2011-02-21 15:22:16

የቅድስት መንበር ርዕሰ ዓንቀጽ፣ ሕሙማን እና ቤተ ክርስትያን


የቅድስት መንበር የዜና እና ማኅተም ክፍል ተጠሪ የቫቲካን ረዲዮ ዋና አስተዳዳሪ አባ ፈደሪኮ ሎምባርዲ በሳምንት መገባደጃ የሚያቀርቡት የቅድስት መንበር ርዕሰ አንቀጽ በመቀጠል ትላንትና ሕሙማን እና ቤተ ክርስትያን በሚል ርእስ ሥር ተመርቶ ባቀረቡት ርዕሰ ዓንቀጽ ቤተ ክርስትያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዓመታዊ በዓለ ማርያም ዘ ሉርድ ከሚከበርበት ቀን ጋር ተያይዞ ዕለተ ሕሙማን ታስቦ RealAudioMP3 እንዲውል በር.ሊ.ጳ. የእግዚአብሔር አገልጋይ ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ውሳኔ መሠረት በኵላዊት ቤተ ክርስትያን የሚታሰበው ዕለተ ሕሙማን፣ በሽታ የእምነት ተመኵሮ ሆኖ በእያንዳንዱ አማኝ ልብ የእያንዳንዱ ሰው ልጅ የሕይወት ምዕራፍ እንጂ ፍጻሜ እንዳልሆነ እንዲታመንበት የሚያሳስብ ዕለት መሆኑ በማብራራት፣ ስቃይ በሥጋ እና በአዕምሮ ፊት ተጋርጦ ፍቅርን ሰብአዊ ተመኵሮን እና እምነትን የሚፈታተን መሆኑ ገልጠው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለታመሙት ለታረዙት በጠቅላላ በስቃይ ላይ ለሚገኙት ቅርብ ብቻ ሳይሆን የሆኑትን ሆኖ በገዛ እራሱ ስቃይ እና ሞት የሰጠው የሕይወት ጥልቅ ትርጉም ቤተ ክርስትያን ተረክባ ይኸው በሕሙማን ዕለት ሕያውነቱን በማረጋገጥ ለታመሙት እና ለታረዙት ቅርብ በመሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትመሰክራለች ብለዋል።

አክለውም ኵላዊት ቤተ ክርስትያን ለር.ሊ.ጳ. የእግዚአብሔር አገልጋይ ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ብፅዕና በይፋ ለማወጅ በምትዘጋጅበት በአሁኑ ወቅት ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በእምነት ሥር የተኖረ ስቃይ መስካሪ የዓለም ስቃይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል ሱታፌ በመኖር ለሁሉም ሕሙማን አባት ወዳጅ መሆናቸው የምናስታውስበት ዕለት ብቻ ሳይሆን ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ የሰው ልጅ ልክነቱ የሚወሰነው ከስቃይ እና ከሕማም ጋር ካለው ግኑኝነት መሆኑ እና የሚያጋጥም ስቃይ እና በሽታ ተቀብሎ ጥልቅ ትርጉም ለመሻት በሚሳነው፣ በስቃይ እና በሕማም የሚገኙትን የሚያገል ማኅበርሰብ ከዚህ ፈተና ተላቆ ለእያንዳንዱ ሰው ልጅ የሚያጋጥም ስቃይ እና በሽታ ሁሉም በየፊናው ተባባሪ እና ተሳታፊ መሆን የሚያሳስብው የጥሪ ግንዛቤ የሚረጋገጥበት ዕለት ነው ብለዋል።

ስቃይ በሽታ እና መከራ ፍቅርን ይጠራል ይቀሰቅሳል፣ አለ ስቃይ እና መከራ አለ በሽታ የፍቅር ጥልቅ ትርጉምን ለመረዳት አንችልም፣ በሰብአዊነት ዕለት በዕለት እንድናድግ በሽታን በጥልቀት ለመረዳት እና የሚያጋጥመን በሽታ ተስፋ የሚያጨልም እንዳልሆነ መገንዘብ እና መኖር አስፈላጊ ነው በማለት ርዕሰ አንቀጹን ደምድመዋል።







All the contents on this site are copyrighted ©.