2011-03-26 13:03:25

ዘደብረ ዘይት


(ከሲታውያን ድረ ገጽ የተወሰደ) ዛሬን በዝግጁነት ለክርስቶስ መኖር - ዘደብረ ዘይት
ምስባክ ዘደብረ ዘይት፦ እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመጽእ፤ ወአምላክነሂ ኢያረምም፤ እሳት ይነድድ ቅድሜሁ።

እግዚአብሔር ግልጽ ሆኖ ይመጣል፤ አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይቃጠላል።

መዝ.49(50):3

ንባባት፦- ማቴ.24:1-36 - 1ተሰ.4:13-18 - 2ጴጥ.3:7-14 - ሐዋ.24:1-21

ይህ ሰንበት ዘደብረ ዘይት ይባላል፤ እኩለ ጾምን ያመለክታል። የዕለቱም ወንጌል በዋነኛነት ጌታ በዳግም ምጽአቱ የሚከሠቱትን ሁኔታዎች በልዩና በጣም ትእይንታዊ በሆነ መልኩ ገልጾ የሰው ልጆች ደግሞ ምድርና ሁለንተናዋ በሚናወጡበት ሁኔታ ውስጥ እንኳ በእርሱ እምነት በመጽናት መኖር እንደሚገባቸው ያሳየናል።

በጾመ አርባ እኩሌታ ላይ ይህን መሰል የዳግም ምጽአት ሀሳብ መንጸባረቁ ጾማችን፣ ጸሎታችንና ምጽዋታችን ሁሉ ክርስቶስን ያማከለ መሆን እንዳለበት ለመገንዘብ ያግዘናል። ምናልባት ወንጌሉ ውስጥ እንደምናነበው ነገሮች በጣም ስዕላዊ ሆነው በዙሪያችን ባንታዘባቸውም በዛሬው ዓለም ብዙ መሳይ እውነታዎች አሉ። ዛሬ ዛሬ በቀጥታም ባይሆን እኔ መሲሕ ነኝ የሚሉን ጥቂት አይደሉም። ከፍ ባለው ደረጃ ስናይ የፖለቲካ መሪዎች የሚገቡት ቃልና የሚሰጡት ተስፋ፣ በአንድ የትምህርት አቅጣጫ ብቻ የሞላ የሚመስለው ሰው በሌላ ብዙ ነገሮች ወደ ኋላ መሆኑን ዘንግቶ “እኔን ስሙኝ” ሲል፣ በሃይማኖትም ስም ሰላምና ደኅንነት እዚችጋ ብቻ ነው ያለችው የኛን ስብከት…ካልሰማችሁ ጠፋችሁ…ወዘተ የምንል ሁሉ ቃል በቃል ባንለውም መሲሕነትን ለመጋራት እየቃጣን ነው።   በዕለታዊ አናኗራችን ደግሞ ሰው ራሱን ብቻ ማየት፣ ለራሱ ብቻም መኖርና ሌላውን መርሳት፣ መርሳትም ብቻ ሳይሆን መናቅ፣ መጥላትና ግድ የለሽ መሆን ከጀመረና ክርስቶስን ከሕይወቱ ካስወጣ ሌላስ ምን ትርጉም ሊሰጠው ይችላል? ቃሉም “ከክፋት ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች” (ቁ.12) ይላል። ለሌሎች ያለን ፍቅር ይታደስ ዘንድም የዚህ ጾም ወቅት ልዩ ግብዣ ነውና ሰው ለሰው ያለንን ክርስቲያናዊ ፍቅር እንመርምር።

ስለ ዓለም ፍጻሜ ሲነገር ደግሞ ሌላውን ትተን ባለፈው ክፍለ ዘመን የዓለም ፍጻሜን የሰበኩ ብዙ ዓይነት እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ እናውቃለን። የቀን መቁጠሪያቸው ላይ ምልክት አድርገውዓለም በዚህ ዓመት፣ ወርና ቀን ያከትምላታል ተዘጋጁ…ብለው ራሳቸውን በአንድ ቦታ ዘግተው በመጠባበቅ ያ ዕለት እንደማንኛውም አዘቦት ቀን ሲያልፍ ተደጋግሞ ተስተውሏል። ይህን መሰል “ትንቢት” ከነበራቸው ስብስቦች አንዱ በ1946 ዓ.ም. ታኅሣሥ ዓለም ሂሳቧን ትዘጋለች፣ ይህ ነው ሊባል የማይችል ጎርፍ ያጥለቀልቃታል…ወዘተ ብሎ ነበር። የዚህ ስብስብ መሪ የነበረችው ሴት ከነተከታዮቿ በአንድ ላይ ሆነው እኛ ግን በዚያን ዕለት ወደ ላይ እንነጠቃለን… በማለት ሲጠባበቁ ቆይተው ያ ቀን የሀሳብ እንጂ የእውነት ጎርፍ ሳይመጣበት እንደ ማንኛውም ቀን ነግቶ መሸና አለፈ። ከዚያም ያው ስብስብ ይህ ነገር ያልተከሠተው እኛ ተሰባስበን በመጸለያችን ነው በማለት ለማስተባበል ሞከሩ። ይህ ከብዙዎች አንዱ እውነተኛ ምሳሌ ነው። የዛሬዎቹ ንባባት ዓላማ ግን ይህን መሰል መልእክት ማስተላለፍ አይደለም። ብዙዎች ይህን መሰል ስብከት ቢያስተጋቡም የወንጌሉ ቁልፍ መልእክት ግን ዛሬን እንዴትና ለምን እንደምንኖር ለማመልከት ነው።

“ቀለል ባለ አማርኛ የተተረጎመ” በሚለው የ1980 መጽሐፍ ቅዱስ ለማቴዎስ 24 የመጀመሪያዎቹ ቁጥር የተሰጠው ርእስ “ስለ ዓለም መጨረሻ” ይላል። መቼ ይሆናል ብሎ መጠየቅና መልሱን መጠበቅ አስቸጋሪ ትግል ነው፤ ብንጠየቅም የምናውቀው ነገር እንደሌለና ሁሉ የእግዚአብሔር ሥራ እንደሆነ እንመልሳለን፤ እውነት ነው ክርስቶስም ይህ ሥልጣን የርሱም ሆነ የኛ ሥልጣን እንዳልሆነ ነግሮናል። መቼ ለሚለውም ጥያቄ በርግጠኝነት የምናውቀው ነገር የለም። ነገር ግን ውስጣችንን ካየን ያ “መጨረሻ” ዛሬ እንዳለሆነ ከሞላ ጎደል ብዙዎቻችን ርግጠኞች የመሆን ግንዛቤ ሊኖረን ይችላል። ለዚህም አናኗራችንን ማየት ይበቃል። ዓለም ዛሬ ያበቃለታልና ብለን የሆነ ያልሆነ “ትንቢት” ለማስፋፋት ሳይሆን ዛሬን በዝግጁነት ለክርስቶስ መኖር ግን ይህን የክርስቶስ የዓለም መጨረሻ ትረካ ማስታወሱ ለተግባራዊ ውሳኔያችን አጋዥ ነገር ነውና ዛሬያችንን እንደ ክርስቲያን ለመኖር እንነቃቃ።

የምኖረው ለምንድነው ብሎ የማይጠይቅ ሰው ምናልባት ገና መኖርን አልጀመረም ማለት ይቻላል። ለዚህና ለዚያ ነው ማለቱ ባይቻልም ግን በጉዞ ላይ መሆናችንና ወደ አንድ አቅጣጫ ሕይወታችን እያለፈች መሆኑን ማንም አይክድም። ታዲያ እየተጓዙ ወዴትና ለምን ያለማለት ካለምጓዝ አይተናነስም። ከክርስቲያናዊ እይታ አንጻር የዚህን መልስ በሁለተኛው የጴጥሮስ መልእክት ውስጥ እናገኛለን፦ “አንዳንድ ሰዎች እንደሚመስላቸው ጌታ ኢየሱስ የተናገረውን የተስፋ ቃል ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ እንጂ ማንም ሰው እንዳይጠፋ ፈልጎ ስለ እናንተ ይታገሣል”። ለንስሐ ማለት ይበልጥ ወደ አምላካችን እንድንቀርብ ማለት ነው። ይህ እውነት በተቃራኒው እየሆነብን ይመጣል፤ በዕድሜ ይበልጥ ባደግን ቁጥር ይበልጥ ከእግዚአብሔር ማለትም ከእምነታችንና ከቤተ ክርስቲያናችን እየራቅን ስንመጥ ይስተዋላል። ይህ ዓይነት ጉዞ ግን መለመድና መቀጠል እንደሌለበት እናስተውል። ይህ እንግዲህ ለምን እንኖራለን የሚለውን ካመላከተን እንዴት የሚለውም ከዚያ የተለየ አይደለም።

በወንጌሉም ቢሆን ማእከላዊ መልእክቱ በዓለም ፍጻሜ ሊሆን ያለው የመብረቅና የምድር መናወጥና የመአት ጋጋታን መተረክ ሳይሆን እንዴት መኖር እንዳለብን መናገር ነው፦ “በዚያን ጊዜ ብዙዎች ሀይማኖታቸውን በመካድ ይሰናከላሉ፤ አንዱ ሌላውን አሳልፎ ይሰጣል፤ ሰዎችም እርስ በርሳቸው ይጣላሉ። …ከክፋት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻ በትዕግሥት የሚጸና ግን ይድናል።” ይላል። ሃይማኖትን መካድ፣ ሌላውን አሳልፎ መስጠት፣ እርስ በእርስ መጣላት፣ የፍቅር መቀዝቀዝ…ዛሬ የሌሉ ነገሮች ናቸው ካልን ስህተት ሊሆን ይችላል። የራሳችን ሕይወት ውስጥ ገብተን መልሱን እናርመው። ስለዚህ እንዴት መኖር አለብን ካልን ሀይማኖታችንን ባለመካድ፣ ሌላውን አሳልፎ በመስጠት ሳይሆን ለሌላው ራሳችንን አሳልፈን በመስጠት፣ እርስ በርሳችን በመፋቀር…መሆኑን አውቀን ይህን የጾም ወቅት እናትርፍበት።

ይህን አስተንትኖ በጴጥሮስ ጥቅስ እንደምድመው “ስለዚህ ወዳጆች ሆይ!...ጌታ ያለ ነውር ወይም ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም እንዲያገኛችሁ በትጋት ሥሩ።” 2ጴጥ.3:14








All the contents on this site are copyrighted ©.