2011-04-15 16:48:59

ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ታላቁን የሚሊንየም ግድብ ፕሮጀክት በማስመልከት ከሊቀ ጳጳሳት ጽ/ቤት የተሰጠ መልእክት


ሚያዝያ 7 ቀን 2003
በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
‹‹እግዚአብሔር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝም የለም

በለመለመ መስክ ያሳድረኛል

በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል ››

መዝሙረ ዳዊት 22
ታላቁ የኢትዮጵያ ሚሊንየም የዓባይ ወንዝ ግድብ ለሀገራችን ህዝብ የሚሰጠው ጠቀሜታ ዕቅድ በመንግስትና የኢትዮጵያ ሕዝብ ርብርብ እንደሚሳካ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እምነቷ ፍፁም ነው፡፡

‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› የምንለው የሀገራችንን የአበው አባባል ልማታዊና ዕድገታዊ አነሳሽነትን ጠቋሚ በመሆን በዚህ ንግግሬ ላይ መጥቀሴ በጣም ደስ ይለኛል፡፡

ትውልድ ያልፋል ትውልድ ይተካል፤ በዚህ የታሪክ ሂደት ውስጥ ለተተኪው ትውልድ ከፍተኛ የሆነ ምንጭ አመቻችቶ ማስተላለፍ


ፈጣሪ አምላካችን ያደለንን ተፈጥሮ በአግባቡ መጠቀም አለብን፡፡ ‹‹ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል›› እንዲሉ ለበርካታ ዓመታት ውሃ እየጠማን ከቤታችን በር ላይ ያለውን የዓባይን ወንዝ ውሃ እንኳን ቀድተን መጠጣት ተስኖን እንደነበር የሁላችን ልቦና ያውቀዋል፤ እስከዛሬ እምብዛም የተዘናጋን ባንሆንም ዛሬ ግን ለልጅ ልጅ የኢኮኖሚ ግንባታ ዋልታና ማገር እንዲሆን አስበንበት በመነሳታችን እስካሁን ግንዛቤ የለም ብለው የሚያስቡ ካሉም ከእንግዲህ ብልሆች እንደሆንን ይገነዘባሉ፡፡ እንዲሁም የምንሰራው ግድብ ዘለዓለማዊ ሀውልት ሆኖ ምስክርነቱን ሲሰጥ ይኖራል፤ በአንፃሩም ይህን አስቦበትና ሕዝቡን ለልማት አነሳስቶ በተግባር ለሚተረጉመው መንግስትና ሕዝብ በታሪክ ተጽፎ ሥራው ሲወደስ ይኖራል፤ ለኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም ዓባይ እንዲህ ላለ ልማት ሲውል ማየታችን ደስታችንን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡

አንድ ሀገር ጠንካራ ኢኮኖሚ በገነባች ቁጥር ለልማትና ለሕዝብ ዕድገት እንዲሁም ለተጀመረው ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ ልማት ማበብ ትልቅ መሠረት እንደተጣለ ስለምንቆጥር በጠቅላላ በኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ስምና በራሴ እንዲሁም በካቶሊካውያን ምዕመናን ስም ቦንድ ለመግዛት ከልብ የተነሳሳን መሆናችንን ከወዲሁ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ በዚሁ ዙሪያም ውሳኔ ለማድረግ በሚያዚያ ወር መጨረሻ የጳጳሳት ጉባኤ ተጠርቷል፡፡ ከዚህም ጋር በሀገርም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ካቶሊካውያን ምዕመናንም ሆነ ግለሰቦች እንዲሁም ተቋማት ለዚሁ ታላቁ የሚሊንየም ግድብ ፕሮጀክት ግድብ ስኬት በስሜት በመነሳሳት ቦንድ እንዲገዙና የተቻላቸውን እርዳታ እንዲለግሱ አሳስባለሁ፡፡

ፈጣሪ አምላክ ሀሳባችንን ከግብ ያደርስልን ዘንድ ጸሎታችን ነው፤ ለሀገራችን ዕድገት በጎ ዓላማ ካላቸው ጎን እንቆማለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
+ ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል

ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት ማህበራዊና ህዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ 








All the contents on this site are copyrighted ©.