2011-04-11 09:55:19

የእያንዳንዱ የሰው ልጅ ህልውናን ለማውደም በመፈታተን ላይ የሚገኘው ኃጢኣት ነው፤ ኃጢኣትም መንፈሳዊ ሞት ነው።


ቅዱስ ኣባታችን ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ትናንትና እሁድ እኩለ ቀን የመል ኣከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት የዕለቱን ቃለ ወንጌል በመጥቀስ ኣስተምህሮ ኣቅርበዋል። እንደ ላቲኑ ሥርዓተ ኣምልኮ ግጻዌ የትናንትና እሁድ ቃለ ወንጌል ጌታ የማርታና የማርያም ወንድም ኣልኣዛርን ከሞት ያስነሣበት ተኣምራት የሚተርክ ኢየሱስ ትንሣኤና ሕይወት መሆኑን የሚገልጥ ከቅዱስ ዮውሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 11 የተወሰደ ነበር።

ቅዱስነታቸው ስለዚህ ትንሣኤ ሲገልጡ “የዕለቱ ንባባት የሚገልጡት ትንሣኤ የኢየሱስ ሳይሆን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በመነሣት ለእኛ ለሰው ልጆች የሰጠንና እኛ በመጠባበቅ ላይ ያለነው ትንሣኤ ነው” ሲሉ ኣብራርተዋል።

የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤን ለማክበር ሁለት ሳምንታት ብቻ በቀረን ወቅት ቅዱስነታቸው ሞት በክርስትያን ኣመለካከት ምን ትርጉም እንዳለው እንዲህ ሲሉ ገልጠዋል፤ ‘ሞት ለእኛ ክርስትያኖች ኣሻግረን እንዳንመለከት እንደሚከለክል ግድግዳ ነው፤ ሆኖም ግን ልባችን ከዚህ ግድግዳ ባሻገር ያለውን በእምነት ዓይን ያየዋል፤ እዛ ላይ ተደብቆ ያለውን ምሥጢራዊ ይዞታውን ሙሉ በሙሉ ባናውቀውም ለዘለዓለማዊ ሕይወት ያለንን ፍላጎት በተለያዩ ምልክቶች በመግለጥ ስለእርሱ ከማሰብና ከማሰላሰል ኣንቦዝንም፤ ዛሬ ከትንቢተ ህዝቅኤል 37፡12 በተነበበው፤ ዕብራውያን ከምድረ እስራኤል ተሰደው በነበሩበት ወቅት እግዚአብሔር የስደተኞቹን መቃብር በመክፈት ሕይወት እንደሚሰጣቸው ወደ ሃገራቸው በመምለስም ሰላም እንደሚያስፈንላቸው እንዲህ ሲል ተናግረዋል፤ ‘ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሕዝቤ ሆይ፥ እነሆ፥ መቃብራችሁን እከፍታለሁ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ፥ ወደ እስራኤልም ምድር አገባችኋለሁ። ሕዝቤ ሆይ፥ መቃብራችሁን በከፈትሁ ጊዜ ከመቃብራችሁም ባወጣኋችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። መንፈሴንም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፥ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፥ በገዛ ምድራችሁም አኖራችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ እንዳደረግሁም ታውቃላችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።’ ይህ በትውልድ ዘር በገዛ ኣገር ከወላጆች ጋር የመቀበር ፍላጎት ከዚህ ዓለም ኣድካሚ የህይወት ጉዞ የሚቀበል ሌላ ኣገር እንዳለ ያመለክታል፡ ይህ ኣስተሳሰብ የትንሣኤን ተስፋ ያመለክታል፤ ይህ ኣስተሳሰብ በብሉይ ኪዳን በመጨረሻ ገጾች እናገኘዋል፤ ሆኖም ግን በኢየሱስ ግዜም ይሁን ኣይሁዶች በሙሉ በዚህ ኣስተሳሰብ ኣይስማሙም ነበር፡ በክርስትያኖች መካከልም ቢሆን ስለ ትንሣኤ ሙታንና ዘለዓለማዊ ህይወት በተለያዩ ግዝያት ብዙ ክርክሮችና ጥርጣሬዎች ታይተዋል፤ ምክንያቱም ምሥጢረ ትንሣኤ በሰው ልጅ ኣስተሳሰብ ልትረዳውና ልትገልጠው ኣስቸውጋሪ በመሆኑ የግድ የእምነት ሥራ ያስፈልጋል። የዚህ ዓይነት እምነት በዛሬው ወንጌል በማርታ ኣንደበት ሲነገር እንሰማለን፤ ‘ማርታም ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ አለችው። ኢየሱስም። ወንድምሽ ይነሣል አላት። ማርታም። በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ አለችው። ኢየሱስም። ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት። እርስዋም። አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ አለችው።’ እውነተኛው ኣዲስ ነገር ይህ ነው፤ ክርስቶስ የሞት ግድግዳን ኣፍርሶታል፤ የሞት ግድግዳውን ኣፍርሶ ከዛ በላይ መጥቀዋል፤ እርሱ ራሱ ዘለዓለማዊ ሕይወት በመሆኑ የእግዚአብሔር ሙላት በእርሱ ላይ ይኖራልና፤ ለዚህም ነው ሞት በእርሱ ላይ ሥልጣን ሊኖረው ያልቻለበት ምክንያት፤ በእግዚአብሔር ፊት እንደ እንቅልፍ የነበረው የኣልኣዛር ሞትና የኣልኣዛር ከሞት መነሣት ጌታ በሞት ላይ የነበረውን ሥልጣን ያሳያል።” ሲሉ ስለ ሥጋዊ ሞትና ጌታ በሞት ያለውን ሥልጣን ከገለጡ በኋላ ስለ ሌላው የባሰ ሞት ማለት የነፍስ ሞት የሚያስከትል፣ ስለ ኃጢኣት የሚከተለውን ብለዋል፡ ‘ለጌታ ብዙ ያስታገለው እስከ በመስቀል ላይ በመዋል ለሞት የዳረገው ሌላ ዓይነት ሞት ኣለ፤ መንፈሳዊ ሞት ይህም ኃጢኣት መሆኑ ነው። ኃጢኣት የሰው ልጅ ህልውናን የሚፈታተን ኣደገኛ ጠላት ነው። ይህንን ሞት ለመሻር ክርስቶስ ሞተ፡ የጌታ ትንሣኤ ወደ ነበርንበት ህይወት መመለስ ሳይሆን ለኣዲስ ህይወት ክፍት መሆንና ለኣዲስ ኣገር መዘጋጀት ነው፤ ይህም ኣዲስ ኣገር የሰማያት መንግሥት ነው፤ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮማውያን በጻፈው መልእክት ‘ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፥ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው። ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል።’ በማለት የሚያስተምረው።” ሲሉ ከዚህ መንፈዊ ሞት መነሣት ያለብን ግዜ ኣሁን መሆኑን ኣብራርተዋል።
በመጨረሻም ቅዱስነታቸው የዚህ ትንሣኤ ተሳታፊ ለሆነችው እመቤታችን ድንግል ማርያም እንደ ኣልኣዛር እኅት ማርታ በእምነት ‘ኣዎ ጌታ ኣንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ መሆንህን ኣምናለሁ’ ለማለት ብቃት እንዲኖረን ጸጋ እንድታስገኝልን ዘንድ እንድንማጠናት ኣደራ ሲሉ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ኣሳርገው ምእመናኑና ነጋድያኑን በተለያዩ ቋንቋዎች በማመስገን ሓዋርያዊ ቡራኬ ችረዋል።







All the contents on this site are copyrighted ©.