2010-12-06 15:53:52

የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የመልኣከ እግዚአብሔር ጉባኤ ኣስተምህሮ(05.12.2010)


ቅ.ኣ.ር. ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ትናንት እኩለ ቀን በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ የዕለቱን ቃለ እግዚአብሔር በመመርኮስ ኣስተምህሮ ኣቅርበው በዚሁ ቀናት የሰው ልጆች መብትና ነፃነት በመጣስ በሚፈጸሙ ድርጊቶች የተሰማቸውን ቅሬታ በመግለጥ ሁላችን በተለያዩ ሰው ሰራሽ ኣደጋዎች ስለተጐዱ ወገኖች እንድጸልይ ኣደራ በማለት ከምእመናንና ከተለያዩ ቦታዎች ከመጡ ነጋድያን ጋር ጸሎተ መልኣከ እግዚአብሔር ኣሳርገዋል።

ቅዱስነታቸው ያቀረቡት ኣስተምህሮ የሚከተለው ነው፣ ‘ውድ ወንድሞቼና ኣኅቶቼ፣ የዛሬው የሁለተኛው ዘመና ምጽአት እሁድ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ተልእኮ ያቀርብልናል፣ ኢሳይያስ ነቢይ በትንቢቱ 40፣3 ላይ ‘የዐዋጅ ነጋሪ ድምፅ እንዲህ ይላል፣፣ የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ኣዘጋጁ፣ ለአምላካችን አውራ ጐዳና በበረሃ ኣስተካክሉ። ሸሎቆው ሁሉ ከፍ ይላል፣ ተራራውና ኰረብታው ሁሉ ዝቅ ይላል፣ ወጣ ገባው ምድር ይስተካከላል፣ ሰርጓጒጡም ሜዳ ይሆናል። የእግዚአብሔር ክብር ይገለጣል ሰው ሁሉ በአንድነት ያየዋል፣ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና’ ባለው መሠረት ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በይሁዳ ምድረበዳ በመሄድ ስብከቱን ጀመረ፣ ሕዝቡን መሲሁ በሚመጣበት ግዜ ለመቀበል ብቃት እንዲኖረው ዘንድ እንዲለውጥና እንዲታደስ ለንስሐ ጠራ፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዐቢይ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ እንዲህ ይላል፣ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ሕዝቡ በእግዚአብሔር ፀጋ ኃይልና አንጸባራቂው እውነት ልባቸውን እንዲነካና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና በመንፈሳቸው ንጹሕ ሓሳብ እንዲኖራቸውና ቃለ እግዚአብሔር በመስማት ወደ መልካም ነገር እንዲመራቸው እውነተኛው እምነትና መልካም ሥራን ኣስተማረ’ ይላል። ኢሳይያስ ነቢይ በሌላው ትንቢቱ 11፣2 ‘የእግዚአብሔር መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ፣ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል’ እንዳለው ኢየሱስን በመምራት ሕዝብን ለማዘጋጀት የተላከው ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ፀሐይ ከመውጣትዋ በፊት እንደሚወጣው የንጋት ኮከብ በአዲስና አሮጌው ኪዳን መሃከል ትስስር ፈጠረ።

በዚሁ የዘመነ ምጽአት እኛም በዚሁ ምድረ በዳ ዓለማችን በቅዱስ መጽሐፍና በመንፈስ ቅዱስ የሚሰበከው የእግዚአብሔር ድምፅን ለመስማት ተጠርተናል፣ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮማውያን በጻፈው መልእክቱ 15፣4 ‘በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።’ እንዳለው እምነት ሁል ግዜ በመለኮታዊ ቃል እንዲበራ የተውነው እንደሆነ ይጠነክራል። ቃለ እግዚአብሔር ልብ ብሎ የመስማትና እተግባር ላይ የመዋል አብነትና ምሳሌ እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት፣ ቅዱስ ኣምብሮዝዮስ ይህንን ሲያብራራ ‘ሁለመናዋ በቃለ እግዚአብሔር የታንጸችውን የእመ ኣምላክ እመቤታችን ድንግል ማርያም ኑሮ በማስተንተን እኛም በዚሁ ጌታ በሕይወታችን ውስጥ ለመኖር በሚያደርግ በምሥጢረ እምነት ለመግባት የተጠራን መሆናችንን እንገነዘባለን። አማኝ የሆነ እያንዳንዱ ክርስትያን እንደ እመቤታችን ድንግል ማርያም የጌታን ቃል ጸንሶ ይወልዳል ለማለትም ይቻላል።

ውድ ጓደኞቼ፣ ትልቁ ጸሓፊ ሮማኖ ጓርዲኒ እንደሚለው ደኅንነታችን በጌታ መምጣት ይጠጋል፣ የአዳኙ መምጣት ከእግዚአብሔር ነፃ ፍላጎት የተደረገ ነው፣ የእምነት ጉዳይም እንደዛው በፍቅሩና በነፃነቱ የቀረበውን ለመቀበል የሚደረግ ነፃ ውሳኔ ነው። አዳኙ ወደ እያንዳንዱ የሰው ልጅ ይመጣል፣ በደስታውም ይሁን በሓዘኑ ግዜ፣ ሁሉም ግልፅ ሆነ በሚበራበት ግዜም ይሁን በመጠራጠርና በፈተና ግዜ፣ በአጠቃላይ ባህርዩንና ኑሮውን በሚያቋቍሙ ሁኔታዎች ውስጥ ይመጣል።

በማኅፀንዋ የእግዚአብሔር ልጅን ያሳደረች ድንግል ማርያም በተለይም በሚመጣው ታሕሣሥ 8 ደግሞ የኣለኣዳም ኃጢኣት መፀንስዋ በዓል ለማክበር በምንዘጋጅበት ግዜ በዚሁ መንፈሳዊ ጉዞ እንትደግፈንና የአዳኙን መምጣት በእምነትና በፍቅር እንድንቀበል ትርዳን ዘንድ እንለምናት’ በማለት ኣስተምህሮኣቸውን ደምድመዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.