2011-02-21 15:18:07

የር.ሊ.ጳ የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ ኣስተምህሮ

እ.ኤ.አ. 20/02/2011


ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ ትላንትና እሁድ እኵለ ቀን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የዕለቱ የወንጌል ንባብ መሠረት በማድረግ ጸሎተ መልአከ እግዚአብሔር ከማሳርረጋቸው በፊት በሕይወቱ እግዚአብሔርን የሚቀበል እና የሚያስተናግድ በፍቅር ሕይወት የሚዘራ ኅልውና ያረጋግጣል በሚል ጥልቅ ሀሳብ ላይ ያተኮረ አስተምህሮ ማቅረባቸው RealAudioMP3 የቅድስት መንበር መግለጫ አስታወቀ።

ቅዱስነታቸው በዚህ ከኢጣልያ እና ከውጭ አገር የተወጣጡ በብዙ ሺሕ የሚገመቱ ምእመናን በተገኙበት ባቀረቡት አስተምህሮ፣ ለሚያጋጥመን መከራ እና ለሚደርስብን ስደት እና ስቃይ ተጠያቂ ለሆኑት ተበቃዮች ከመሆን እንድንቆጠብ በማሳሰብ፣ ክፋትን በክፋት ሳይሆን በፍቅር ሙሉ በሙሉ እንደሚሸነፍ እና ይኸንን እግብር ላይ ለማዋል በፍቅር የተመራ አዲስ የኗኗር ሥልት ወሳኝ መሆኑ፣ የዕለቱ ምንባበ ወንጌል ማቴዎስ ምዕራፍ 5 ከቁጥር 38 እስከ 48 ያለውን መሠረት በማድረግ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጠላቶቻችሁን ውደዱ ስደትና መከራ ለሚያደርሱባችሁም ጸልዮላቸው በማለት የሰጠው መሪ ቃል በመከተል ቂም በቀል መያዝ እንደማይገባ በመግለጥ፣ ይህ በእግዚአብሔር የጸናው አዲስ ደንብ እና ሕግ ባለእንጀራህን እንደ ራስህ ወደድ ለሚለው ማኅበራዊ ሕግ መሠረት ነው ብለዋል።

እግዚአብሔር ሥጋችንን ለብሶ እንደኛ ሰው ሆኖ ለእያንዳንዳችን ቅርብ በመሆን እያንዳንዱ ለባለእንጀራው ቅርብ እንዲሆን የሚያደርግ የፍጹም ፍቅር ኅያው አብነት ሆነዋል፣ ስለዚህ ሁላችን ለዚህ ቁርጠኝነትን ለሚጠይቀው ግብ መጠራታችን ገልጠው፣ ይኸንን ክርስቶሳዊ ጥሪ ተቀብሎ ለመኖር የመንፈስ ጽናት እደሚጠይቅ ቅዱስ አባታችን በማብራራት፣ በሕይወቱ እግዚአብሔርን የሚቀበል እና የሚያስተናግድ በሙሉ ልብ የሚያፈቅር በፍቅር ሕይወት የሚዘራ ዘለዓለማዊ ሕይወት የዕጣ ፈንታው የሆነው ኅልውና ያረጋግጣል ብለዋል።

ክርስቶስን መምሰል በተሰየመው መንፈሳዊ መጽሓፍ፦ ፍቅር፣ ሸክምን የሚያቀል አስቸጋሪ የሆነውን ሁሉ እንድንችለው እና እንድንወጣው በምድራዊ ነገሮች ሳንገታ ወደ ላይ እንድንመነጥቅ የሚያደርግ አቢይ ኃይል መሆኑ የሚያብራራውን ጥቅስ በማስታወስ፣ ፍቅር ከእግዚአብሔር የሚወለድ ፍጻሜውም እግዚአብሔር ነው ብለዋል።

በመጨረሻም እ.ኤ.አ. የካቲት 22 ቀን የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል ዓመታዊ በዓል የሚከበርበት ዕለት መሆኑ በመዘከር፣ ለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞችን በእምነት እንዲያጽናና እንዲያበረታታ እንዲደግፍ እርሱም የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ ሰማይ ያቀና ዘንድ መምህር እና እረኛ እንዲሆን የተሰጠው ሐዋርያዊ ኃላፊነት መሠረት በእግዚአብሔር የተጠሩ እረኞች የእግዚአብሔር ሕዝብን እንዲመሩ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተኖረው ሐዋርያት የራሳችው በማድረግ የኖሩት በፍቅር ላይ የጸናው የሕይወት ሥልት ይኖሩ ዘንድ ምዕዳን አቅርበው፣ ጸሎተ መልአከ እዚአብሔር አሳርገው ለሁሉም መልካም እሁድ ተመኝተው በተለያዩ ቋንቋዎች ሰላምታን አቅርበው ሐዋርያዊ ቡራኬ በመስጠት የሰጡትን አስተምህሮ ደምድመዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.