ ጊዜ ራስ ወዳድነታችን ራስን ወደማየት ብቻ ያሳድገንና የእግዚአብሔርን ፈቃድና ሰዎችን ማሰቡ ይከብደናል። ነጋ መሸ “እኔ” ና ለኔ ብቻ በሚል ዓይነት መጓዝን እንመርጥ ይሆናል፤ ይህ ከሆነ ግን በክርስትና ማደጋችን አቁሟል ማለት ነው። ከእኔነት ቅርፊታችን ካልወጣን ከኛ ውጭ የሆነውን መገንዘብ አንችልም፤ ያልተፈልፈለ ማንነት ወይም ያላደገ እምነት ይዘን በሥጋ ወደፊት እንጓዛለን። በዚህ ዓይነት ስብእና የክርስቶስን ሕማማትና ትንሣኤ ማክበሩ ትርጉም አይኖረውምና የዛሬው ወንጌል ከማንነታች ወጥተን ለክርስቶስና ለሌሎች የመኖርን ሕይወት፣ በእምነታችን ከዕለት ዕለት ማደግን እንድንለማመድ ይጋብዘናል። ይህ ካልሆነ ክርስቶስ የከፈለውን ዋጋ ሁሉ እንዳልተከፈለልን እናደርገዋለንና ዳግም መወለድ የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ለእኔ በምን መልኩ ተግባራዊ አድርጌ ለዘንድሮው የክርስቶስ ትንሣኤ ብርሃን ራሴን ላዘጋጅ ብለን በቅዱስ ቃሉና በምስጢራቱ ፊት እናስተንትን።








All the contents on this site are copyrighted ©.