2010-12-08 16:41:55

የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የመልኣከ እግዚአብሔር ጉባኤ ኣስተምህሮ (08.12.2010)


በላቲኑ ሥርዓተ ኣምልኮ ግጻዌ ዛሬ በዓለ ፅንሰታ ለማርያም ነው፣ ይህንን በዓል ምክንያት በማድረግ ቅ.ኣ.ር. ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ዛሬ እኩለ ቀን በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ የበዓሉን ቃለ እግዚአብሔር በመመርኮስ የሚከተለውን ኣስተምህሮ ኣቅርበዋል። ‘ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፣ ለዛሬው የመልአከ ጸሎት ግኑኝነታችን ልዩ ድምቀት የሚያለብሰው የእመቤታችን ድንግል ማርያም በዓለ ፅንሰታን እናከብራለን፣ የዛሬው ቃለ ወንጌል መልአኩ ገብርኤል የኢየሱስ መወለድ ለእመቤታችን ድንግል ማርያም እንዳበሠራት የሚገልጽ ከሉቃስ ወንጌል 1፣26~38 የተወሰደ ነው፣ የእግዚአብሔር መልእክተኛው ‘በጸጋ የተሞላሽ ደስ ይበልሽ፣ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው’ ይላታል፣ በዚህም ማርያም የሚለው ስም ምን ያህል ጥልቅ ትርጉም እንዳለው በመግለጥ ማንነትዋል ያብራራል፣ ይህ ስም ከሁሉም የጣፈጠ እግዚአብሔር እመቤታችንን በሱ የሚጠራት ጸጋ የሞላው ስም ነው። ይህ አጠራር ከሕፃንነታችን ጀምረን በሰላመ ቅዱስ ገብርኤል በምንደግምበት ግዜ የምንጠቀምበት ስለሆነ የተለመደ ነው፣ ዛሬ ለምናከብረው በዓል ትርጉምም ይገልጥልናል። እመቤታችን ድንግል ማርያም በወላጆችዋ ከተፀነሰችበት ግዜ ጀምራ ልዩ በሆነ በእግዚአብሔር ጸጋና ጥበቃ ለዘለዓለማዊ የደኅንነት ዓላማ ስለመደባት እንደኛ ሰው ለሆነው ልጁ እናት እንድትሆን ስለመደባት ከኣባታችን ኣዳም ኃጢኣት ጠበቃት፣ ነጻ ኣድርጎም ፈጠራት። ለዚህም ነው መልአኩ ባቀረበው ሰላምታ ከዘለዓለም የእግዚአብሔር ፍቅር ማደርያ የጸጋው ማደርያ ብሎ ሰላምታ ያቀረበላት።

የአለ ኣዳም ኃጢኣት መፀነስ ምሥጢር የውሳጣዊ ብርሃን ምንጭ ነው፣ የተስፋና የመጽናናት ምንጭም ነው፣ የሰው ልጅ በሕይወቱ በሚያጋጥሙት ፈተናዎች በተለይም እያንዳንዳችን በኅሊናችንና በኣከባብያችን በሚያጋጥሙን እርስ በእርስ የሚቃረኑ ሁኔታዎች ተከበን ብምንገኝበት ግዜ የክርስቶስ እናት የሆነች እመቤታችን ድንግል ማርያም ‘ጸጋ ከኃጢኣት እጅግ ይልቃል፣ የእግዚአብሔር ምሕረት ከመጥፎ ነገር እጅግ ከፍ ያለና ቻይ በመሆኑ ሁሉንም ነገር ወደ በጎ ነገር ሊለውጥ ይችላል’ ትለናለች።በዕለታዊ ኑሮኣችን በተለያዩ ኣጋጣሚዎች ክፋት ሲያስቸግረን እንመለከታለን፣ የባሰውኑ ደግሞ ይህ ክፋት የሚገኘው በሰው ልጅ ልብ መሆኑ፣ ይህ ልብ የታመመና የቆሰለ ልብ ነው፣ በገዛ ራሱ ከዚህ ሕመም ለመዳን ኣይችልም፣ ቅድስ መጽሓፍ የዚሁ ክፋት ምንጭ ለእግዚአብሔር ፍላጎት አለመታዘዝ መሆኑ ይገልጥለናል፣ እንዲሁም በዚህ ዓለም ሞት ሥልጣን ያገኘው የሰው ልጅ በገዛ ፈቃዱ የክፋት ኣባት የሆነው የዲያብሎስ ፈተናን በመቀበሉ መሆኑንም ያስተምረናል። እግዚአብሔር ግን በዚሁ በሰው ልጅ ውድቀት ከፍቅርና ከሕይወት ዕቅዱ ሊገታ ኣልቻለም፣ ትዕግሥት በተሞላበት ረዥም የዕርቅ ጉዞ ኣዲሱና ዘለዓለማዊ ኪዳኑን ኣዘጋጀ፣ ኪዳኑም በኣንድያ ልጁ ደም እንዲታተም ኣደረገ፣ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ገላትያ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ 4፣4 እንደገለጸው ይህ ከሴት ልጅ የተወለደው ኣንድያ ልጁ ለሰው ልጅ ጥፋት ካሣ እንዲሆን ሕይወቱን መሥዋዕት ኣቀረበ። ይህንኑን ኣንድያ የእግዚአብሔር ልጅ የወለደች ድንግል ማርያም የድኅንነታችን ዋስትና ከሆነው ከልጁ ሞት በፊት ከመጸነስዋ ጀምሮ ክፋቱ እንዳይነካት እግዚአብሔር ጠበቃት፣ ይህም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕማማትና የትንሣኤ ትሩፋት ኣስቀድሞ በጸጋው ሰጣት፣ በዚህ ምክንያት ይህች ያለ ኣዳም ኃጢኣት የተፀነሰችው እመቤታችን ድንግል ማርያም በንፁሕ ልብዋ ወደ ኢየሱስ ተጠጉ እርሱ ያድናችኋል ትለናለች።

ውድ ጓደኞቼ ዛሬ ማምሻውን በፕያሳ እስፓኛ በሚገኘው ለእመቤታችን ክብር ብታነጸው ኃውልት በዘልማድ የምናደርገውን ሥርዓተ ጸሎተ ሰርክ እንደገና ኣሳድሳለሁ። በዚሁ የኣክብሮት ሥርዓት የሮማና የመላው ዓለም ኣማንያን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ለሰጠችን እመቤታችን ያልቸውን ፍቅር ኣቀርባለሁ። የቤተ ክርስትያንና የመላዋ ዓለም ኣንገብጋቢ ጥያቄዎችን ለኣማላጅነትዋ ኣማጥናለሁ፣ በእግዚአብሔር እምነት እንዲኖረን በቃሉም እንድናምንና እንድንጸና እንዲሁም ክፋትን ትተን በጎ ነገርን ለመምረጥ ትርዳን፣ በማለት ትምህርታቸውን ከደመደሙ በኋላ ጸሎተ መልአክ እግዚአብሔር ኣሳርገዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.