2011-04-12 09:57:03

የቅዱስ መንበር ርእሰ አንቀጽ፦ ስም የለሽ ኃዘን


እንደ ተለመደው በሳምንት መገባደጃ የቅድስት መንበር የዜና ማኅተም ክፍል ተጠሪ እና የቫቲካን ረዲዮ ዋና አስተዳዳሪ አባ ፈደሪኮ ሎምባርዲ የሚያቀርቡት የቅድስት መንበር ርእሰ አንቀጽ በመቀጠል፣ ትላትና ከሰሜን አፍሪቃ አገሮች በማምለጥ የሜዲትራኒያን ባህር በተለያዩ ተናንሽ ባለ ሞተር ጀልባዎች በማቋረጥ ወደ ደቡብ ኢጣሊያ እና በኢጣሊያ በኩሉ ወደ ኤውሮጳ የሚጎርፈው የስደተኛው ጸአት አሁንም እየቀጠለ መሆኑ በማስታወስ፣ የሜዲትራኒያን ባሕር በማቋረጥ ወደ ኤውሮጳ ለመዝለቅ በሚደረገው ጉዞ ለሞት አደጋ የሚጋለጠው የስደተኛው ብዛት ከፍ እያለ መሆኑና በቅርቡ በዚህ የባህር ጉዞ የሞት አደጋ ያጋጠማቸው የአፍሪቃ ዜጎች ለአፍሪቃ እና ለዓለም ትልቅ የሕዘን ምክንያት ሆነዋል። ይህ ሥም የለሽ ስቃይ በእውነቱ የሚያሳዝን ብቻ ሳይሆን በርግጥ ለመላ ሰው ዘር በተለይ ደግሞ ለበለጸገው ዓለም የኅሊና ጥያቄ ነው። እ.ኤ.አ. በ 1979 ዓ.ም. ከድኽነት ከአሰቃቂ እርሃብ ከከፋው ጭቆና ከአመጽ እና ከጦርነት ለማምለጥ ተገደው ይሰደዱ ከነበሩት ውስጥ ለሞት የተዳረጉትን ዘክረው እነዚያ ማንነታቸው ያልተገለጠ ቁጥር ሆነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ተብለው ጠቅለል ባለ አንጋገር አለ መለያ እና ሥም የሚጠቀሱት ንጹሕን የቬትናም ዜጎች በማስታወስ፣ የዚህ ዓይነቱ ሥም የለሽ ሐዘን እና ስቃይ በሰው ልጅ ሕይወት ሲደጋገም ማየቱ የሚያሳዝን ብቻ ሳይሆን ሚዘገንን ነው።

በእያንዳንዳችን ልብ ያስከተለው ሐዘን ለሞት የተዳረጉትን ዘወትር ለመዘከር የሚያነቃቃ ኃይል መሆን አለበት። የያድ ቫሸም ለሞት የተዳረጉት የያሁድ ምእመናን ለመዘከር በየዓመቱ የሚደረገው አንድ በአንድ ለሞት የተዳረገውን በሥም የመዘከሩ ሂደት ትልቅ አብነት ነው። አነዚህ በናዚው ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት ለሞት የተዳረጉት የያሁድ ሃይማኖት ምእመናን በገፍ ለሞት የተዳረጉ ቢሆንም ቅሉ ስማቸው ግን ዘወትር የሚታወስ ነው። ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም ስማቸው ግን አልተለየም። በሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ትውስት የታተሙም ናቸው።

የናዚው ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት ያስከተለው የሰው ዘር የማጥፋት እልቂት እና አመጽ ዳግም እንዳይከሰት ነቅተን በመጠበቅ በምናደረገው ጉዞ በአሁኑ ወቅት የሚታየው ኢፍታሃዊነት የሰላም እጦት ግድ የለሽነት እና ራስ ወዳድነት እያስከተለው ያለው እልቂት ለማስወገድ ነቅተን ሰብአዊነት ማእከል የሚያደርግ ፍትህ ሰላም የሚሻ ባህል በማነቃቃት ማስወገድ የሁሉም ኃላፊነት ነው ካሉ በኋላ፣ እነዚህ የተሻለ የመጪው ሕይወት ለመሻት በሜዲትራኒያን ባሕር በመጓዝ ላይ እያሉ ለሞት የተዳረጉት ሁሉ እግዚአብሔር እንዲያስባቸው እና እኛም እናስባቸው በማለት ርዕሰ ዓንቀጹን ደምድመዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.